ፖሊስ ለሕግ ይገዛ !

0
818

በተለያዩ ጊዜያት የሕዝብ መነጋገሪያ የሆኑ በፖሊሶች የተፈፀሙ የመብት ጥሰቶች እና ጭካኔዎች ቢኖሩም አጥፊዎች ግን ሕግ ፊት ቀርበው ቅጣታቸውን ሲቀበሉ አይሰማም። በዚህ [ታኅሳስ 18/2012] የአዲስ ማለዳ ዕትም ያካተትናቸው ኹለት የፖሊስ የመብት ጥሰት ዜናዎች እንደሚያሳዩት፣ በፖሊሶች ተገድለዋል የተባሉ ግለሰቦችን አስመልክቶ ፖሊስ ለቤተሰቦቻቸው መልስ እና የሕክምና ሪፖርት አልሰጠም። እንዲሁም ወንጀሎቹ ከተፈፀሙ ስድስት ወራት ቢቆጠሩም፤ እስከ አሁን ተጠርጣሪዎቹ ፖሊሶች አልተከሰሱም።

በአገራችን ፖሊስ ሰዎችን ሲመታ ማየት የተለየ አጋጣሚ አይደለም። በዱላ፣ በእርግጫና በጥፊ በፖሊስ ተመትቶ የሚያውቀውን ሰው ቤቱ ይቁጠረው። እንኳን በወንጀል የተጠረጠረ፣ አንዳች ትዕይንት ለማየት የታደመ ሰው ከተመደበለት ቦታ እንዳያልፍ ለማድረግ እንኳን የአገራችን ፖሊሶች የሚጠቀሙበት ዋነኛው ስልት ድብደባ ነው። እንዲያውም ከመልሶች ሁሉ ፖሊሶችን የሚያናድዳቸው «መብቴ ነው» እና «መማታት አትችልም» የሚሉት እንደሆኑ ይህን ርዕሰ አንቀጽ በማዘጋጀት ሒደት ውስጥ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ሰዎች ገልፀዋል።

ከዚህ ዘለል ሲል፣ የፖሊስ ጭካኔ በዜናው ላይ እንደተጠቀሰው ግድያ ድረስ የሚደርስ ቢሆንም ከዚያ በታች ያሉትን ለምሳሌ ሳያጠፉ ወይም ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ሰዎችን ማሰር፣ ማስፈራራት፣ የቃላት ጥቃት፣ ወሲባዊ ጥቃት፣ የፖሊስ ሙስና፣ የብሔር መድሎ እና ፖለቲካዊ ጭቆናንም የሚያካትት ነው።

«ፖሊስ እና ሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ» የተሰኘ ጥናት እንደሚያሳየው፣ መንግሥት ካሉበት ሦስት የሰብዓዊ መብቶች ኃላፊነቶች ውስጥ ፖሊስ ኹለቱ ይመለከቱታል። ሦስቱ የመንግሥት ኃላፊነቶች ሰብዓዊ መብቶችን ማክበር፣ መጠበቅ እና ማሟላት ናቸው። የመጀመሪያዎቹ ኹለት ኃላፊነቶች ፖሊስንም የሚመለከቱ ናቸው።
እንደ ጥናቱ ትንታኔ ሰብዓዊ መብትን ማክበር የሚለው ሐሳብ፣ ተጠቂ ፍትሕ እንዲያገኝ ማድረግንና ተጠርጣሪን ሰብዓዊ መብቶቹ ሳይጣሱ ሕግ ፊት ማቅረብን የሚያካትት ነው። ‹መጠበቅ› የሚለው ሐሳብ ደግሞ የማኅበረሰብ አባል የሆነ አንድ ግለሰብ ወይም ቡድን በሌላ ግለሰብ ወይም ቡድን ምንም ዓይነት የመብት ጥሰት እንዳይደረግበት ወይም እንዳይደረግባቸው ከለላ መስጠትን ይመለከታል።

ከላይ የተጠቀሰው ጥናት ፖሊሶች ተጠቂዎችን እና ተጠርጣሪዎችን ሲይዙ ሊከተሉት ስለሚገባው ሒደት በፌዴራል የሕግ ማዕቀፍ ውስጥ በግልጽ ያለመቀመጡ ችግር እንደሆነ ይገልጻል። ከዚህም በተጨማሪ ፖሊሶች ላደረሱት የመብት ጥሰት ኃላፊነት የሚወስዱበት እና ተጠያቂ የሚሆኑበት አጋጣሚ በጣም አናሳ መሆኑን ጥናቱ ደምድሞ፣ ሒደቱም ጥቃት ለደረሰባቸው ግለሰቦችና ቡድኖች በጣም ፈታኝ እንደሆነ ይጠቁማል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ስሜነህ ኪሮስ፣ የኃይል አጠቃቀምን ለመወሰን አዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰው ችግሩ የሕግ ክፍተት አይደለም ይላሉ። እንደ እርሳቸው አባባል ችግሩ አተገባበር ላይ በመሆኑ አዲሱ አዋጅ ከወጣ በኋላም የሚፈለገውን ያህል ለውጥ ላይመጣ ይችላል። የመጀመሪያው የፌዴራል ፖሊስ ማቋቋሚያ አዋጅ ሲወጣ ጠንከር ያለ ነበር ያሉት ስሜነህ፣ በተተገበረባቸው ዓመታት የነበሩ የሕዝብ ቁጣዎችን ለማብረድ በተደረገው ጥረት ሕጉ መጥበቁ ስለታመነበት በማሻሻያ እንዲላላ ተድርጓል ብለዋል።

መንግሥት ፖሊስ በሕዝብ እና በእርሱ መካከል ያለ ሕግ አስከባሪ ገለልተኛ ኃይል እንዲሆን ሳይሆን ሕዝብን ለመጫን የሚያገለግል ተቋም እንዲሆን አድርጎ ሲጠቀምበት ስለቆየ፣ ፖሊስ የሕግ የማስፈፀም ኃላፊነቱን ሳይሆን የፖለቲካ አካል ሆኗል ይላሉ ስሜነህ። በመሆኑም የኃይል አጠቃቀም አዋጁ መውጣት የመንግሥትን ዝንባሌ ላይቀይረው ስለሚችል ችግሩ በቀጣይነትም ሊታይ የሚችልበት ሰፊ አጋጣሚ እንዳለ ጠቅሰዋል።

ሌላ የመብት ጥሰት ያደረሱ ፖሊሶች በኢትዮጵያ ተጠያቂ እንዳይሆኑ የሚያደርጋቸው ችግር ብለው ስሜነህ ያነሱት ነጥብ የጥቃቱ ሰለባዎች ፖሊስን ፖሊስ ጋር የሚከሱ መሆኑ ነው። እንደ እርሳቸው አባባል፣ ፖሊስ ስለ አባሉ ጥሰት መረጃ መሰብሰቡ እና ምርመራ ማድረጉ ጉዳዩን ለማደባበስ የሚረዳ በመሆኑ ፖሊስ ሲከሰስ እነዚህ ተግባራት በቀጣይነት ወደ ዐቃቤ ሕግ መሸጋገር አለባቸው። ይህም የፖሊሶችን ክስ ሌላ አካል እንዲመረምር እድል በመክፈት ተጠያቂነታቸውን ሊጨምረው እንደሚችል ስሜነህ ያምናሉ።

የእንባ ጠባቂ እና ሰብዓዊ መብት አካላት፣ ሌሎች የመብት ጥሰት የሚመለከታቸው አካላት በመሆናቸው ፖሊሶች ሰብዓዊ መብቶችን በሚጥሱበት ጊዜ ያለባቸውን ኃላፊነት መወጣት አለባቸው ብለዋል፤ ስሜነህ። ከዚህ በተጨማሪ መንግሥትን ተጠያቂ የማድረግ ባህል በአገራችን ስለሌለ ይህንንም ለመገንባት መሥራት ያስፈልጋል ሲሉ ያስረዳሉ።
ከላይ እንደተጠቀሰው ፖሊስ ግለሰብ ወይም ቡድን ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲያደርግ መብቶቹን የማክበር እና የመጠበቅ ኃላፊነቶቹን እየጣሰ ነው። ቀደም ብለን በጠቀስነው ዜና ላይ ያለው በፖሊሶች ተፈፀመ የተባለው ግድያ፣ ፖሊስ ሰብዓዊ መብቶችን የማክበር ኃላፊነቱን ቸል ብሎ ውድ የሆነውን የሰው ሕይወት ቢያጠፋ እንኳን ምንም ዓይነት ተጠያቂነት እንደማይጠብቀው የሚያሳይ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ በቅርብ ጊዜ በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች የሚታየው የተማሪዎች ግድያን፣ የአካል ጉዳትን እና ሌሎችንም የመብት ጥሰቶችን ፖሊስ የማስቀረት ኃላፊነት አለበት። የፖሊስ ሰብዓዊ መብቶችን የመጠበቅ ኃላፊነት ዜጎች ላይ የሚደርስን ጉዳት መከላከልን ያካትታል። በዚህም ረገድ ፖሊስ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንዳልሆነ በየቀኑ በብሔር፣ ሃይማኖት፣ ፖለቲካዊ አቋም እና ሌሎችም ምክንያቶች በየቦታው በየዕለቱ የሚሰማው ወንጀል ማሳያ ነው።

አሁን አሁን ሕገ ወጥነት እየተንሰራፋ በመጣባት አገር ይህ የሚጠበቅ ቢሆንም፣ ፖሊስ ጠንከር ብሎ ኃላፊነቱን መወጣት ካልቻለ እና በአንዳንድ ዘገባዎች ላይ እንደሚታየው ይባስ ብሎ የችግሩ አካል በመሆን ለአንዱ ወገን ወግኖ ሌላውን የሚያጠቃ ከሆነ ችግሩን ከመፍታት ይልቅ እያባባሰው ነው የሚሔደው። ይህ ሁኔታ ደግሞ በዘላቂ መንገድ ኅብረተሰቡ ለፖሊስ ያለው ግምት እና አመኔታ ላይ ከፍተኛ ጥላ ያጠላል።

እንዲህ ያለው ኃላፊነት የጎደለው እንቅስቃሴ እንኳን ሳይጨመር ኅብረተሰቡ ፖሊስን ሲያይ ሊጠብቀኝ መጣ ከሚል ስሜት ይልቅ ስጋት ሲሰማው የቆየ ነው። ይህ የሆነበት ዋነኛው ምክንያት ደግሞ ሕዝቡ በእለት ተእለት እንቅስቃሴው የሚያየው መደበኛ የሆነ የፖሊስ መብት ጥሰት ነው። የሰውን ልጅ በጠራራ ፀሐይ ሕዝብ በተሰበሰበበት ገድሎ ከዚያ ለጥያቄ እንኳን የማይቀርብ ፖሊስ መኖሩ በኅብረተሰብ ውስጥ ያለውን የፖሊስ ጥላቻ የሚያንር ከመሆኑም በላይ ሌሎችም የፖሊስ አባላት ከሕግ በላይ እንደሆኑ እንዲሰማቸው የሚያደርግ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ስሜት ደግሞ ለበለጠ ጥፋት ጥሩ መነሻ የሚሆን ስንቅ ነው። በመሆኑም ድርጊቱን የፈፀሙት ፖሊሶችም ሆኑ ከመንግሥት ኃላፊዎች ውስጥ ትዕዛዙን ሰጥተው ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎች፣ በፍጥነት ለፍርድ እንዲቀርቡ አዲስ ማለዳ ጥሪ ታቀርባለች።

በዚህ ማጠፊያው ባጠረበት የግጭትና ክፍፍል ወቅት ነገሮችን ወደ ተሻለ መንገድ ለመመለስ ፍትሕን ከማረጋገጥ የበለጠ አዋጭ እና ትክክለኛ መንገድ የለም። የመንግሥት ተአማኒነትን ይበልጥ የሚሸረሽሩ እንደዚህ ዓይነት ተግባራትን ደግሞ ፖሊስ ራሱ ከማንም በፊት ሊዋጋው ይገባል። መደበኛ እየሆነ ከመጣው የራስን ወንጀለኛ የመሸሸግ አባዜ ክልሎችን ማላቀቅ ሲገባ፣ ይባስ ብሎ ይህንን ችግር ወደ ሕዝብ ተቋማት ማሻገር ይቅርታ የሚደረግለት ተግባር መሆን የለበትም። አሁን ያሉት ሁኔታዎች የሚያሳዩት ፖሊስ የሕዝብን መብት ከማክበርና መጠበቅ ይልቅ በተለያዩ የፖለቲካ ጉዳዮች ታስሮ መብትን እየጣሰ እንደሆነ ነው። በመሆኑም ይህ አካሔድ በፍጥነት ሊገታ እና ወደ ተገቢው መስመር ሊመለስ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 60 ታኅሣሥ 18 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here