በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ በሚገኙ ከማእከላት እስከ ወረዳ ባሉ ክፍት የሥራ ቦታዎች 8 ሺሕ 100 አዳዲስ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃንን በመቅጠር ሂደት ላይ እንደሚገኝ አስታወቀ።
በ2010 እና 2011 ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ከ56 በላይ በሚሆኑ የትምህርት መስኮች የተመረቁ የአዲስ አበባ ወጣቶች እንዲወዳደሩ ጥሪ ቀርቦ፣ የበለጠ ብቁ የሆኑትን ለመለየት በተሰጠ ፈተና 8 ሺሕ 100 የተሻለ ውጤት ያላቸውን ተፈታኞች በመለየት የሥራ ቅጥር በመከናወን ላይ እንደሚገኝም ተገልጿል።
በአዲስ አበባ ከተማ ከ2011 ጀምሮ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ቅጥር እንዳያከናውኑ ታግዶ ቆይቶ ነበር ያሉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሓድጉ ፀሐዪ ናቸው። በሁሉም ማእከላት፣ ክፍለ ከተሞች እና ወረዳዎች የሚገኙ ክፍት ቦታዎችን ለመለየት በተደረገ ጥናት ከጀማሪ እስከ አራት ዓመታት 5 ሺሕ 95 ክፍት ቦታዎች መገኘታቸውን ተናግረዋል።
የሥራ ፈተናው ከተሰጠ በኋላ ተጨማሪ 3 ሺሕ ክፍት ቦታዎች በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች መገኘታው የተገለፀ ሲሆን፣ በአጠቃላይ 8 ሺሕ 95 ክፍት ቦታዎች ላይ አዳዲስ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃንን በመቅጠር ሂደት ላይ እንደሚገኝ ቢሮው አስታውቋል።
ለሥራ ቅጥሩ በወጣው ማስታወቂያም 27 ሺሕ 328 ተመዝጋቢዎችን በ10 ቀናት መመዝገብ ተችሎ እንደነበር የአስተዳደሩ ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ኃብት ልማት ቢሮ አስታውቋል።
ተወዳዳሪዎችንም ለመመዝገብ የአዲስ አበባ ነዋሪነት መታወቂያ እንዲሁም በ2010 እና 2011 መመረቃቸውን የሚያሳይ ማስረጃ እንዲያቀርቡ ሲደረግ እንደነበር ተገልጿል። እንዲሁም ቢሮው በሚመድባቸው የሥራ ቦታ ላይ ለመሥራት ፈቃደኛ መሆናቸው ሲጠየቅ እንደነበር ተጠቅሷል።
ፈተናውንም ገለልተኛ በሆነ ተቋም ለማስወጣት በመታሰቡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተዘጋጀ 70 ጥያቄዎችን የያዘ የአፕቲትዩድ ፈተና ለማኅበራዊ እና በተፈጥሮ ሳይንስ የትምህርት መስክ በፈተናው ላይ ለተገኙ ለ23 ሺሕ 328 ተፈታኞች ተሰጥቷል።
ፈተናው በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ አማካኝነት ታርሟል የተባለ ሲሆን፣ የ17 ሺሕ 608 ተፈታኞች ውጤት ለቢሮው እንደደረሰ ተገልጿል። የሌሎች ተፈታኞች ውጤት የመፈተኛ መለያ ቁጥር እና መሰል ችግሮች የወደቁ ተፈታኞች በመኖራቸው ሊካተቱ አልቻሉም ተብሏል።
የሥራ ቅጥሩ በከተማ አስተዳዳሩ ስር በሚገኙ ክፍት የሥራ ቦታ ባላቸው በሁሉም ክፍለ ከተሞች ማእከላት እና ወረዳዎች ይከናወናል ያሉት ኃላፊው፣ ተቋማቱ አስቸኳይ ሥራ ከሌላቸው በስተቀር በቀጣይ 10 ቀናት ውስጥ ይጠናቀቃል ብለዋል።
በሥራ ቅጥሩ ላይም የአንድ ብሔር የበላይነት ይታያል እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ የነዋሪነት መታወቂያ የተሰጠው ለአንድ ብሔር ብቻ ነው የሚሉ ቅሬታዎች ሲነሱ ነበር ያሉት ሓድጉ፣ አክለውም ‹‹ጥያቄዎቹ ትክክለኛ አይደሉም። ተቀጣሪዎቹ ሲመዘገቡም ሆነ ወደ ሥራ ሲመደቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጓል›› ብለዋል።
በተጨማሪም ‹‹መታወቂያ መስጠት የእኛ ሥራ አይደለም። አዲስ አበባ ከተማ ነዋሪነት መታወቂያ ማቅረብ የቻሉ አመልካቾችን መመዝገብ ግዴታችን በመሆኑ እንዲመዘገቡ አድርገናል።›› ያሉ ሲሆን፣ በፈተናው ላይ ከውጤት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ጥያቄዎች እና ቅሬታዎችን መሰብሰባቸውንና ከየካቲት 16 እስከ 20 ባሉት ቀናት ምላሽ እንደሚሰጡበት አስታውቀዋል።
የሥራ ቅጥሩም ለወጣቶች የሥራ እድል መፈጠርን መሰረት ያደረገ እና መንግሥት የሥራ እድል የመፍጠር ግዴታ ስላለበት ያከናወነው ነው። እንዲሁም በተቋማት የተመደቡትን አዳዲስ ሠራተኞች ብዛት በመመልከት የሥራ ቅጥሩ ሐሰተኛ ስለመሆኑ የሚነገረው መረጃም ትክክለኛ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
አያይዘውም ከዚህ ቀደም በከተማ አስተዳደሩ ስር የሚደረጉ የሥራ ቅጥሮች በተቋማቱ የሚደረጉ እንደነበር እና ይህም ለሙስና እና ለብልሹ አሰራር ሲያጋልጥ እንደነበር አስታውሰዋል። አሁን ግን ሁሉም የሥራ ቅጥሮች በቢሮው በኩል እንደተደረጉ ገልፀው እስከ ሰኔ 30/2012 ድረስ ተቋማቱ ምንም አይነት ቅጥር እንዳያከናውኑ ተደርጓል ብለዋል።
በኢትዮጵያ በአማካይ ሦስት ሚሊዮን ወጣቶች የሥራ የእድሜ ክልልን ይቀላቀላሉ። በየዓመቱም ከ150 ሺሕ በላይ ተማሪዎች ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚመረቁ ሲሆን፣ የሥራ አጥነት ምጣኔ በከተሞች 19 በመቶ ላይ ደርሶ ይገኛል።
ቅጽ 2 ቁጥር 66 ጥር 30 2012



