ደኅንነት ይሰማሻል?

0
842

የኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ናት። እህቴ ስለሆነችና በቅርበት ስለማውቃት፣ ከተማሪነቷ ላይ ጎበዝ፣ በራስ መተማመን ያላትና ደፋር መሆኗን አውቃለሁ። ገና ተማሪ ስለሆነችና ዋናውን የሕይወት ሩጫ ባለመጀመሯ፣ አላት ብዬ የማምነው ጥንካሬ እንዳላት የምታውቅ አይመስለኝም። በቀደም ግን ከማይባት ጥንካሬ ውስጥ ሌላ ዓለም እንዳለ ገባኝ። እንዲህ ነው፤ በቤተሰብ ጨዋታ መካከል መንገድ ላይ በማንኛውም ሰዓት ለብቻዋ መንቀሳቀስ ምቾት እንደማይሰጣትና ፍርሃት ፍርሃት እንደሚላት አነሳች።

አልፎም፤ ‹‹በአካባቢዬ ዞር ዞር ብዬ በደንብ አያለሁ። ተለቅ ያለ ድንጋይ የሚገኝበት አካባቢ ካልሆንኩኝ እንደውም የባሰ ይጨንቀኛል፤ አነስ ያለ ድንጋይ ሳይ ትልቅ ቢኖር እያልኩ እመኛለሁ›› አለች። ነገሩ አስደንግጦኛል። እንደውም ጨምራ ከኋላዋ የሰው ጥላ ሲያርፍባትም ሆነ እልፍ ሲላት ፍርሃቷ እንደሚያይል ነገረችን። ‹‹ለምን ትፈሪያለሽ፤ ይህማ ጥሩ አይደለም!›› በሚል የቀረው የቤተሰብ አባል ትንሽ ሐሳቡን ሰጣት። ‹‹የእኔ ይገርማችኋል፤ እገሊትኮ እንደውም ስለት ነገር ይዛ ነው የምትንቀሳቀሰው›› ስትል የጓደኛዋን ሥም ጠርታ ክው አደረገችን። ለምን? እኛስ ለምን ክው አልን? ለምንስ ነው ጓደኛዋ ስለት ይዛ የምትንቀሳቀሰው? እህቴ በእንቅስቃሴዋ ደኅንነት ስሜት እንደማይሰማት ገባኝ። በእርግጥ ብዙ ሴቶች በዛ ውስጥ እንዳለን የታወቀ ነው። እንደው የፖለቲካውና አገራዊ የደኅንነት ጉዳይ ያለበት ሁኔታ እንዳለ ሆኖ፣ ሴቶች ደግሞ የበለጠ ለፖለቲካ ጨዋ በሆነ አካባቢ እንኳ ደኅንነት አይሰማንም።

ለአራዊት በተፈቀደና ለሰው በተከለከለ ሰዓት የመንቀሳቀስ ያህል ምሽቱን የሚፈሩተ ጥቂት አይደሉም። ምሽትም ለወንዶች ብቻ የተፈቀደ ይመስል በምሽት ለሴቶች መንቀሳቀስ በ‹ወንድ› እና በሌባ መካከል እንደመንቀሳቀስ ነው። ይህቺ እህቴ ሴቶች ብቻ በሚማሩበት ትምህርት ቤት የምትማር በመሆኗ ሊደርስባት የሚችለው ተጽእኖ ምን ያህል ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ገመትኩ። አስታውሳ ከነገረችኝ ክስተቶች መካከል አንዱ የሚከተለው ነው። ኹለት ሴቶችና አምስት ወንዶች በአንድ ክፍል ውስጥ እንዲገኙ ተደርጎ ክፍሉ ተዘጋ።

እነዚህ ሴቶች ታድያ ጭንቀቱን መቋቋም አቅቷቸው በመስኮት ከአንደኛ ፎቅ ዘልለው ከክፍሉ ወጡ። እግራቸው ላይ ሊደርስ የሚችለው ጉዳት ወይም ከወረዱ በኋላ የደረሰው ጉዳት አልተሰማቸውም። ከዛ የበለጠ ሰውን ‹ወንድን› እንደ አውሬ እንዲሸሹ ሆነዋል። እነዚህ ነገሮች በሥነ ልቦና ላይ በተለይም ገና አዳጊ በሆኑ ልጆች ላይ ያለውን ጫና የሚያሳዩ ናቸው። ነገሮችም ይተሳሰራሉ። የአንድ ሰሞን ርዕሰ ጉዳይ ከመሆን ባለፈ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች ፍትኅ ቆማ አልታየችም/አላየንም። ጭር ባለ መንገድ እንደ እኔ እህት ያለች ሴት ጥቃት ቢደርስባት ‹‹ለምን ሰው በበዛበት ቦታ አትሄጅም›› ነው የምትባለው። በማንም ልትተማመን አትችልም። አደጋ የማያደርስባት፣ አልፎም ሊጠብቃት የሚችል ወንድ ሊኖር ይችላል ብላ እንኳ አትጠረጥርም።

ይህ ያየሁትና የሰማሁት እውነት ነው። እንግዲህ ቀጣይ ተረካቢ ወጣት ሴቶች በዚህ መንፈስ ውስጥ እንዳሉና ይህን እያሰቡ እንደሆነ ማን ምን ያህል ልብ ብሎት እንደሆነ እኔ አላውቅም። ግን በእጅጉ አሳሳቢ ስለመሆኑ ሳልናገር ማለፍ አልቻልኩም። እርግጥ ነው! በደፈናው ለሁሉም ሰው የማይመች የከፋ ጊዜ ላይ ነን የሚሉ አይጠፉም። የእህቴን ስሜት ሳዳምጠው ግን ከዛም የከበደ ጫና አለ። እኔና ቤተሰቤ ጆሮ ሰጥተን የሰማነው እንዲህ ያለ ስጋት የገባት ደኅንነት የማይሰማት ስንት እህት በየጎጆው ትኖር ይሆን? መንገድ ላይ ይቅርና በገዛ ቤቷ ከባሏ፣ ከወንድሟ፣ ከአጎቷ ከዘመዷ ጋር ሆና እንኳ ደኅንነት የማይሰማት ስንት አለች!

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here