የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሠረታዊ የሠራተኛ ማኅበር አመራሮችን በማንሳት እና ዕድገት በመስጠት ማኅበሩን ለማዳከም እየሠራ መሆኑ ተገለፀ።
የማኅበሩን ፕሬዝዳንት ጨምሮ ሌሎች ሦስት የሥራ አስፈፃሚ አባላት የሥራ ዕድገት እንዲያገኙ የተደረገ ሲሆን፣ በአንድ ጊዜ ከማኅበሩ ነባር አራት አባላት ባልተለመደ መልኩ ያለ ውድድር ዕድገቱን እንዲያገኙ መደረጉ ማኅበሩን በማዳከም አደጋ ላይ ሊጥለው እንደሚችል ተገልጿል።
ፕሬዝዳንቱን ጨምሮ የሥራ አስፈፃሚ አባላቱ ከ 2009 ጀምሮ ማኅበሩን ሲመሩ የቆዩ ሲሆን፣ በሠራተኛው በተደጋጋሚ ሲነሳ የነበረውን ደሞዝ እና ጥቅማ ጥቅም እንዲሁም በርካታ የመብት ጥያቄዎችን እስከ ፍርድ ቤት በመውሰድ ምላሽ እንዲያገኙ ያደረጉ እንደነበሩ ተጠቅሷል።
በተደጋጋሚም የሥራ እድገት ጥያቄው በባንኩ በኩል ሲቀርብላቸው የቆየ ሲሆን፣ ባሳለፍነው ሳምንት ፕሬዝዳንቱን ጨምሮ ሌሎች ሦስት የሥራ አስፈፃሚ አባላት የባንኩን ቅርንጫፎች ለማስተዳደር የሚያስችል የሥራ ዕድገት ማግኘታቸው፣ ባንኩ ማኅበሩን ለማዳከም ያደረገው እንደሆነ ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአዲስ ማለዳ ምንጮች ተናግረዋል።
በ 2009 ከመላው ኢትዮጵያ ከሚገኙ ዲስትሪክቶች ከተመረጡት ስድስት ሥራ አስፈፃሚዎች እና ሦስት የቁጥጥር አባላት መካከል በሥራ ዕድገት ምክንያት እንዲሁም በግል ችግር ከሥራ አስፈፃሚ የወጡትን ጨምሮ አሁን ሦስት ብቻ ቀርተዋል። አሁን ያሉትም ተደጋጋሚ የሥራ እድገት ጥያቄ በንግድ ባንኩ በኩል እየቀረበላቸው መሆኑን አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች።
ከነባር አመራሮቹም መካከል አሁን አራቱ በቀረበላቸው የሥራ እድገት ምክንያት ከማኅበሩ አመራርነት የተሰናበቱ ሲሆን፣ በተደጋጋሚ የሚመጡ እድገቶች አልፈዋቸዋል በሚል ምክንያት እድገት እንዲያገኙ ተደርጓል። በአንድ ጊዜም የዚህን ያህል ቁጥር ያለው ሥራ አስፈፃሚ እድገት ማግኘቱ ማኅበሩን ማዳከምን ዓላማው ያደረገ እንደሆነ ምንጮች ተናግረዋል።
በሥራ እድገት የለቀቁትን የሥራ አስፈፃሚ አባላትም ማኅበሩ አስቸኳይ ስብሰባ በመጥራት በተጠባባቂዎች የተካ ሲሆን፣ አሁን ማኅበሩን እየመሩ ላሉ አካላትም ተመመሳሳይ የሥራ እድገት ጥያቄ በማቅረብ ላይ ይገኛል።
በሠራተኛ ማኅበር የሥራ አስፈፃሚነት ውስጥ ያለ ሠራተኛ በአስተዳደር የሥራ መስኮች ላይ መሳተፉ አባሉን ወደ አሰሪነት መለወጡን ተከትሎ፣ በዚህ የሥራ እርከን እድገት የሥራ አስፈፃሚ አባሉ በራሱ ፈቃድ ካልተወዳደረ በስተቀር በተቋሙ ሊመደብ አይችልም።
ማኅበሩ የአምስት ዓመት ስትራቴጂያዊ እቅድ ለማዘጋጀት በመንቀሳቀስ ላይ የነበረ ሲሆን፣ ከባንኩ ጋር 13ኛ የኅብረት ስምምነት ለመፈራረም በወራት የሚቆጠር ጊዜ መቅረቱ ጉዳዩን በይበልጥ አሳሳቢ አድርጎታል።
በቀጣይ ሦስት ዓመታት የሠራተኞች ደሞዝ፣ የዓመት ፈቃድ እንዲሁም ሌሎች አዳዲስ ጥቅሞችን በማካተት በባንኩ እና በማኅበሩ በኩል የሚደረግ ድርድር፣ ከሦስት ወራት በፈት ቀድሞ መጀመር የነበረበት ሲሆን፣ በ2009 የተፈረመው የኅብርት ስምምነት በአዲስ ተተክቶ የፊታችን የካቲት ወር ላይ መጠናቀቅ እንዳለበት ከማኅበሩ ሞባይል መተግበሪያ ላይ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
በዚህ ወቅት ላይ አራት የማኅበሩ አመራሮች ከማኅበሩ መለየታቸው ማኅበሩን ሊጎዳው ይችላል የተባለ ሲሆን፣ አሁን በተተኩት አዳዲስ ሥራ አስፈፃሚ አባላትም ላይ ባንኩ ከፍተኛ ክትትል በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ምንጮች ገልጸዋል።
የተደረገው የደሞዝ ጭማሪም በአንዳንድ የሥራ መደቦች ላይ እስከ ኹለት እጥፍ የሚደርስ የገንዘብ ጭማሪ ቢያመጣም፣ በአንዳንድ የሥራ መስኮች ላይ በባንኩ የተደረገው የደረጃ ቅነሳ በንግድ ባንኩ ሠራተኞች ማኅበሩ ምንም እንዳላደረገላቸው በማንሳት፣ ደረጃ ቅነሳው በማኅበሩ የደሞዝ ጭማሪ ውትወታ የመጣ ነው በሚል ማኅበሩን እንዲቃወሙ አድርጓል።
ቅጽ 2 ቁጥር 60 ታኅሣሥ 18 2012



