በቀጣይ ቀናት በአብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ መኖሩን ተከትሎ በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳይደረስ ጥንቃቄ እንዲደረግ ማሳሰቢያ ተሰጠ።
በተለይም በአብዛኛው ምሥራቅ፣ ሰሜን ምሥራቅ፣ ደቡብ፣ በደቡብ ምዕራብ፣ በሰሜን ምዕራብ እንዲሁም መካከለኛው የአገሪቱ አከባቢዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር ስለሚጠበቅ ኅብረተሰቡ አስፈላጊውን የቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የግብርና ሚኒስቴር ብሔራዊ ሜትሮሎጂን ዋቢ በማድረግ አሳስቧል።
ይህንንም ተከትሎ ኅብረተሰቡ የደረሱ ሰብሎችን የመሰብሰቡን ሥራ ሁሉም አርሶ አደር እና አርብቶ አደር ማኅበረሰብ ትኩረት እንዲያደርግ ማሳሰቢያ የተሰጠ ሲሆን፣ የደረሱ ሰብሎችን በፍጥነት እንዲሰበስቡ ሚኒስቴሩ መልዕክት አስተላልፏል።
የተሰበሰቡትን ምርቶች እርጥበት በማያገኛቸው መልኩ ከመሬት ከፍ አድርጎ እንዲከመሩ እና ዝናብ የሚከላከል ነገር /ፕላስቲክ/ ማልበስ፣ እንዲሁም እርጥበት ያገኛቸው ሰብሎች ካሉ ደግሞ ለማድረቅ ምቹ ቦታ ላይ በመከመር በዝናብ ምክንያት የሚከሰትን የምርት ላይ ጉዳት በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ እንደሚገባ ተገልጿል።
እንዲሁም የጎርፍ እና የውሃ ሙላት ችግር ሊኖር ስለሚችል የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች ከወዲሁ ትኩረት እንዲያገኙ በማለት ጥብቅ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።
ቅጽ 2 ቁጥር 57 ኅዳር 27 2012



