አርሶ አደሮች መሬታቸውን ለብድር የሚያስይዙበት አገልግሎት ተጀመረ

0
1127

አርሶ አደሩ ብድሩን ካልመለሰ መንግሥት እስከ 30 ዓመት ድረስ መሬቱን በማከራየት ብድሩን ያስመልሳል

የይዞታ ማረጋገጫ ላላቸው አርሶ አደሮች መሬታቸውን እንደ ማስያዣ በመጠቀም በአነስተኛ የፋይናስ ተቋማት አማካኝነት እስከ 100 ሺህ ብር ድረስ ብድር የመስጠት ሥራ በአማራ፣ ኦሮሚያና እና ደቡብ ክልሎች ላይ መተግበር ጀመረ።

በአነስተኛ የብድር እና የቁጠባ ተቋማቱ እስከ 100 ሺህ ብር ድረስ ብድር የሚቀርብ ሲሆን መንግሥት ብድሩ ካልተመለሰ እስከ 30 ዓመት ድረስ በማከራየት እዳውን ለመመለስ እንዲችል የሚፈቅድ የሕግ ማዕቀፍ መውጣቱን በግብርና ሚኒስቴር የገጠር መሬት አጠቃቀም ዳይሬክተር ካሳሁን ግርማ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

መንግሥት መሬታቸውን ወስዶ ብድሩ እስኪመለስ ለሌላኛው ወገን ከበዛ እስከ 30 ዓመት በሚደርስ በማከራየት ብድሩን የሚያስመልስበት አሰራርም አርሶ አደሩ ብድሩን ባለመክፈሉ ምክንያት መሬቱን እንዳያጣ ይረዳዋል ተብሎ መታሰቡን ገልጸዋል።

እስከ አሁን ለብድር አገልግሎቱ 500 ሚሊዮን ብር በላይ እንደዋለ ዳይሬክተሩ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በዚህም ከአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም ጋር ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ አገልግሎቱ በመጀመርያ በክልሉ ተተግብሮ በቅድሚያ በሁለት ወረዳዎች ላይ የሙከራ ሥራ መሠራቱን ኃላፊው ይገልፃሉ። ለመነሻም ከአምስት ሺህ አስከ 15 ሺህ ብር በማበደር የተጀመረ ሲሆን አሁን ውጤታማነቱን በመመልከት አንድ የመሬት ባለይዞታ ማረጋገጫ ያለው ሰው እስከ 100 ሺህ ብር መበደር የሚችልበት ሁኔታ መመቻቸቱን ገልጸዋል።

በየክልሉ ማይክሮ ፋይናንሶች ተመርጠው አገልግሎቱን ለገበሬው እንዲያቀርቡ መደረጉንም ገልጸዋል። ‹‹ይህ የብድር አገልግሎት ከተዘጋጀ በኋላ ለገበሬው የፋይናንስ አማራጭ በመስጠት ከፍተኛ ለውጥ ያመጣ ሲሆን ነገር ግን የሕግ ማዕቀፋቸውን ያሻሻሉት አማራ፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ ብቻ በመሆናቸው ለሌሎች ክልሎች ገበሬዎች አገልግሎቱን ማድረስ አልተቻለም›› ሲሉ ካሳሁን ገለጸዋል። ከእነዚህ ክልሎች መካከልም የትግራይ ክልል የገጠር መሬት ልማት አዋጁን አስኪያስተካከል በመዘግየቱ አስካሁን አገልግሎቱን መጠቀም አለመቻሉን ተናግረዋል። ካሳሁን እንደገለጹት ወደዚህ ሥራ ከመገባቱ በፊት በተለያዩ ክልሎች ዙርያ የግንዛቤ ማስጨበጫ የተሠራ ሲሆን አስከ አሁን በየክልሉ 126 ማይክሮ ፋይናንሶች ተሳታፊ ሲሆኑ በብድሩም 15ሺ የሚጠጉ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ሆነዋል።

የንብረት ሕግ ባለሞያ የሆኑት ደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) እንደሚሉት መሬትን እንደንብረት የመቁጠር እና እንዲህ ዓይነት አገልግሎት የመስጠት ተግባር መጀመር ካለበት ጊዜ የዘገየ ሲሆን ‹‹ፖለቲካው ላይ ብቻ ትኩረት በማድረጋችን ኢኮኖሚው ላይ መሠራት ያለበትን ጉዳይ ችላ ማለታችን ዋጋ አስከፍሎናል›› ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል። በተጨማሪም አርሶ አደሩ ከመሬቱ ያለውን ተጠቃሚነት ከፍ ለማድረግ እና በገንዘብ አቅም ማነስ ምክንያት የሚመጡበትን ችግሮች ለመቅረፍ እንዳይቻል የነበረው የመሬት ፖሊሲ ማነቆ ነበር ይላሉ።

‹‹ለምሳሌ አንድ ገበሬ ለመበደር ቢፈልግ ባንኮች ለማበደር ማስያዣ ይጠይቃሉ፤ ገበሬው ደሞ ሊኖረው የሚችለው የእርሻ መሬቱ ብቻ ነው›› ሲሉ ያብራራሉ። ይህም የገበሬውን ግብአት የመግዛት እና ሥራውንም የማዘመን ፍላጎቱን ገትቶታል ብለዋል። ነገር ግን የመሬቱ መጠን፣ ደረጃ እና የመሬቱ ለምነት ካልተለየ ይህ የብድር ሒደት ከሚያመጣው ጥቅም ይልቅ በአገር ላይ የሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ይበልጣል ሲሉም ስጋታቸውን ገልፀዋል። በተጨማሪም የፋይናንስ ተቋማቱ ቴክኒካዊ ሥልጠና በመስጠት ብድሩን ከማመቻቸት ጎን ለጎን አርሶ አደሩን ማብቃት ላይ ከፍተኛ ትኩረት ማድረግ ይኖርባቸዋልም ብለዋል። በኢትዮጲያ ከ50 ሚሊዮን በላይ ቁራሽ መሬቶች ሲኖሩ ከነዛ ውስጥ 15 ሚሊዮኑ ብቻ ነው የይዞታ ማረጋገጫ ያላቸው።

ቅጽ 2 ቁጥር 64 ጥር 16 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here