በአዲስ አበባ ከ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ የወጣባቸው ሼዶች ያለሥራ ቆመዋል

0
599

የአዲስ አበባ ከተማ ሥራ እድል ፈጠራ እና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ከ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ የወጣባቸው 527 ሼዶች የኤሌክትሪክ ኃይል ባለማግኘታቸው ለተጠቃሚዎች ማስተላለፍ አለመቻሉን አስታወቀ።

የመሥሪያ ቦታዎቹ በአዲስ አበባ በሁሉም ክፍለ ከተሞች እንደሚገኙ የገለፀው ኤጀንሲው፣ ግንባታቸው ከተጠናቀቀ ከኹለት ዓመታት በላይ ቢቆጠርም የመብራት እና የውሃ መሠረተ ልማቶች ባለመሟላታቸው ሼዶቹ ያለ አገልግሎት ቆመው እንደሚገኙ ገልጿል።

ኤጀንሲው ለሼዶቹ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ የአብዛኛዎቹን ክፍያ ቢፈፅምም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እስከ አሁን ኃይል እንዳላቀረበ አስታውቋል።
ጉዳዩን ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በተደጋጋሚ አቅርበናል የሚሉት የኤጀንሲው የመሥሪያ ቦታዎች አስተዳደር ጊዜያዊ ኃላፊ ተድላ አጥናፉ፣ የአብዛኛዎቹንም ክፍያ ብናጠናቅቅም እስከ አሁን የኃይል አቅርቦት ማግኘት ባለመቻላችን ሼዶቹ ያለሥራ ቆመዋል ብለዋል።

ከኤሌክትሪክ አገልግሎትም አብዛኛዎቹ ትራንስፎርመር የሚያስፈልጋቸው ናቸው። ትራንስፎርመሮች ከውጪ አገራት በውጪ ምንዛሬ ተገዝተው የሚመጡ በመሆናቸው፣ በኢትዮጵያ ባለው ወቅታዊ የውጪ ምንዛሬ ዕጥረት ምክያንት ኃይል ለማቅረብ አልተቻለም የሚል ምላሽ ተሰጥቶናል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ከ 527ቱ የመሥሥ ቦታዎች ውስጥ 419 የሚሆኑት ከኤሌክትሪክ ኃይል በተጨማሪ የውሀ አቅርቦት የሌላቸው ናቸው ተብሏል።

አንድ የመሥሪያ ሼድ ውስጥም ከአምስት እስከ 10 አባላት ያሏቸው የኅብረት ሥራ ማኅበራት መያዝ ይችላሉ የተባለ ሲሆን፣ ሼዶቹ ወደ ሥራ መግባት ቢችሉ ከ 5 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ እድል መፍጠር ይቻል እንደነበር ተገልጿል።

የፌዴራል ሥራ እድል ፈጠራ እና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ በበኩሉ፣ በክልሎች በመሠረተ ልማት ችግር ምክንያት ወደ ሥራ ያልገቡ 492 ሼዶች፣ 8 ሕንፃዎች መኖራቸውን ጠቅሷል። ከእነዚህ ውስጥ 75ቱ ትራንስፎርመር የሚያስፈልጋቸው መሆናቸውንም አስታውቋል።

64ቱ ግምታቸው የተጠናቀቀ እና 48ቱ ደግሞ ክፍያ ተፈጽሞላቸው የኃይል አቅርቦት በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውም ተጠቁሟል። የሚመለከተው አፋጣኝ መፍትሔ ሊሰጠው እንደሚገባ የፌዴራል ሥራ እድል ፈጠራ እና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቦዘነች ነጋሽ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ባለፉት ስድስት ወራትም 742 ለሚሆኑ ሼዶች መሠረተ ልማት ለማሟላት ቢታቀድም፣ መሰረተ ልማት ሊሟላላቸው የቻለው 300 ለሚሆኑት ብቻ ነው። ሼዶቹም በኦሮሚያ 248፣ ትግራይ 27፣ አዲስ አበባ 23 እና ጋምቤላ 2 ናቸው። በግማሽ ዓመቱ 1 ሺሕ 223 የሚሆኑ በሕገ ወጥ መንገድ የተያዙ እንዲሁም የመጠቀሚያ ጊዜቸውን ያጠናቀቁ ኢንተርፕራይዞችን በማስለቀቅ ለአዳዲስ ኢንተርፕራይዞች ተሰጥቷቸዋል። እነዚህም በኦሮሚያ ክልል 342 ሼዶች፣ በደቡብ ክልል 23፣ አማራ ክልል 570፣ አዲስ አበባ 44፣ ቤኒሻንጉል 7፣ ጋምቤላ 2 እና ሶማሌ 3 ናቸው።

በስድስት ወራት ውስጥም ለ177 ሺሕ ኢንተርፕራይዞች የ8 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የገበያ ትስስር ተፈጥሯል። የተፈጠረው የገበያ ትስስርም በአብዛኛው በመንግሥት በሚወጡ ጨረታዎች እና ግንባታ ዘርፍ ላይ የተንጠላጠሉ መሆናቸውን ኤጀንሲው አስታውቋል።

በጥቃቅን ማኑፋክቸሪንግ፣ በኮንስትራክሽን፣ በከተማ ግብርና፣ በአገልግሎትና በንግድ ለ649 ሺሕ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ እድሉን ለ406 ሺሕ ዜጎች መፍጠር ተችሏል። ኤጀንሲው በሰጠው መረጃ መሠረት፣ ከተፈጠረው የሥራ እድል ውስጥ ቋሚ 273 ሺሕ ሲሆን ጊዜያዊ ደግሞ 133 ናቸው።
የሥራ እድሉ በአብዛኛው በኮንስትራክሽንና በአገልግሎት ዘርፎች ሲሆን፣ በማንፋክቸሪንግና በከተማ ግብርና የተፈጠረው የሥራ እድል ዝቅተኛ ነው።
አዲስ ማለዳ ስለ ጉዳዩ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትን በተደጋጋሚ በስልክ ብትጠይቅም፣ ምላሽ ማግኘት ሳትችል ቀርታለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 65 ጥር 23 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here