የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ያለግባብ የተመዘበረ 50 ሚሊዮን ብር አስመለሰ

0
635

ከጸረ ሙስና ትግሉ ጋር ተያይዞ በተሠሩ ሥራዎች ያለ አግባብ በሙስና ወንጀል በተመዘበሩ ሀብቶች ላይ ምርመራ መደረጉ የተገለፀ ሲሆን፣ ይህንንም ተከትሎ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ባለፉት አምስት ወራት ያለ አግባብ የተመዘበረ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ማስመለስ መቻሉን አስታወቀ።
ባለፉት አምስት ወራት ያለ አግባብ የተመዘበረ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት ወደ መንግሥት ካዝና በጥሬ ገንዘብ ማስመለስ መቻሉን ጠቅሰው፣ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ዝናቡ ቱኑ ተናግረዋል።
ከአገር የሚሸሹ ሀብቶችን ለማስመለስም የሀብት ማስመለስ ስትራቴጂ ተዘጋጅቷል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ሀብቱ የሸበባቸውን አገራት የመለየት ሥራ መሠራቱን አንስተዋል። ከእነዚህ ገንዘብ ከሚሸሽባቸው አገራት ጋር ድርድር መጀመሩን የገለፁት ዝናቡ፣ ጉዳዩን ምስጢራዊ ለማድረግ የአገራቱን ሥም ከመዘርዘር ተቆጥበዋል።
ከሕግ ማሻሻያ አፈጻጸም ጋር በተያያዘ የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የሚወጣው አዋጅ፣ የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ፣ እንዲሁም የፌዴራል የአስተዳደር ስነ ስርአት አዋጅ በቅርቡ ጸድቀው ወደ ሥራ እንዲገቡ እየተሠራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በተለይም የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የሚወጣው አዋጅ ምርጫን ተከትሎ የሚኖሩ ቀውሶችን ለመከላከል እንደሚያግዝ በመታመኑ በአስቸኳይ ጸድቆ ወደ ሥራ እንደሚገባ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
በተያያዘም ካለፈው መስከረም ወር ጀምሮ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ እንዲሁም በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በተለያዩ ዞኖችና ከተሞች የተፈጸሙ ወንጀሎችን የሚያጣራ የምርመራ ቡድን ተቋቁሞ የምርመራ ሥራ መካሔዱን አንስተዋል። አክለውም በኦሮሚያ ክልል ባለፈው ጥቅምት ወር ከተፈጠረው ብጥብጥ ጋር በተያያዘ እስከ አሁን 250 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ብለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 59 ታኅሣሥ 11 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here