የሴቷን ድምፅ ዋጋ፤ ከብልፅግናው ዘይት በፊት!

0
623

አገራዊ ምርጫ ደርሷል፤ በቅርቡም ፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያዩ የምረጡኝ ቅስቀሳ ማድረግ ይጀምራሉ። በዚህ ጊዜ ደግሞ ቀድሞ የተዘነጉና ድምጻቸው ሳይሰማ የቆዩ ከፍተኛ ድርሻ የያዙት የሴቶች ድምጽ መጠየቁ አልቀረም። ብልፅግና ፓርቲን በዋናነት ያነሱት ሕሊና ብርሃኑ፣ በቅርቡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሴቶችን በተሰበሰቡበት ፓርቲውን በሚመለከት ተናግረው እንደነበር አውስተዋል። ይህም የሴቶችን ድምጽ ለማግኘት የሚደረግ አንዱ እንቅስቃሴ ነው ያሉት ሕሊና፤ አስቀድሞ ለቀረበ የሴቶች ‹እኛንም አናግሩን› ጥሪ ምላሽ እንዳልተሰጠ ጠቁመዋል። አሁንም ቢሆን በንግግርና ጥቂት ሴቶችን ወደ ሥልጣን በማቅርብ ሳይሆን የፖሊሲና የአሠራር መሠረታዊ ለውጥ በማምጣት የሴቶችን ድምጽ በሥራ ሊያገኙ ይገባል እንጂ ሸቀጥ አይደለም ሲሉ አስምረው ያነሳሉ።

ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም ይባል የለ? ምርጫ በነሐሴ ሊሆን ነው ሲባል ሰማን። ይሁን! የሴቷ አምላክ ዝናቡን ከያዘ ችላችሁ ሞክሩት።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ባለድርሻ አካላትን በመጥራት የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ላይ ምክክር አድርጎ ነበር። በዚሁ ቀን በተመሳሳይ ሰዓት በሚሊኒየም አዳራሽ አንድ ሌላ ድግስ ነበር። የብልፅግና ድግስ! የኮሮጆ ጉዳይ። ሊበሏት ያሰቧትን ድምፅ ‘አንቺዬ ፆታሽ ማማሩ’ ሊሉ፤ ሊያባብሉ ያሰናዱት ድግስ!

በድግሱ ላይ ከአዲስ አበባ ከተማ የተውጣጡ ሴቶችም ታድመው ነበር። ከፓርቲ ጉድኝት ነፃ መሆናቸው በሕግ የተደነገገላቸውን ክብርት ፕሬዝዳንት ፎቶ በባነር ታትሞላቸው በአዳራሹ ግድግዳ ላይ ተሰቅሎ ነበር ፕሮግራሙ የተካሔደው። እንዲህ ያለው የሕግ ጥሰት ምን ያህል አለማወቅ ወይም ማን አለብኝነት እንደሆነ ደጋሾቹ ይወቁት። የፕሬዝዳንቷ ቢሮ ስለዚህ ፈቃድ ሰጥቶ ይሆን?

ከድግሱ ድባብ ወደ ይዘቱ ስንመጣ እነኚህ ሴቶች የተጠሩት ስለ አገራዊ ጭንቀቶቻቸው፣ የዜግነት ክብራቸው፣ ስላሉባቸው ፆታዊ ተግዳሮቶች እና መሰል ሐሳቦችን ለማወያየት እንዳይመስላችሁ። እንዲህ ነው፤ ከዚህ ቀደም የአገራችን ርዕሰ መንግሥት (ጠቅላይ ሚኒስትር) በተጠቀሱት አጀንዳዎች ላይ ከሴቶች ጋር እንዲወያዩ በተደጋጋሚ ቢጠየቁም ምላሻቸው ግን አሉታዊ ነበር። አሁን ግን ‘ዐይኔን በጨው’ ብለው “እምቢ አላገኝሽም” ያሏትን ሴት የምርጫ ጊዜ ደርሷልና ድምጿን ለመቀራመትና ለማባበል የፓርቲ ሊቀመንበርነት ካባቸውን ደርበው ሚሊኒየም አዳራሽ ለተማፅኖ መጥተዋል።

በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ገዥው ፓርቲ ለሴቶች እጅግ የተመቸና የሴቷን ጥያቄ በመመለስ ግንባር ቀደም እንደሆነ አበልፃጊው ጠቅላይ ሚኒስትራችን ተናግረዋል። በመድረኩም ለኢትዮጵያዊቷ ሴት ብቸኛው አማራጭ የብልፅግና መንገድ እንደሆነ ተደጋጋሚ ቅስቀሳ ሲያደርጉም ነበር። እስኪ ጉዳዩን ትንሽ እናፍታታ እና በዝርዝር እንየው፤

ብልፅግና በሴቷ ሲፈተሽ

ብልፅግና ፓርቲ በቅርቡ የተዋቀረ የፖርቲዎች ውህደት ቢሆንም በኹለት መንገድ ልንገመግመው እንችላለን። አንድም እንደ ውህድ ፓርቲ ባዘጋጃቸው ፕሮግራሞችና የፖሊሲ አቅጣጫዎች ነው። አልያም የ’ለውጡ’ አቀንቃኝ ቁንጮ መሪዎች ላለፉት አስራ ዘጠኝ ወራት ከሴቶች ጉዳይ ጋር በተያያዘ በወሰዷቸው አዎንታዊ ወይም አሉታዊ እርምጃዎች እና ተስፋ ፈንጣቂ ወይም ስጋት አጫሪ ሆነው ባለፉት ድርጊቶቻቸው ነው።

ለመሆኑ ፓርቲው በአመራር ደረጃ የትኛዋን ሴት ይዞ ይሆን “ብቸኛው አማራጭሽ ነኝ” ለማለት የበቃው? በብልፅግና ኦሮሚያ ቅርንጫፍ አንዲት አዳነች አቤቤ? በብልፅግና አማራ ቅርንጫፍ አንዲት ዳግማዊት ሞገስ? በብልፅግና ደቡብ ቅርንጫፍ አንዲት ሙፈሪያት ካሚል? በዚህ የተሳትፎ ማዕቀፍ ነው ብልፅግና የሴቶች ብቸኛው መንገድ ይሆናል የተባለው። አጋር የነበሩና አሁን ብልፅግናን የተቀላቀሉ ፓርቲዎችንም ስናይ ከዚህ ብዙም የተለየ አይደለም።

በአጠቃላይ ብልፅግና ፓርቲ ካሉት የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት 11.1% ሴቶች ናቸው። ሁሏም ሴት አንድ ለፓርቲዋ በሚመስል ይዘት መደርደሯ፣ ከለውጡም በኋላ ብዙኀኑ ወደ ላይ መምጣት አለመቻላቸው አሳሳቢ ሆኖ እናገኘዋለን።

“ይኼ አሁናዊ ሁኔታ ነው፣ ቀስ በቀስ ይስተካከላል” ብለን እንዳናስብ ደግሞ በፕሮግራም፣ በፖሊሲ አልያም በሕግ ደረጃ የተቀመጠ ለውጡን ተከትሎ የመጣ የፆታ እኩልነት ማሻሻያ ማእቀፍ አላየንም፤ አልሰማንም።

እርግጥ ነው በፌዴራል መንግሥት ደረጃ ሴቶች ወደተለያዩ ቁልፍ የሥልጣን ቦታዎች መጥተዋል። ይህን ተከትሎም ብዙ ወራት ለዉጡ ተወድሷል፣ የብዙ ዓለም ዐቀፋዊ ወዳጆች ዐይን ውስጥም ገብቷል። ታዲያ ይህ ቅሬታ ምስጋና ቢስ ለመሆን ሳይሆን “በአዲስ መልክ ሥራ ጀምረናል” ያለ መንግሥትን አሠራር የመፈተሽ የአንዲት ዜጋ መብት መሆኑን ማስታወስ እፈልጋለሁ።

ለውጥም አይደል? ታዲያስ ከዚህ ያነሰ ለምን እንጠብቅ? ንፅፅሩ ከድሮው ጋር ሳይሆን ከለውጥ መሠረታዊ መርሖዎች እና ከለውጥ ባሕሪያት ጋር ሊሆን ይገባዋል እላለሁ።

በነገራችን ላይ የቀድሞው ኢሕአዴግም ቢሆን ይህን ሴቶችን ወደፊት የማምጣት ባሕሪይ መጀመሪያ አካባቢ ላይ በትጋት አሳይቶ ነበር። ታዲያ ይህን ለመደገፍ የተቀመጠ የፖሊሲና ሕግ ማዕቀፍ በበቂ አልነበረምና፣ ሴቷን ቀስ በቀስ ገሸሽ ማድረጉ እንዴትስ ይረሳል?

ከዚሁ ጋር አያይዘን ወደ ሌላኛው ሐሳብ ስንመጣ፦ በአመራር ውክልና ደረጃ የሚቀረው ብዙ ነገር እንዳለ ሆኖ ዛሬ ላይ ለውጡ ያኖራቸው የሴቶች ወደፊት መምጣት ነገ ሁኔታው ሲደላደል ሊፈርስ እንደማይችል ምን ማረጋገጫ አለን? የአንድ ግለሰብ ፈቃድ ላይ የተንጠለጠለ ችሮታ እንዳይሆንብን የመብት ጉዳይ ነው እና በሕግ ማእቀፍ ተዘጋጅቶ በሰነድ ሊቀመጥ ይገባል። “በቃል ያለ ይረሳል በጽሑፍ ያለ ይታወሳል” አይደል?

የጽሑፍ ጉዳይ ሲነሳ ከለውጡም በኋላ የሴቶችን መብት ወደኋላ የጎተቱ ሕጎችም እንደጸደቁ ማስታወስ ያስፈልጋል። በብልፅግናው ዘመን ማለት ነው። በቅርቡ እንኳ “የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የሥነ ምግባር አዋጅ” ረቂቅ አዋጅ በሚፀድቅበት ስብሰባ በሕዝብ ተወካዮች ደረጃ ጭምር ሕገመንግሥቱ ለሴቶች የሰጠውን መብት “የፆታ እኩልነት መርሕን ይፃረራል” በማለት ከረቂቅ አዋጁ አንድ አንቀፅ እንዲወጣ ተደርጓል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባሉበት በሕገመንግሥቱ የሴቶች ውክልናን ለማሳደግ የተቀመጠ አንቀጽ ተጥሶ በሙሉ ድምፅ ጸድቋል። ይህ ሕገመንግሥታዊ መብት በአደባባይ ሲፋቅ ብልፅግናው የት ነበረ?

ሴትም ሆነ ወንድ ተወካዮቻችን ሕገመንግሥቱን አለማንበባቸው አሳሳቢ ሆኖ ሳለ የወንድ ጓዶቻቸውን በማስደሰት ተስፋና ይሉኝታ ተይዘው በሚመስል መልኩ “ይህ ለምን ሆነ?” ተብለው ሲጠየቁ “አይ እኛ በማካካሻ ድጎማ (affirmative action) አናምንም” ያሉ አንዳንድ ሴት ሚኒስትሮች መልስ ደግሞ ይበልጡኑ ያስከፋል። የዜግነት መብታቸውንና ሕገመንግሥቱን ክደው፣ ተገምቶ በተሰፋላቸው ልክ ሲንቀሳቀሱ፣ የወንዳዊ ስርዓትን ለማሳለጥ ማጣፈጫ ሆነው ሲቀርቡ ማለት ይህም አይደል?

ከአመራር ቆጠራና ከሕግ ማሻሻያ ወደ ሌላኛው ፍሬ ነገር ደግሞ እንምጣ፣ ተቋማዊ ባህል። የሴቶች የፖለቲካ ሹመት በቁጥር ማደግ ለእኩል ውክልና ብሎም ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ወሳኝ ሆኖ እናገኘዋለን። ቁጥር ብቻ ግን በራሱ በቂ አይደለም። እናም ልወደድ ባይነት ይዟቸው አልያም ያሉበትን ቦታ እንደ ውለታ ቆጥረው ሲጠሩ “አቤት” ሲላኩ “ወዴት” የሚሉ ሴቶችን በኃላፊነት ወደፊት ለማምጣት ከሆነ ዋናውን ዓላማ መሳት ይሆናል።

ተሿሚዎች ያሉበትን የሥልጣን ወንበር ለሴቶች አጀንዳ ለማዋል ቢሞክሩ፣ የሴቶችን መብቶች፣ እኩል ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥ የሚችልን አጀንዳ ለማንሳት፣ አዲስ ሐሳብ፣ ሕግ፣ ፖሊሲ ለማስተዋወቅ ቢንቀሳቀሱ በዚሁ ምክንያት ዘልማዳዊ ነቀፌታና ከደረጃ ዝቅ መደረግን ጭምር ሊያስተናግዱ እንደሚችሉ ከለውጡም በኋላ አይተናል። ታዲያ የመንግሥት ሥልጣን ተይዞ ማኅበረ – ባሕላዊ ለውጥ ጭምር ካልተጠየቀ ትርጉሙ ምን ላይ ነው?

የሴቶች ጥያቄ የቁጥርና የሕግ ብቻ ሳይሆን አገራዊ የባህል እና አመለካከት መስተካከልን፣ ይህም እንዲሆን ከመሪ ግለሰቦች እስከ ተቋማዊ ፖለቲካ አሰራር መታረምን አልፎ ተርፎም ተምሳሌታዊ መሆንን ይጠቃል። ይህ ሳይሆን ሲቀር እኛም እንጠይቃለን፤ ሴቶች መንግሥት ትኩረት ሊነፍጋቸው የሚገባ ኹለተኛ ዜጎች ናቸውን? ኢትዮጵያስ የእኛም አገር አይደለችምን?

ይህ ሴቶችን የማገልገል ግዴታ ታድያ ሴት ሚኒስትሮች እና ኃላፊዎች ላይ ብቻ ልንተወው የምንችለው ጉዳይ መሆን የለበትም። ዐሥር ሚኒስትሮች ሴት ሆኑ እንጂ ኻያውም፣ ወንዶቹን ጨምሮ ማለት ነው፣ የሴት ኢትዮጵያውያን ጥያቄዎችን የመመለስ ግዴታ አለባቸው። በሌላ ጎን ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ክብርት ፕሬዝዳንቷ ሲሆኑ እንዳየነው ሴት የሴቷን አጀንዳ ብቻ እንደሚመለከታትና በሌሎች አገራዊ አጀንዳዎች ላይ የዳር ተመልካች እንድትሆን የሚደልል ብልፅግናንም አልቀበልም። የታችኛውን ቤት የሴቷ፣ ሌላውን አጀንዳ ወደ አራት ኪሎ ዓይነት በማስከተልም የምርጫ ድምፄን ከመስጠቴ በፊት ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ ማግኘት እሻለሁ፦

በብልፅግና ውስጥ ዕጩዎች ምልመላ እንዴት ይከናወናል? እንዴት ለሕዝብ ይፋ ይሆናል? ሒደቱ ግልጽነት እና ተጠያቂነት አለው? ሴቶች ሁሉ ተመሳሳይ እንዳልሆኑ እገነዘባለሁ። ጥያቄዎቻቸውም በርከት ያሉና ፈርጀ ብዙ ናቸው። እነዚህን መጠነ ሰፊ ጥያቄዎች እንዴት ልትመልሱ ተዘጋጅታችኋል? በፓርቲው ውስጥ ዕጩ ሆኖ ለመቅረብስ ምን ዋጋ ያስከፍላል? ዕጩ ለመሆን ፍላጎት ያላቸው ሴቶችን ለማግኘት የትኞቹን አደረጃጀቶች ትጠቀማላችሁ? የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ የሃይማኖት፣ የመደብ፣ የብሔር፣ የአካል ጉዳተኞች፣ የአርብቶ አደሮች ተወካይ ሴቶችን እንዴት ልታካትቱ አስባችኋል? ሴቶች የመምረጥ/ የመመረጥ መብታቸውን ተጠቅመው ድምፅ እንዳይሰጡ/ እንዳይወዳደሩ የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች እንዴት ለመፍታት አስባችኋል?

ብልፅግና ሆይ ከላይ የጠቀስኳቸውን ስህተቶች በማረምና ለተቀመጡት ጥያቄዎች ፈጣን የሆኑ ምላሾችን በመስጠት የሴቷን ድምጽ ማግኘት ይችላል። የኢትዮጵያ ሴት ቅንጦት አልጠየቀችም። በጭራሽ! መሠረታዊ የሆነውን የወር አበባ ንፅሕና መጠበቂያ ሞዴስ እንኳን ከቀረጥ ነፃ ለማስገባት ስንታገል ስንት ዓመት ገፋን? የኢትዮጵያ ሴት ከሌሎች ዜጎች በተለየ ቀይ ምንጣፍም ይነጠፍልኝ አላለችም። በእኩል ዐይን ልታይ፣ በቤትና ከቤት ውጭ እየተጋፈጥኩት ያለው አሸማቃቂና አስፈሪ ጥቃት ይቅርልኝ፤ በዜግነቴ እኩል ልቆጠር ነው ያለችው።

ይህም ሕገመንግሥታዊ መብቷ መሆኑን ታውቃላችሁ። አሁን ምርጫ ሲደርስ እየጠራችሁ የምትማፀኗት ድምጿ ምን ያህል ዋጋ እንዳለው ስለምትረዱም እንደሆነ የአደባባይ ምስጢር ነው። በሴቷ ድምፅ መቆመርና ጊዜያዊ ድግስ ቀርቶ እንደ ማንኛውም ዜጋ መብቷ ሲከበርና የፖለቲካ እኩልነት ሚዛን ላይ ስትቀመጥ አጀንዳዋም እኩል ክብደት ሲሰጠው የሚበጃትን መዝና ድምጿን ለሚገባት/ው ትሰጣለች። ይህ ካልሆነ ደግሞ ሴቷ ራሷን አደራጅታ የፖሊሲ አጀንዳዎችን ነድፋ ልትታገላችሁ ትገደዳለች፤ የተገፋ ማኅበረሰብን አቅም መቼስ ከብልፅግናው በላይ የሚያውቀው የለም።

ሴቶች ሆይ “በኢሕአዴግ ቁጥር አንድ” ዘመን የሴቶች ድምፅ “ዘይት፣ ቅንጬ እና ዘጠና ብር ያወጣል” ይባል ነበር። እናም ብልፅግናው ዘይቱን ለምግብም ይሁን ለሌላ ጥቅም ከመከጀሉ በፊት፣ የምንፈልገውን በግልፅ ማስቀመጥና እኛው የጥያቄ ድግስ አዘጋጅተን ምላሽ እንዲሰጡን ጥሪ ማቅረብ ይኖርብናል። የሴቷ ድምፅ በርካሽ የሚገኝ ሸቀጥ አይደለም! መሥራትን ይጠይቃል።

ሕሊና ብርሃኑ የሥርዓተ-ፆታና የሕግ ባለሙያ ሲሆኑ፣ በዚህ አድራሻ ይገኛሉ bhilina.degefa@gmail.com

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here