የፌዴራል የግዢ እና ንብረት ማስወገጃ አገልግሎት በግብርና ሚኒስቴር በኩል በተያዘዉ የበጀት ዓመት ለሴፍቲ ኔት የሚዉል 75 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ግዢ ለማከናወን ባሳለፍነዉ ሳምንት ረቡዕ ታኅሳስ 8/2012 ጨረታ ከፈተ።
የፌዴራል የግዢ እና ንብረት ማስወገጃ አገልግሎት ባወጣዉ ጨረታ ላይ እንደሚያሳየዉ፣ በኮምቦልቻ 24 ሺሕ 500 ሜትሪክ ቶን፤ በድሬዳዋ 28 ሺሕ ሜትሪክ ቶን እና በአዳማ 22 ሺሕ 500 ሜትሪክ ቶን፤ በአጠቃላይ የ75 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በኮታና በቦታ በመከፋፈል ለሴፍቲ ኔት ግዢ እንደሚፈፅም ተገልጿል።
‹ፕሮሚሲንግ› የተሰኘ የስንዴ አቅራቢ ድርጅት ጨረታዉ ላይ በቦታ እና በኮታ በሦስት ተከፍሎ በቀረበዉ በኹለቱ ኮታ 52 ሺሕ 500 ሜትሪክ ቶን በ17 ሚሊዮን ዶላር በዝቅተኛ ዋጋ አቅርቧል።
የጨረታዉን ሰነድ ከወሰዱ 16 ድርጅቶች መካከል ተሳታፊ የሆኑት ሦስት ሲሆኑ፣ ፕሮሚሲንግ ኢንተርናሽናል፤ ሃካም አግሮ እና ጌም-ኮርፕ ናቸዉ። የጨረታዉ ማስያዢያ 260 ሺሕ የአሜሪካን ዶላር ነው። ጌም ኮርፕ ጨረታዉ ባወጣዉ መሠረት በኮታና በቦታ በሦስት ተከፍሎ በቀረበዉ በኹለቱ ኮታ 52 ሺሕ 500 ሜትሪክ ቶን በ18 ሚሊዮን ዶላር በከፍተኛ ዋጋ አቅርቧል።
ኢትዮጵያ በዓመት 4.5 በዓመት 4.6 ሚሊዮን ቶን የስንዴ ምርት በማምረት ላይ ብትገኝም፣ የአገር ውስጥ ፍላጎት ማሟላት ባለመቻሏ ሚሊዮን ዶላሮችን በማውጣት ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ላይ ትገኛለች።
መንግሥት የግብርናውን ዘርፍ ለማሻሻል በርካታ ለውጦችን በማድረግ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ግብርናውን ለማዘመን እና አርሶ አደሮች የተሻለ ገቢ ከግብርናው ማግኘት እንዲችሉ ለማድረግ የሚያስችል አካታች የሆነ በዘለቄታዊነት ችግሮችን የሚቀርፍ አሠራር ተግባራዊ ለማድረግ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ሲገልፅ ቆይቷል።
ቅጽ 2 ቁጥር 59 ታኅሣሥ 11 2012



