በኢትዮጵያ ውስጥ የዲጂታል ቴክኖሎጂ፤ በተለይም የሞባይል አገልግሎት መስፋፋትን ተከትሎ መንግሥት የግል መረጃዎችን መበርበሩ የተለመደ ተግባር ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም። ከ11 ዓመታት በፊት ፀድቆ ወደ ሥራ የገባው የፀረ ሽብር አዋጅ ደግሞ ለዚህ እንደ መልካም አጋጣሚ ሆኖ የዜጎች የግል መረጃዎችን እንደልብ ለማገላበጥ በር ከፍቶ ነበር። በሽብር ወንጀል ተከሰው ፍርድ ቤት የቀረቡ ተከሳሾችም በርግጥም የግል ንግግሮቻቸው ወይም የኢሜል ግንኙነቶቻቸው ተጠልፈው የሚቀርቡትን ያክል የሃሰት ማስረጃዎችም ይቀርቡ እንደነበር ያስታውሳሉ።
የሚቀርቡ የተጠለፉ የግል ልውውጦችን በፅሁፍ ገልብጦ ማቅረብ እንጂ የተደረገውን ልውውጥ በቀጥታ ለችሎቱ የማቅረብ ግዴታ ያለመኖሩ ሌላኛው ክፍተት ነበር። ታዲያ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር ወደ ሥልጣን መምጣቱን ተከትሎ የፀረ ሽብር አዋጁ መሰረታዊ የሚባሉ እና የግል ግንኙነቶችን ሚስጥራዊነት በሚጠብቅ መልኩ ተሻሽሏል። ታዲያ ከጥቂት ወራት በፊት የተገላቢጦሽ ሆኖ የመንግሥት ባለሥልጣናት የግል መረጃዎች ተበርብረው የአንድ ሰሞን የማህበራዊ ፍጆታ ሆነው ነበር። በዚህ ዙሪያ የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰጡ ቢቆዩም ሺዎች በመረጃው እውነትነት ተማምነው ሲቀባበሉት ሰንብተዋል። የዲጂታል መብቶች ተሟጋች የሆኑት ብርሃን ታዬ እንደሚሉት የዲጂታሉ ዓለም ልክ እንደ ብሮድካስት ወይም በመሬት ላይ እንዳለው የፖለቲካ መጫወቻ ሜዳ ለፖለቲካ ሽኩቻዎች የተጋለጠ ነው፡፡
ይሀም በተለያዩ የዲጂታሉ ዓለም በበለፀገባቸው አገራት ላይ ከዚህ ቀደም በተለያየ መልኩ የታየ እና አሁንም እያጋጠመ የሚገኝ ነውም ይላሉ። ‹‹ፖለቲከኞች ሚስጥሮቻቸውን በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን ወይም በተለያየ መልኩ በማጋራት አንዱ ሌላውን ለመጣል እንደሚሞክር ሁሉ በዲጂታሉ ዓለምም አንዱ ሌላውን ቢበረብር አይገርምም፤ ይህ ማለት ግን አግባብ ነው ማለት አይደለም›› ሲሉ ያብራራሉ። ‹‹በግሌ ግን ሁለት ነገሮች ያሳስቡኛል›› የሚሉት ብርሃን ‹‹የመጀመሪያው አሳሳቢ ነገር የመንግሥት ባለሥጣኖቻችን በቀላሉ ሊሰበር የሚችል የይለፍ ቃል እንዴት ሊኖራቸው ይችላል? ሲሆን ሌላው እንዴት የአገር ኃላፊነት ያለባቸው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የዲጂታል ደህንነታቸውን የሚጠብቁበት ልምድ ሊኖራቸው ይችላል›› የሚሉት ናቸው ይላሉ።
እንደ ባለሞያዋ ገለፃም ይህ የውስጥ ችግራችን ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ የውጪ ጠላቶች ተጠቂነትን የሚያሰፋ እና በሌለን ሃብት መሰረተ ልማቶቻችን ላይ ጉዳት የሚያደርስ ነው። በተለይ እስከ አሁን ድረስ በመንግሥት ባለሥልጣኖች ላይም ሆነ በዜጎች ላይ ለተፈፀሙ የብርበራ ወንጀሎች ተጠያቂ የሆነ አካል ያለመኖሩ ነገሩን የበለጠ አስጊ እንደሚያደረገው ይናገራሉ። ነገር ግን ይህ ጉዳት ደርሶብኛል ብሎ ያመለከተ አካል ስለመኖሩ ግለፅ ባይሆንም ያለመበርበር መብት አለኝ፣ የበረበረኝን አካል የመክሰስ መብት አለኝ ብሎ የሚያምን ዜጋ መፍጠር ላይ ገና ብዙ መሠራት እንዳለበት ባለሞያዋ ይናገራሉ። የአዲስ ማለዳ የኤዲቶሪያል ቡድን አባላት ይህ የዜጎችን ግንኙነቶች መበርበር እንደከዚህ ቀደሙ በመንግሥት የበላይነት ሳይሆን ማን ያድርገው ማን በማይታወቅበት ሁኔታ ከእለት ወደ እለት የመበራከቱ ነገር አሳሳቢ ሆኖ አግኝተነዋል። ይህም በባለሞያዎች እንደሚነሳው በሳይበር ደህንነት፣ በፋይናንስ ተቋማት፣ በአገራዊ ምስጢሮች እንዲሁም በሌሎች በርካታ ዘርፎች ላይ ሊያመጣ የሚችለው ቀውስ እንዳለ ሆኖ መንግሥት ዜጎቹን ቢያንስ መሠረታዊ መብቶቻቸውን በማክበር እኩልነታቸውን ማረጋገጥ ይገባዋል።
በኢትዮጵያ ከእለት ወደ እለት እየጨቀየ የመጣው የፖለቲካ ሜዳ አሁን ከሸር፣ ተንኮል እና ሴራ ፀድቷል ቢባል ያስተዛዝባል። አብረው ታግለው ዛሬ ባላንጣ ሆነው የተማማሉላቸውን ሃሳቦች ማሳካቱ ቀርቶ በተለያየ ጥግ ቆመው መመልከትን ከለመድን ሰንብተናል። የሃሳብ ልዩነቶች መኖራቸው ወይም ከዚህ ቀደም በአንድ ድርጅት ወይም በተመሳሳይ ጎራ የቆመ ዛሬ ላይ የግብ ለውጥ ማድረግ በየትኛውም የዴሞክራሲ ስርአት ውስጥ የተለመደ እንጂ እንግዳ ጉዳይ አይደለም። ነገር ግን በኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ባለው ነውጥ ዜጎች እየረገፉ እና የሰቆቃ ዜና መስማት ተለምዶ ‹‹ደሞ ዛሬ ስንት ሰው ሞተ›› እንጂ ‹‹እንዴት ሰው ሞተ›› ብሎ መጠየቅም ቀርቶ አገር በጭንቅ ውስጥ ነች ብንል ሃሰት አይሆንም። ታዲያ እንዲህ በጨቀየው የመጫወቻ ሜዳ ላይ የጊዜውን የሃሳብ ቦይ የሚቀደው ማህበራዊ ሚዲያ በእንዲህ አይነት ድርጊቶች ከታጀበ ጨዋታው ዳኛ የሌለበት መሆኑ አይቀርም።
የማህበራዊ ሚዲያዎቹ ከተጠለፉ በኋላም ሆን ተብለው በሚተላላፉ መልዕክቶች ሊደርሱ የሚችሉ ጥፋቶችም ከወዲሁ ሊታዩ የማይችሉ እና የተደበቁ አይደሉም። የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችም ሆኑ የመብት ተሟጋቾች የሚደርስባቸውን ጠለፋ ይፋ ከማውጣት ባለፈ አሁንም በሕጋዊው መስመር ለማስፈተሽም ሆነ የሕግ ተጠያቂነት ለማምጣት ሲሞክሩም አይታይም። ነገር ግን የምርጫ ወቅት ላይ ቆመን የሳይበር ደህንነትን እንዳላዩ ሆኖ ማለፉ የተጀመሩትን ድርጊቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ማበረታታት ነው። የዲጂታል መብት ተሟጋች እና ተንታኝ የሆኑት ብርሃን እንደሚሉትም የሳይበር ወንጀሎችን ለሕግ ማቅረብ እና ማስቀጣት ከመደበኛው ወንጀል የበለጠ የሰለጠነ የሰው ኃይል የሚፈልግ እና ማስረጃዎችን ማግኘትም ቀላል ባለመሆኑ ሰዎች ለክስ ላይበረታቱ ይችላሉ። የሕግ ፈፃሚ አካላት ከመረጃ መረብ ደህንነት ተቋማት ጋራ በመሆን ጠንከር ያለ የሕግ ማስከበር ሥራ መሥራት አለባቸውም ይላሉ። በርግጥ የዲጂታል ዓለምን በሕግ እና በደንብ ቆንጥጬ ካልያዝኩ ቢባልም የሚቻል አይደለም ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
የመረጃ ጠለፋው የማህበራዊ ሚዲያ አውታሮች እና የኢሜል ልውውጦች ላይ ያተኮረ ሲሆን እነዚህ የመገናኛ አውታሮች ደንበኞቻቸው አባል ሲሆኑ የሚገቧቸው የደህንነት ማስተማመኛ ቃላት አሏቸው። ከዛም ባሻገር በእነዚህ አውታሮች ላይ የማይተላለፉ ይዘቶችን ለመለየትም ድርጅቶቹ ጥብቅ ደንብ እና ግዴታዎች እንዳሏቸውም ደጋግመው ይናገራሉ። ከእነዚህ መስፈርቶች ያፈነገጡ ይዘቶች ተሰራጭተው ቢገኙም ሪፖርት የሚደረግባቸው መንገዶች እንዳሉ የሚታወቅ ቢሆንም በኢትዮጵያ ውስጥ በሚነገሩ ቋንቋዎች የሚሰራጩ መረጃዎችን የሚያጣሩበት መንገድ ግን ጠባብ ነው። ብርሃን እንደሚሉትም ምንም እንኳን የይዘት ፍተሻዎች ቢኖሩም የአገሪቱን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት እና አውዱን በመረዳት የማህበረሰቡን እሴቶች የሚጎዱ ወይም ግጭት የሚቀሰቀሱ ወይም የተለያዩ አግባብነት የሌላቸው ይዘቶችን መለየት የሚችል የሰው ኃይል አላቸው ወይ የሚለው አጠያያቂ ነው።
በኢትዮጵያ እስከ ታህሳስ 2012 ባለው መረጃ 45.4 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የቴሌኮም አገልግሎት ይጠቀማል። ከዚህ ውስጥም 23 ሚሊዮን ገደማ የሚሆነው ዜጋ የዳታ ተጠቃሚ ሲሆን 44 ሚሊዮን የሚጠጋ የሞባይል ተጠቃሚ መኖሩንም ኢትዮ ቴሌኮም ገልጿል። በመሆኑም ድርጅቱ ይህንን ትልቅ ገበያ የሚያስተዳድርበት እና የሚሰጠው አገልግሎትም የተቋሙንም ሆነ የኢትዮጵያውያንን ጥቅም በማይነካ መልኩ መሆኑን የሚያረጋግጥበት ስርአት መዘረጋት ይገባዋል። ይህንንም እውን ለማድረግ መንግሥታዊ የሆኑም ያልሆኑም ተቋማት ቅስቀሳ እና ማስተባበር በማድረግ ጫና መፍጠር ይገባቸዋል። ሚሊዮን ዶላሮች የሚሰበሰቡበት ገበያም በአግባቡ ሃብት ፈሰስ በማድረግ በተገባው ቃል መሠረት ካላስተዳደረ አገልግሎት እንዳይሰጥ እስከመታገድ ድረስ ሊደርስ ይገባል።
የዲጂታል ዓለሙን ብንተዋወቀውም ተለማምደነዋል ለማለት ግን ያስቸግራል። ስለዚህም የዲጂታል ጤና አጠባበቅ ዘዴዎችን በመማር የግል መረጃዎቻችንን ከመንታፊዎች መጠበቅ የሁላችንም ድርሻ ቢሆንም መንግሥት ግን የሰብአዊ መብቶች አካል የሆነውን የግል ምስጢር የመጠበቅ መብትን ሊያከበር እና ሊያስከበር ይገባል። ፍትሃዊ የሆነ የፖለቲካ የውድድር ሜዳ በማስፋት ለተፎካካሪዎቹም ሆነ ለባላንጣዎቹ ምሳሌ መሆን ይገባዋል። ብርሃን እንደሚሉትም በመገናኛ ብዙኃን የዲጂታል ጤንነት አጠባበቅ ዘዴዎችን ማስተማር ያስፈልጋል። አዲስ ማለዳ በዚህ የዲጂታል ዘመን፣ የአገር ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ እና ማህበራዊ ግንኙነቶቻችን ሁሉ በዲጂታሉ ዓለም ላይ በሰፈሩበት ወቅት የዲጂታል ደህንነትን ማረጋገጥ ካልተቻለ እንደ አገር ወደ ከባድ አረንቋ መግባታችን አይቀርም ትላለች።
መጪው የምርጫ ወቅትም በሰላም እንዲገባደድ መሰል ድርጊቶችን ለማስቆም አንድ ሊባል ይገባል። ከዲጂታል ዓለም ውጪ ያለው የፖለቲካ ፉክክርም ሆነ ሽኩቻ ወደ ዲጂታሉ ዓለም መግባቱ እንደሰለጠነው ዓለም በቀላሉ የምንሻገረው ሳይሆን በፉክክር መሰረታዊ ተቋማቶቻችን ድረስ ዘልቆ የሚገባ ነው፡፡ አዲስ ማለዳም የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ የዲጂታል ዓለሙን ጤንነት በመጠበቅ ከአሁኑ እንዲጠነቀቁ ጥሪዋን ታቀርባለች፡፡
ቅጽ 2 ቁጥር 64 ጥር 16 2012


