ቅዳሜ ጥቅምት 17 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በኢትዮጵያ በተለይም በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለውን ግጭት ተከትሎ፤ የሰብአዊ መብት ጥሰት መፈጸሙን እንዲሁም በደርዘን የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች መጉዳታቸውን አስመልክቶ የሚደርሱት ሪፖርቶች በእጅጉን እንዳሳሰቡት የአውሮፓ ኅብረት አስታውቋል፡፡
በኅብረቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሓላፊ የሆኑት ጆሴፕ ቦረል በዛሬ ዕለት ባወጡት መግለጫ፤ በአማራ ክልል በተለይም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀበት ጊዜ አንስቶ ከፍተኛ የዜጎች እስራት እየተፈጸመ መሆኑን አንስተዋል።
ኅብረቱ የአፍሪካ ኅብረት፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምክክር ኮሚሽን ሲቪል ዜጎችን እንዲጠበቁ፣ ጦርነቱ እንዲቆም እና በግጭቱ አካላት መካከል ውይይት እንዲደረግ እንዲያበረቱ ጥሪ ማቅረቡን ጆሴፕ ቦረል ገልጸዋል።
የአውሮፓ ኅብረት በፖለቲካዊ እልባት ወደ ውይይት፣ እርቅ እና ሰላም የሚያመራውን ማንኛውንም ሂደት ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑንም ነው ያመላከቱት።
“በተለይም በመካሄድ ላይ ያለው አገራዊ የምክክር ሂደት፤ ለአገሪቱ የወደፊት ሰላም ተጨባጭ እና ዘላቂ መፍትሄ የሚያመጣ በመሆኑ ኹሉም ኢትዮጵያዊ የውይይት መንገዱን ሊከተል ይገባል።” ሲሉ ሃላፊው አሳስበዋል፡፡
ኅብረቱ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን እያከናወነው የሚገኘው ብሔራዊ ምክክር በውጤት እንዲጠናቀቅ የሰባት ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል፡፡



