በደቡብ ክልል ሃዲያ ዞን በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ ስርቆት ሲፈጽም እጅ ከፍንጅ የተያዘው ግለሰብ በአስር ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጣ።
ግለሰቡ ጥቅምት 17/2012 ከምሽቱ 2:00 አካባቢ በወላይታ ዲስትሪክት ሾኔ አገልግሎት መስጫ ማእከል አካባቢ በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ ስርቆት ሲፈፅም በኅብረተሰቡ ጥቆማና በጸጥታ ኃይሎች ትብብር መያዙን አገልግሎቱ አስታውቋል። በደቡብ ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሾኔ ምድብ ችሎት ታኅሳስ 20/2012 በዋለው ችሎትም፣ ግለሰቡ በአስር ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኗል።
ከዚህ ጋር በተያያዘም በሲዳማ ዞን ብላቴ ወረዳ ባሌላ ከተማ አካባቢ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ተገዝተው የተሠሩ ባለ 400 ኬቪ የከፍተኛ ኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ በተደረገ ተደጋጋሚ ስርቆት፣ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የኤሌክትሪክ መስመር ተሰርቋል።
በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ስርቆት ላይ ፖሊስ እና ኅብረተሰቡ በጋራ ባደረጉት እንቅስቃሴ፣ ተባባሪና ተረካቢ የሆኑ 24 ተጠርጣሪዎችን ከነ ሙሉ መረጃቸው ለፖሊስ በመስጠት፣ በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ላይ እየተፈፀመ የሚገኘውን ስርቆትና ውድመት ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ኅብረተሰቡ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ 2012 በጀት ዓመት ሦስት ወራት ብቻ በተለያዩ አካባቢዎች በኤሌክትሪክ መስመሮች እና ትራንስፎርመሮች ላይ በተፈፀመ ዝርፊያ፣ ከ 38 ሚሊዮን ብር በላይ መክሰሩን መግለፁ ይታወሳል።
ቅጽ 2 ቁጥር 62 ጥር 2 2012



