የበረሃ አንበጣ ኢትዮጵያን እንደሚያሰጋት ተገለፀ

0
544

አደገኛ የበረሃ አንበጣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የምሥራቅ አፍሪካ አገራትን እንደሚያሰጋ ዓለም ዐቀፉ የምግብ ድርጅት ገለፀ።
በምሥራቅ ኢትዮጵያ እና በሶማሊያ አካባቢዎች የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመቆጣጠር በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ቢሆንም፣ በያዝነው ወር አጋማሽ በምሥራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች፣ በሶማሊያ፣ ኬኒያ እና ኤርትራ በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት ሊያደርሱ እንደሚችሉ ተገልጿል።
በአካባቢው አዲስ የተፈለፈሉ አንበጣዎች ወደ ኬኒያ እና ደቡባዊ ክፍሎች ሊሰራጩ ይችላሉ የሚለው የተቋሙ ዘገባ፣ ባለፉት ሳምንታት በአካባቢው የጣለው ዝናብ የአንበጣዎቹን እንቅስቃሴ እንደገደበው እና እስከዚህ ወር መጨረሻም ቀድመው በተጠቁት አፋር እና ድሬዳዋ ላይ እንደ አዲስ ሊፈለፈሉ እንደሚችሉ አሳስቧል። የአንበጣ መንጋው ቀድሞ በተከሰተባቸው በድሬዳዋ አካባቢዎች እንደ አዲስ በመፈልፈል ወደ ሰሜናዊ የኤርትራ ክፍል እና ጂቡቲ ሊዛመት እንደሚችልም ተገልጿል።
ዓለም ዐቀፉ የምግብ ድርጅት በያዝነው ዓመት በኢትዮጵያ ከስምንት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለከፍተኛ የምግብ እጥረት ሊጋለጡ እንደሚችሉ መግለፁ የሚታወስ ሲሆን፣ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በሰብሎች ላይ ያደረሰው ጉዳት እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ ግጭቶች በግብርና ሥራ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ እንዳሳደሩ ጠቅሷል።
ይህንን ተከትሎ ከ 8 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ የሆኑ ዜጎች ለከፍተኛ የምግብ እጥረት ሊዳረጉ የሚችሉ በመሆኑ አፋጣኝ እርምጃዎች መወሰድ እንደሚገባቸው ገልጿል።
ከምሥረቅ አፍሪካ በተጨማሪ፣ እንደ ሳውዲ አረቢያ፣ ኢራን እና ፓኪስታን ያሉ የመካከለኛው ምሥራቅ እና የአካባቢው አስር አገራት ተመሳሳይ የበረሃ አንበጣ ስጋት ስላለባቸው ተገቢው የቁጥጥር ሥራ እንዲሠራ ድርጅቱ አሳስቧል።

ቅጽ 2 ቁጥር 59 ታኅሣሥ 11 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here