በደንበኛቸው ላይ በወጣ የእስር ትእዛዝ የታሰሩት ጠበቃ ድብደባ ደረሰባቸው

0
647

በቡራዩ ከተማ አስተዳደር ወረዳ ፍርድ ቤት በሚገኝ የአሠሪ እና ሠራተኛ ክርክር ነገረ ፈጅ የሆኑት አብዲ አብርሃም፣ ደንበኛቸው አልፈፀሙትም በተባለ የአፈፃፀም መዝገብ ምክንያት ፍርድ ቤቱ ተከሳሽ እና ነገረ ፈጁ ይታሰሩ በሚል ባዘዘው መሰረት፣ ለሦስት ቀናት ታስረው በፖሊስም ራሳቸውን እስኪስቱ መደብደባቸውን ተናገሩ።

እነ ተፈሪ ከበደ በሚል ስድስት ሰዎች የተካተቱበት መዝገብ ያለ አግባብ ከሥራ መሰናበትን የሚመለከት ሲሆን፣ ሠራተኞቹ መባረራቸው ሕገ ወጥ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ በመግለፅ ድርጅቱ ለሠራተኞቹ የካሳ ክፍያ እንዲፈፀምላቸው ይወስናል። ከውሳኔውም በኋላ የአፈፃፀም መዝገብ ተከፍቶ የነበረ ሲሆን፣ ድርጅቱም የተጣለበትን የካሳ ክፍያ በመክፈል ጉዳዩን እንዲፈፅም ለታኅሳስ 10/2011 በፍርድ ቤቱ ቀጠሮ ይያዛል።

ነገረ ፈጁ አብዲ አብርሃም ጉዳዩን በማስመልከት ለአዲስ ማለዳ በሰጡት ማብራሪያ፣ በድርጅቱ ለይ የተሰጠውን ውሳኔ በቼክ ለመፈፀም ጥረት አድረገን ነበር ብለዋል። ሆኖም በዕለቱ ቼኩ ሊደርስ ባለመቻሉ በፍርድ ቤቱ ቀጠሮ ላይ መገኘት አለመቻላቸውን ገልፀዋል።

በእለቱም ዳኛው፣ መቅረታቸው የቅጣት ውሳኔውን ላለመፈፀም መፈለጋቸውን ያሳያል በማለት፣ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ወይም ነገረ ፈጅ ረቡዕ ታኅሳስ 15/2012 ተይዘው ይቅረቡ የሚል ትዕዛዝ አስተላልፈዋል ሲሉ ተናግረዋል።

‹‹ውሳኔው መተላለፉን አልሰማንም ነበር›› ያሉት ነገረ ፈጁ፣ ‹‹ሰኞ ታኅሳስ 13 ለሌላ ጉዳይ ክርክር እንዲሁም የድርጅቱ ላይ የተከፈተውን የአፈፃፀም መዝገብ ወሳኔውን በመፈፀም ለማጠናቀቅ በፍርድ ቤቱ በተገኘሁበት ወቅት ፖሊሶች በመምጣት የእስር ትዕዛዝ እንደወጣብኝ በመንገር ወደ ማረፊያ ቤት እንድሔድ ጠይቀውኛል›› ሲሉ ገልፀዋል።

በወቅቱም አብዲ ድርጅቱን በሕግ ጉዳዮች የሚወክሉ እንጂ ሥራ አስኪያጅ አለመሆናቸውን ጠቅሰው፣ በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ላይም የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ወይም ነገረ ፈጅ ይበል እንጂ በሥም የተጠቀሰ ነገር እንዳልነበረውም ይናገራሉ።

‹‹እንዲሁም የድርጅቱ ነገረ ፈጆች ሦስት ነን እንጂ እኔ ብቻ አይደለሁም በማለት ለፖሊሶች ላስረዳ ሞክሬ ነበር። ሆኖም ሊቀበሉኝ አልቻሉም። ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱኝ። ወደ ፖሊስ ጣቢያው ስሔድ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅም እዛው ተይዘው ነበር›› ሲሉ ጉዳዩን አብራርተዋል።

አክለውም ሥራ አስኪያጁ ከተያዘ የእሳቸው መያዝ የሕግ መሰረት እንደሌለው በመጥቀስ ለፖሊስ ጣቢያው ኀላፊ እንዲለቋቸው ወይም ፍርድ ቤት እንዲያቀርቧቸው ቢጠይቁም ‹‹ከቀጠሮ ቀን በፊት አናቀርብህም›› የሚል ምላሽ እንደደረሳቸው እና ለኹለት ቀናት በእስር ላይ እንደቆዩ ተናግረዋል።

ሦስት በሦስት የሆነ በጣም ጠባብ ማረፊያ ቤት ውስጥ መቆየታቸውን የሚናገሩት የሕግ ባለሞያው፣ በአንድ ክፍል ውስጥ ከ15 ያላነሱ ተጠርጣሪዎች አብረው መታሰራቸውንም ተናግረዋል። የተጠርጣሪዎች አያያዝ ላይ ከፍተኛ ችግር የነበረበት፣ መፀዳጃ ቤት ለመሔድ ፈቃድ እንኳን ለማግኘት አስቸጋሪ የሆነበት እንደነበር ለአዲስ ማለዳ አብራርተዋል።

ረቡዕ ታኅሳስ 15 በቀጠሮው መሰረት ፍርድ ቤት የቀረቡት ጠበቃው እና ሥራ አስኪያጁ፣ ትእዛዙን መፈጸማቸውን ተከትሎ ዳኛው እንዲፈቱ ትእዛዝ አስተላልፈው ነበር። ሆኖም ፖሊስ ትእዛዙ በጽሑፍ ካልደረሰን አንለቀም የሚል ምላሽ ሰጥቷል። ፍርድ ቤቱም በወቅቱ መብራት ባለመኖሩ ‹‹በጽሑፍ ትዕዛዝ መስጠት አንችልም፤ ይለቅቅ›› የሚል ቀጥታ ትእዛዝ አስተላልፎ፣ ፖሊስም ትዕዛዙን ተቀብሎ ነበር ሲሉ ገልፀዋል።

‹‹ከችሎት ከወጣን በኋላ ወደ ፖሊስ ጣቢያ የጽፍ ትእዛዙ እስኪደርስ ወደ ማረፊያ ቤት እንደሚወስዱኝ ገለፁልኝ። እኔም እንድለቀቅ መወሰኑን በመግለፅ ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንደማልሔድ ብገልጽም ድብደባ እና መንገላታት ፈፅመውብኛል›› ብለዋል። አክለውም ጭንቅላታቸው ላይ በመመታታቸው መንገድ ላይ ራሳቸውን ስተው ለተወሰነ ሰዓታት መቆየታቸውን እና ሲነቁም ራሳቸውን ፖሊስ ጣቢያ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

ፖሊስ ጣቢያ ከሔዱ በኋላም ፍርድ ቤት ለመቅረብ ቢጠይቁም አንድ የደንብ ልብስ የለበሱ ፖሊስ ‹‹የፍርድ ቤት ትእዛዝ እንዳይፈፅም ከልክለሃል፣ በፖሊስ ላይ ፀብ አስነስተሃል፣ እንዲሁም እጅ በመጠላለፍ በመጠርጠርህ ማረፊያ ቤት ትቆያለህ›› እንዳሏቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ‹‹የእምነት ክህደት ቃሌን ተቀብለው ነበር። በዚህ መሃል የፍቺ ትእዛዝ በጽሑፍ ቢመጣም ተጠርጣሪ በመሆንህ እንለቅህም የሚል ምላሽ ተሰጥቶኛል›› ብለዋል።

ወደ ፍርድ ቤቱ ለመቅረብ እና የዋስትና መብት ጥያቄ ለፖሊስ ጣቢያው ያቀረቡ ሲሆን፣ ይህ ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱን ቢነግሯቸውም፣ ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ ግን ዳኛው ክስ እንደተመሰረተባቸው ገልጸው የዋስትና ጥያቄ ግን እንዳልቀረበ መስማታቸውን ገልጸዋል።

‹‹ፍርድ ቤቱም በማረፊያ ቤት እንድቆይ ወስኖ ለሐሙስ ታኅሳስ 13 ቀጠሮ በመያዝ ያቀረበኝ ሲሆን፣ ፖሊስ የፍርድ ቤትን ትእዛዝ የሚያስፈፅም ፖሊስን ደብድበሃል እንዲሁም ጥቃት ፈፅመሃል የሚል ክስ ተመስርቶብኛል። የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ በእለቱ አቅርቤ ጉዳዩን ለማየት ለታኅሳስ 20/2012 ቀጠሮ ተይዞ በእለቱ ከእስር ተፈትቻለሁ›› ሲሉ ተናግረዋል።

ድርጊቱ መብቶቻቸውን የሚጋፋ መሆኑን ያነሱት ጠበቃው፣ በፖሊስ በኩል ያለው የእስረኛ አያያዝም ሆነ የሕግ አረዳድ ከፍተኛ ችግር ያለበት ነው። በመሆኑ በቀጣይ ጉዳዩን በመያዝ የሚመለከታቸውን አካለት የመጠየቅ ሐሳብ እንዳለቸው ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት በበኩላቸው፣ ስለጉዳዩ የሰሙት መረጃ እንደሌለ እና ድርጊቱ ተፈፅሞም ከሆነ ጠበቃው ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱም ሆነ ለሌሎች ለሚመለከታቸው አካላት ማመልከት እንደሚችሉ ተናግረዋል። በኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተቋቋሙት አዳዲስ የኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬቶች፣ ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወይም ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዳኞች የተፈፀመ ጥፋት ካለ ማመልከት እንደሚችሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ጠበቆች ማኅበር ፕሬዘደንት ደበበ ኃይለገብርኤል በበኩላቸው፣ ጠበቃ ችሎቱን በንግግር ካልደፈረ፣ ዳኞችን አላስፈላጊ ንግግር ካልተናገረ በስተቀር ከፍርድ መፈፀም እና አለመፈፀም ጋር በተያያዘ የእስር እርምጃ ሊወሰድበት አይችልም ብለዋል። ‹‹እንደዚህ አይነት አጋጣሚዎች በብዛት አይታዩም፤ ጠበቃ በዚህ ምክንያት ሲታሰር አይተን አናውቅም›› ብለዋል።

እስከ አሁን ጉዳዩ እኛ ጋር አልደረሰም ያሉ ሲሆን፣ ጉዳዩ ከሕግ አግባብ ውጪ ከሆነ እንዲፈታ ለማድረግ የክልሉን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አልያም ፌዴራል ዐቃቤ ሕግ በማቅረብ እንዲታይ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 60 ታኅሣሥ 18 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here