የአዲስ አበባ ሆቴል ባለቤቶች ማኅበር ከባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር ጋር በመተባበር ለ5 ሺሕ ሰዎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር መድረክ ማዘጋጀቱን ገለፀ።
መድረኩ ከኅዳር 29 እስከ 30 በሚሊኒየም አዳራሽ የሚከናወን ሲሆን፣ በሆቴል እና ቱሪዝም ላይ የተሰማሩ ከ 200 በላይ ቀጣሪዎች እንደሚሳተፉበት ተገልጿል። ከእነዚህ ውስጥም 125 የሚሆኑት በአዲስ አበባ የሚገኙ ሆቴሎች ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ በክልሎች የሚገኙ ሆቴሎች እና የቱር ኦፕሬተሮች እንደሆኑ ማኅበሩ አስታውቋል።
በዝግጅቱ ላይ ከ10 ሺሕ በላይ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች እንደሚሳተፉበት የሚጠበቅ ሲሆን፣ የሥራ ማመልከቻ አፃፃፍ ዘዴዎችን እና የሥራ ቃለ ምልልስን የተመለከቱ ሥልጠናዎች በነፃ ይሰጣሉ ተብሏል። እንዲሁም ቀጣሪዎች ከሥራ ፈላጊዎች መሀል አወዳድረው የሚቀጥሩበት መንገድ መመቻቸቱ ተገልጿል።
በኢትዮጵያ የሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፍ እያደገ መምጣቱ የተገለፀ ሲሆን፣ በሠራተኞች ላይ የሚታየውን የሙያ ክፍተት ለመድፈን እና ሥራ ፈላጊ ወጣቶችን ከቀጣሪዎች ጋር ለማገናኘት እንደሚጠቅም የማኅበሩ ፕሬዝደንት ቢንያም አስራት ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በዘርፉ ላይ ስላሉ አንገብጋቢ ችግሮች የፓናል ውይይቶች ይደረጋሉ ያሉት ቢኒያም፣ ሆቴሎች ዓለም ዐቀፍ ልምዶች እና አሰራሮች ይለዋወጣሉ፣ የሥራ እና የገበያ ትስስርም ይፈጠርበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ የሚታየውን ሰፊ የሥራ አጥ ቁጥር በዘርፉ እንዲሳተፍ ለማድረግ እና በሥራ ፈላጊዎች እና ቀጣሪዎች መካከል የሚስተዋለውን አለመገናኘት ለማስቀረት እንደሚጠቅም ተገልጿል። ይህ መድረክ በአገራችን ለኹለተኛ ጊዜ የሚከናወን ሲሆን፣ በባለፈው ዓመት ዝግጅት 2 ሺሕ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሎ ነበር።
ቅጽ 2 ቁጥር 57 ኅዳር 27 2012


