አወዛጋቢው የታሪክ ማስተማሪያ ሞጁል ተሸሽሎ ሊተገበር ነው

0
717

ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች የታሪክ ትምህርትን ለማስተማር ታስቦ ተዘጋጅቶ የነበረው ሞጁል ሲነሱበት የነበሩት ቅሬታዎች ላይ ማሻሻያዎች ተደርገውበት በመጪው መንፈቅ ሊተገበር ነው። በመላ አገሪቱ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ መምህራን ‹‹የኢትዮጲያ እና የምስራቅ አፍሪካን ታሪክ ማስተማሪያ ሞጁል›› በሚል ስያሜ ለመስጠት የታሰበውን የታሪክ ትምህርት ለማስቀጠል ሰፊ ውይይት አካሂደዋል። በዚህም መነሻ አከራካሪ በሚባሉ ይዘቶች ላይ ውይይት በማድረግ ግብአት ተሰብስቦ አዲስ ረቂቅ መዘጋጀቱን የሳይንስ እና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።

አስተያየቶቹ ከተሰበሰቡ በኋላ ኮሚቴ ተዋቅሮ እንደተመለከተው እና ቀጣዩ መንፈቅ ከመጀመሩ በፊት የተለያዩ ውይይቶች ተካሂደው መግባባት ላይ ይደረሳል ተብሎ ይጠበቃል ሲሉ የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ደቻሳ ጉርሙ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ከተደረጉት ዋና ዋና ማሻሻያዎች መካከል አንዱ ሙሉ ለሙሉ በታሪክ ማስተማሪያው ውስጥ ያልተካተቱ የኢትዮጵያ ክፍሎች መኖራቸውን አስመልክቶ የቀረበው አስተያየት ሲሆን ይህም በረቂቁ ላይ እንዲሻሻል ተደርጓል ብለዋል።

የታሪክ ሞጁሉ ታሪክን ከማዛባት ባሻገር የታሪክን ቅደም ተከተል ያልጠበቀ ነው በሚል በከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ ውስጥ እንዳይተገበር ታግዶ ነበር። እንዲሁም ማስረጃ የሌላቸው አፈ ታሪኮች ተካተዋል በሚል የቀረበውን አስተያየት በመቀበል በማስተማሪያው ላይ ማስረጃ ያላቸው ብቻ ተካተው፤ ማስረጃ የሌላቸው መቀነሳቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ደቻሳ ጉርሙ አክለው እንደገለፁትም ለቀጣይ መንፈቅ ዓመት ረቂቁ ቀርቦ ካልፀደቀ እና የዩኒቨርሲቲዎች ሰላም አስተማማኝ ደረጃ ላይ ካልደረሰ ሞጁሉ የሚተገበርበት ቀን ሊራዘም እንደሚችል ነገር ግን ይህ እድል ጠባብ እንደሆነም ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የታሪክ ተመራማሪው ሳሙዔል አሰፋ እንደሚሉት ከዚህ ቀደም የነበረው ካሪኩለም ተኣማኒነቱ ጥያቄ ውስጥ የገባ ነበር። በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ ታሪክ አፃፃፍ ላይ የሚነሳው የወገንተኝነት ችግር በዚህ ማስተማሪያ ላይ ታይቷል ብለው የሚያምኑት ሳሙኤል አዲስ ተዘጋጀ የተባለው ማስተማሪያም ይሄን ቅሬታ በአግባቡ ካላሻሻለ ፖለቲካዊ ቀውሱን እና በትውልድ ላይ የሚፈጥረውን ውዥንብር ይጨምረዋል ብለዋል። የታሪክ አፃፃፉ የብሔር ብሔረሰቦችን ታሪክ ብቻ ሳይሆን እንደ ኢትዮጲያ ታሪክ ተዘጋጅቶ መቅረብ አለበት የሚሉት ባለሞያው ይህ ሲሆን ‹‹የኔ ብቻ በማለት ጽንፍ ከመያዝ የእኛ የሚባል ታሪክ እንዲሆን እድል ሊከፍት ይገባል›› ብለዋል።

የአገሪቷ ታሪክ ለፖለቲካ ፍጆታ እንዳይውል የታሪክ ጸሐፊዎችን እና የታሪክ ተመራማሪዎችን ብቻ ለዚህ ሥራ ማሳተፍ ያስፈልጋል የሚሉት ሳሙኤል፤ ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚሠራውን ማንኛውንም ሥራ ከስር ከስር ማስገምገም በታሪክ ላይ የሚፈጠረውን ውዥንብር ለማጥራት እና ተቀባይነት ያለው የታሪክ ማስተማተርያ ሞጁል ማዘጋጀት እንዲቻል ይረዳል ሲሉ አስተያየታቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 64 ጥር 16 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here