በከተማው 20ሺሕ ቤት ፈላጊዎች አሉ
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በ 2012 የበጀት አመት ይተላለፋሉ ከተባሉት ሁለት ሺህ ቤቶች ውስጥ 353ቱን ብቻ መስተላለፉ ለአመታት ገንዘብ ሲቆጥቡ የነበሩ ከ ስድስት ሺህ በላይ ነዋሪዎቹን አስቆጥቷል።
በከተማ አስተዳደሩ ከ 2008 ጀምሮ የቤት ባለቤት ለመሆን ከ 15 ሺሕ በላይ ሰዎች ገንዘብ ሲቆጥቡ የቆዩ ሲሆን በ2012ም ላለፉት ስድስት ወራት ቁጠባ ያቋረጡ ሰዎች ከእጣ ውጪ በማድረግ ለስድስት ሺህ ነዋሪዎች ለማውጣት ዝግጅት እየተካሄደ ነው።
ነገረ ግን በ 2011 ግንባታቸው ተጀምረው በተያዘው አመት ይጠናቀቃሉ ተብለው ከሚጠበቁት ሁለት ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ አምስት በመቶው ብቻ ተገንብቶ ለመተላለፍ ተዘጋጅቷል።
‹‹የከተማ አስተዳደሩ በገባው ቃል መሰረት ቤቶችን ገንብቶ ለማስተላለፍም ከፌደራል መንግስት ብድር ሲያቀርብ ነበር›› የሚሉት የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ኮንስትራክሽን ቢሮ የቤት ማስተላለፍ እና ማስተዳደር ኃላፊ አዲና መሀመድ ድጋፉ በመቆሙ ምክኒያት አስተዳደሩ እነዚህን ቤቶች በራሱ በጀት መገንባቱን ገልፀዋል።
ቤቶቹ ለተጠቃሚዎች በሚተላለፉበት መንገድ ላይ በርካታ ጥያቄዎች እየቀረቡ እንደሚገኙ ገልፀው የከተማ አስተዳደሩ ያለማቋረጥ ሲቆጥቡ ለነበሩ የአስተዳደሩ ነዋሪዎች በዕጣ እንደሚያስተላልፍ ተናግረዋል።
ከተማዋ ከፍተኛ ሆነ የቤት ፍላጎት መኖሩን የገለፁት ኃላፊው የቤቶች አቅርቦቱ ከፍላጎቱ ጋር የሚመጣጠን ባለመሆኑ በቀጣይ 20ሺሕ ቤቶችን ለመገንባት ከከተማ ልማት ሚኒስቴር እና ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት በማድረግ ላይ እንገኛለን ብለዋል።
አስተዳደሩ በቀጣይ 20 ሺሕ መኖሪያ ቤቶች ለመገንባት ለያዘው እቅድም ከፌደራል መንግስት ብድር እንዲያገኝና አሁን በአስተዳደሩ በጀት እየተገነቡ የሚገኙ ቤቶች ክፍያ ከባንክ ጋር እንዲተሳሰር ለማድረግ የፌደራል መንግስት ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ አስተደዳሩ ጥያቄ አቅርቧል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ቤቶች ኮርፖሬሽን በበኩሉ በርካታ ያልተከፈሉ ውዝፍ እዳዎችን የማስከፈል፣ በህገ ወጥነት የተያዙ ቤቶችን የማስመለስ፣ ከእገዳ በፊት የኮርፖሬሽኑን መመሪያ ለደንበኞች ቀድሞ የማስተዋወቅ፣ ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቱ በገቢ እራሱን እንዲችል እንዲሁም ህገ ወጥነትን ለማስቀረት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጿል።
ባለፉት ስድስት ወራት የቤቶችን ካርታ ሰርተፍኬት ወደ ዳታ ቤዝ የማስገባት እንዲሁም ካርታ ላልነበራቸው 1 ሺ 109 ቤቶች ውስጥ 4 መቶ 18 የሚሆኑትን የይዞታ ማረጋገጫ እንዲኖራቸው ተደርጓል የተባለ ሲሆን ቀሪዎቹን ለማጠናቀቅ ከአስተዳደሩ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑንም ታውቋል።
የመረጃ አያያዝን በዘመናዊ ቋት በመጠቀም ለማዘመን ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ የኮርፖሬሽኑ ስራ አስኪያጅ እውነቱ ወርቅነህ አስታውቀዋል።
ደንበኞች በተለይም የመንግስት ኃላፊነት ያላቸው አመራሮች ከኃላፊነታቸው ሲነሱ ይኖሩባቸው የነበሩ የኮርፖሬሽኑ የመኖሪያ ቤቶችን ለተተኪው አመራር በህጋዊ መልኩ ለማስተላለፍ ያለመፈለግ ችግርና መስሪያ ቤቱ ምንም አይነት መረጃ ሳይኖረው ለሌሎች ሰዎች ተላልፎ የመገኘት ሂደት በተጨባጭ መረጃን እያዛባና ቤቶችን በፍትሃዊነት ለማስተላለፍ አስቸጋሪ ሁኔታ መፍጠሩን ኃላፊው ተናግረዋል።
በድሬ ዳዋ አስተዳደር አሁን ተመዝግበው ከሚገኙት 15 ሺሕ ሰዎች በተጨማሪ ሌሎች 20ሺሕ ቤት ፈላጊዎች ይኖራሉ ተብሎ እንደሚገመት የአስተዳደሩ ኮንስትራክሽን ቢሮ አስታውቋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 69 የካቲት 21 2012



