ሰኞ፣ ኅዳር 29 የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን “ሕገ መንግሥታዊ ቃል ኪዳናችን ለዘላቂ ሰላም” በሚል መሪ ቃል ለ14ኛ ጊዜ በኦሮሚያ ክልል አስተባባሪነት አዲስ አበባ ላይ ተከብሮ/ታስቦ ይውላል። ኢትዮጵያ የብዙ ብሔሮች አገር እንደ መሆኗ መጠን ልዩነት በአንድነት አንድነትም እንዲሁ በልዩነት አስተሳስራ መጓዟ እንዲሁም ይህንንም ሕገ መንግሥታዊ እውቅና በመስጠት ቀን መድቦ እንዲከበር ማደረጉ አመክኗዊ ነው። ብሔር ብሔረሰቦች እርስ በርሳቸው እንዲተዋወቁ ከማድረግ ባሻገር የተጋመዱባትን ኢትዮጵያ ለማጠንከር ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደርጋል።
በእርግጥ በአሁኗ ኢትዮጵያ የብሔር ጥያቄ በከፊል እውቅና ቢሰጠውም ሙሉ ለሙሉ ተመልሷል ማለት ግን መሬት ላይ ያለው እውነት እንደመካድ ይቆጠራል። ዋለልኝ መኮንን በአደባባይ በ1962 ያነሳው የብሔር መብቶች መረጋገጥ አለበት ጥያቄ በአሁናዊው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ትልቁ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የልዩነት ብሎም የግጭትና የአገር ሉዓላዊነትን በመፈታተን ላይ የሚገኝ ለመሆኑ ብዙ አብነቶችን መጥቀስ ይቻላል።
ከሰሞኑ የተከሰቱትን እንደ ምሳሌ ብንገልጽ፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል በሚገኙ ዩኒቨርሲተዎች፣ በድሬዳዋ፣ በባሌ እንዲሁም ትንሽ ቀደም ብሎ ደግሞ በተለያዩ የኦሮሚያ ክፍሎች፣ በአማራ ክልል፣ በደቡብ በዋናነት እንዲሁም በሌሎች ክልሎችም ጭምር ከማንነት ጋር በተያያዘ በተነሱ ግጭቶች ክቡር የሰው ልጆች ሕይወት ጠፍቷል፤ የአካል ጉዳት ደርሷል፤ ንብረትም ወድሟል። ከሳምንት በፊት ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የተከሰተውን እጅግ አሳዛኝ ግድያና ማንነትን ማዕከል ባደረገ ግጭት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለግድያ፣ ለአካል ጉዳትና ለሥነ ልቦና መረበሽ መዳረጉ ብዙዎችን ያሳዘነ ክስተት ሆኖ አልፏል።
ዜጎች ማንነትን (ማለትም ፆታ፣ የቆዳ ቀለም፣ ቋንቋ እና/ወይም ባሕል፣ ሃይማኖት፣ ማኅበራዊ አመጣጥን፣ ውልደትን፣ የፖለቲካ አመለካከትን ወይም ሌላ መለያን) መሠረት ካደረገ ማናቸውም ዓይነት ጥቃት፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም አስተዳደራዊ መገለል ወይም በደል ሊፈፀምባቸው አይገባም። ይህም መብት ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው የሰብኣዊ መብት ድንጋጌዎች – በተባበሩት መንግሥታት የሰብኣዊ መብቶች ድንጋጌ፣ የአፍሪካ የሰብኣዊ እና ሕዝቦች መብቶች ቻርተር – እንዲሁም በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ጥበቃ እንደሚደረግለት የተወሰነ ነው።
አሁንም ግን በሚያሳዝን ሁኔታ በማንነታቸው ምክንያት በተለያዩ መንገዶች መገለል እና መድልዖ እየተደረገባቸው እንደሆነ የሚሰማቸው ዜጎች አሉ። ይሁንና የማንነት ጥያቄዎች ሲነሱ በአንድ በኩል አፈና ይደርስባቸዋል። በሌላ በኩል የፖለቲካ ልኂቃን ከሚገባው በላይ ለጥጠውት የግጭት መንስዔ ከማድረግም ባሻገር፣ የማይታረቁ ልዩነቶች እያስመሰሉ ግጭቶቹን ያጋግሉታል።
የማንነት ጥያቄዎችን በቀናነት ማስተናገድ እና ዴሞክራሲያዊ መፍትሔ ማፈላለግ ኹለት ጠቀሜታዎች አሉት። አንደኛው በማናቸውም ሁኔታ መገሰስ የሌለባቸውን የሰብኣዊ መብቶችን ማክበር ሲሆን፣ በሌላ በኩል የኢትዮጵያን ውስጣዊ ችግሮች ለዘለቄታው መፍትሔ መስጠት ይሆናል።
የፖለቲካ ልኂቃን በኢትዮጵያ ያሉትን የማንነት ጥያቄዎች የሚበይኑበት ምልከታ በራሱ ችግር እየፈጠረ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ታምናለች። ልኂቃኑ የማንነትን ብያኔ የገዢ እና ተገዢ፣ የጨቋኝ እና ተጨቋኝ፣ የበላይ እና የበታች፣ የተጠቃሚ እና የተበዝባዥ፣ የበይ እና የበይ ተመልካች ኹለትዮሽ ግንኙነት ብቻ ወደ መፍትሔው በመቅረብ ፈንታ የችግሩን ትክክለኛ ምንጭ ለመረዳት በሚያስቸግር መልኩ መፍትሔውም እንዳይገኝ እንቅፋት እየሆነ ነው።
ችግሩን በተሳሳተ መንገድ መበየን መፍትሔውንም በተሳሳተ መንገድ ለመበየን ዳርጓል። ብዙ የፖለቲካ ልኂቃን ብሔርተኝነትን ለማንነት ጥያቄዎች ብቸኛው መልስ ማግኛ መፍትሔ በማድረግ “የእኛ” እና “የእነሱ” የሚል ክፍፍል በማበረታታት እና የቂም በቀል ተረኮችን በማግነን ቅራኔዎችን እያባባሱ ይገኛሉ።
በተጨማሪም በኢትዮጵያ የሥልጣን መሠረቱ የዘውግ ማንነት መሆኑ በአንድ በኩል፣ የተለያዩ ክልሎች ሕገ መንግሥታት የክልል “መሥራች” የሚሏቸው የተወሰኑ የዘውግ አባላትን ብቻ መሆኑ በሌላ በኩል ይህንን “የእኛ” እና “የእነርሱ” ቅራኔ ከማባባሱም ባሻገር፣ የሌሎች ዜጎችን ተዘዋውሮ የመሥራት እና የመኖር ሰብኣዊ መብቶች እንዳይከበሩ እንዲሁም የመምረጥ እና የመመረጥ ብሎም እኩል የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ባለማስገኘቱ የልዩነት እና የግጭት መንስዔ እየሆነ ነው። በዚህም ምክንያት እያንዳንዱ የማንነት ቡድን የራሱን ዞን፣ ክልል ወይም አስተዳደር ወሰን በማግኘት የተጠቃሚነት አድማሱን ማስፋት እንዲፈልግ ሆኗል። ይህም የምጣኔ ሀብት ጥያቄዎችን የማንነት መልክ እንዲሰጡ ሰበብ ሆኗል።
ኢትዮጵያን ከዚህ ፈታኝ ሁኔታ ለማውጣት እና ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት ለጥቃት እና መድልዖ ተጋላጭ የማይሆኑበትን ስርዓት ለመዘርጋት የመጀመሪያው እርምጃ የፖለቲካዊም ይሁን የምጣኔ ሀብት ተጠቃሚነት በተለይም ዜጎች በምርጫቸው በማይወስኑት ነገር ግን በደም ቆጠራ በሚገኝ የማንነት ብያኔ እንዳይኖር እና ሕጋዊ ከለላ እንዲደረግለት ማድረግ ነው። በመቀጠልም ሕዝባዊ ተሳትፎን ያረጋገጠ ዘላቂ ዴሞክራሲያዊ መፍትሔን ተፈፃሚ ማድረግ ያስፈልጋል።ኢትዮጵያ የተለያዩ ስርዓተ መንግሥታትን በተለያየ አስተዳደራዊ መዋቅሮች እና በተለያየ የተፅዕኖ አድማስ ውስጥ ማለፏን የታሪክ መዛግብት እና አርኪዮሎጂያዊ መረጃዎች ያመለክታሉ።
በረጅሙ የኢትዮጵያ የታሪክ ጉዞ ውስጥ የውጪ ወራሪ ኃይልን ለጋራ ደኅንነትና ለአገር ሉዓላዊነት ለመመከት ሲባል ብዙ ኢትዮጵያውያን መስዋዕትነት ከፍለውበታል። አገራዊ ሉዓላዊነትን ከውጭ ጠላት በመከላከል ላይ ያለንን ቁርጠኝነት ያክል ግን የእርስ በእርስ ግንኙነታችን ላይ አይንፀባረቅም።
ይልቁንም፣ ለንግሥና እና ለበላይነት በተደረጉ ቀደምት ትግሎች የተፈፀሙ በደሎች እና መድሎዎች እንዲሁም የተዛቡ ግንኙነቶች ላይ በመመሥረት እና እነዚህን ታሪካዊ ቁርሾዎች በመቆስቆስ ዛሬም ድረስ የፖለቲካ ዓላማ ለማስፈፀሚያነት ማዋል የተለመደ ነገር ግን መራር የፖለቲካችን ነባራዊ ሁኔታ ሆኗል። አዲስ ማለዳም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እዚህም እዚያም እያገረሹ ያሉት ማንነትን መሠረት ያደረጉ አቤቱታዎች ወይም ሽፋን ያደረጉ ግጭቶች ለዚህ ሁነኛ ማሳያዎች ናቸው ብላ ታምናለች።
እናም ባለንብት ጊዜ እድገትና ለውጥ ለማምጣት ብሎም፣ ሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቱ ተሟልቶና ደኅንነቱ ተጠብቆ እንዲኖር፣ አገርም ለተረካቢ ትውልድ በሰላም ትተላለፍ ዘንድ ዴሞክራሲያዊ መንገዶች ሊመረጡ ይገባል። ለብሔር ጥያቄም እስከ አሁን ሲሰጥ ከቆየው በቂና አጥጋቢ ውጤት ካላስገኘ መልስ ባሻገር ዴሞክራሲያዊ የሆነ መልስ ሊሰጥ ይገባል ስትል አዲስ ማለዳ አጽንኦት ትሰጣለች።
ቅጽ 2 ቁጥር 57 ኅዳር 27 2012


