በኹለት ወር የጤፍ ዋጋ አምስት መቶ ብር ጨመረ

0
1027

ከኅዳር ወር መጀመሪያ አንስቶ ጭማሪ ማሳየት የጀመረው የጤፍ ዋጋ፣ እስከተገባደደው ሳምንት መጨረሻ ድረስ እስከ 500 ብር የዋጋ ጭማሪ አሳየ።
ማኛ ነጭ ጤፍ እስከ 4 ሺሕ 500 ብር ድረስ በመሸጥ ከፍተኛው የዋጋ ንረት የታየበት ሲሆን፣ ቀይ ጤፍ በኩንታል የ300 ብር ጭማሪ እና ሰርገኛ ጤፍም በተመሳሳይ የ300 መቶ ብር ጭማሪ በማሳየት ወደ 3 ሺሕ 400 ብር ከፍ ማለቱን አዲስ ማለዳ በገበያ ላይ ያደረገችው ቅኝት ያሳያል።

ካዛንቺስ አካባቢ የሚገኘው ድል በጌ ገበያ ውስጥ ነጭ ጤፍ በ 4 ሺሕ 500 ብር ሲገዙ አዲስ ማለዳ አግኝታ ያነጋገረቻቸው ሳምሶን ታዬ እንደሚሉት፣ ከኹለት ወራት በፊት በ4 ሺሕ ብር ተመሳሳይ ነጭ ጤፍ መግዛታቸውን ይናገራሉ። ከአራት ወር በፊት በ3 ሺሕ 300 ብር ሲሸጥ የነበረው ኹለተኛ ደረጃ ነጭ ጤፍ፣ የ 700 ብር ጭማሪ በማሳየት 4 ሺሕ ብር የገባ ሲሆን፣ እምቡር የተሰኘው የነጭ ጤፍ አካባቢ የሚመጣው ጤፍ ሙሉ በሙሉ ከገበያ መጥፋቱን አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ነጋዴዎች ተናግረዋል።

የጤፍ ምርት የሚሰበሰብበት የመኸር ወቅት ላይ ዘንቦ የነበረው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እየጨመረ ለመጣው የጤፍ ዋጋ በምክንያትነት የተጠቀሰ ሲሆን፣ በተጨማሪም የሕገወጥ ደላሎች መበራከት የንግድ ሰንሰለቱን እንዳረዘመው እና ይህም ለዋጋ መጨመሩ ምክንያት መሆኑን ነጋዴዎች ገለፀዋል።

የድል በጌ ጤፍ መሸጫና ማስፈጫ ባለቤት የሆኑት ሀያት በረከት እንደሚሉት፣ ከዚሀ በፊት ከገበሬዉ በቀጥታ በመረከብ ለገበያ ያቀርቡ ነበር። አሁን ግን ደላሎች ይህንን ሂደት በመከልከል ተፅእኖ እስከማሳደር መድረሳቸውን ተናግረዋል። ከጊዜ ወደ ጊዜ የደላሎች ቁጥር መብዛት እና በተያዘው ሳምንትም የጤፍ ዋጋ ላይ ጭማሪ መደረጉን ደላሎች እንደነገሯቸዉና፣ ከዚህ በላይ አልጨምርም ብለዉ እንዳልገዙ ነግረዉናል። የደላሎች ትስስርም በኹለት ቦታ መሆኑን ሀያት ጨምረዉ ተናግረዋል።

የሰብር ወፍጮ ቤት ሠራተኛ የሆኑት ከሚል አሕመድ እንደሚሉት ደግሞ፣ አንደኛ ደረጃ ጤፍ ዋጋው በመወደዱ ምክንያት ደንበኞቻቸው መግዛት በማቆማቸው እርሳቸውም ጤፍ ማቅረብ ማቆማቸውን ገልፀዋል። ከኹለተኛ እስከ አራተኛ ደረጃ ያለ ነጭ ጤፎ እያንዳንዱ እስከ ሦስት መቶ ብር በኩንታል መጨመሩንም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የጤፍ ዋጋ ላይ በስድስት ወር ውስጥ የአንድ ሺሕ ብር ጭማሪ መታየቱን አዲስ ማለዳ በተለያዩ የጤፍ መሸጫ ቦታዎች ተዘዋውራ ያነጋገረቻው ነጋዴዎች አረጋግጠዋል።

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የንግድ ክትትልና ቁጥጥር ኃላፊ ሀብታሙ ጥላዬ፣ የዋጋ ንረቱ እዚህ መድረሱን እንደማያውቁ ተናግረዋል። ከዚህ በፊት የነበረዉ የጤፍ ዋጋ ከ3 ሺሕ 200 እስከ 3 ሺሕ 500 መሆኑንና እየታየ የመጣውን የዋጋ ንረት ለማስተካከልም በጥናት ላይ ተመስርቶ እርምጃ እንደሚወሰድም አስታውቀዋል።
ከዚህ በፊት የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ሕገ ወጥ ነጋዴዎችንና ደላሎችን ለመቆጣጠር ንብረታቸዉን የመዉረስና በሕግ የማስቀጣት ሥራ እየሠራ መቆየቱና አሁን ያለዉ የሕገ ወጥ ደላሎች ዝዉዉር አዲስ መልክ ይዞ መምጣቱን ሀብታሙ ጠቅሰዋል።

ሀብታሙ እንደሚሉት፣ ወቅቱ የመኸር ወቅት ከመሆኑ አንፃር የገበያ ሁኔታዉ መቀነስ ሲኖርበት፣ ነገር ግን ሊቀንስ ባለመቻሉ ምክንያቱን ለማወቅ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ጥናት እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል። ችግሩን የአድስ አበባ ንግድ ቢሮ ብቻ ሊያስቆመዉ ስለማይችል፣ ሌሎች የሚመለከታቸዉ አካላት ተሳትፎ እንደሚያስፈልግም ለአዲሰ ማለዳ ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 65 ጥር 23 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here