አዲስ የፊልም ጣቢያ በፈረንሳይ ኩባንያ ሊከፈት ነው

0
882

ካናል ፕላስ የተሰኘ የፈረንሳይ የቴሌቨዥን ድርጅት በኢትዮጵያ የቴሌቪዥን ጣቢያ በመክፈት የኢትዮጵያ ፊልሞችን ለእይታ ሊያቀርብ መሆኑን አስታወቀ።
የፈረንሳይ የሚዲያ ድርጅት እና የክፍያ ቴሌቪዥን ኦፕሬተር ከኢትዮጵያው ኖላዊ ፊልም ፕሮዳክሽን ጋር በኢትዮጵያ በፊልም እና ሲኒማ ኢንዱስትሪ ለመሰማራት ስምምነት መፈራረሙ ታዉቋል። በስምምነቱ የካናል ፕላስ ቡድን ይዞት የሚመጣውን የቴሌቪዥን ስርጭት ከጥቂት ወራት በኋላ በኢትዮጵያ ማሰራጨት እንደሚጀምር ተገልጿል።

ከኢትዮጵያው ኖላዊ ፊልም አምራች ጋር የተደረገዉ ስምምነት የኢትዮጵያን ሲኒማ በአገር ውስጥ እና በውጭ ለማስተዋወቅ ካለው ፍላጎት ጋር የተቆራኘ መሆኑን ካናል አስታውቋል።

የኖላዊ ፊልም አምራች ሥራ አስኪያጅ ሐኒ ወርቁ ለአዲሰ ማለዳ እንደገለፁት፣ ከካናል ጋር የተደረገው ስምምነት በኢትዮጵያ ፊልም ባለሙያዎች የተሠሩ ፊልሞችን ለፕሮድዩሰሮች አስፈላጊውን ክፍያ ከፍሎ ፊልሞችን ከኖላዊ ፊልም አምራች በመግዛት በሚከፍተው የቴሌቪዥን ስርጭት ጣቢያ ለኢትዮጵያ ፊልም ተመልካቾች ለማቅረብ መሆኑን ተናግረዋል።

ሥራ አስኪያጇ እንደገለፁት፣ የኖላዊ ፊልም አምራች ሥራ የኢትዮጵያ ፊልሞችን ለካናል መርጦ ማቅረብ እና መሸጥ ነው። እንዲሁም የሚከፈተዉ ጣቢያ የተመረጡ የኢትዮጵያ ፊልሞች ብቻ የሚታዩበት መሆኑን የሚናገሩት ሥራ አስኪያጇ፣ ለተወሰኑ ወራት አዳዲስ ፊልሞችን በመከራየት ለማሳየት መስማማታቸዉን ገልፀዋል።
ድርጅቱ የሚከፍተዉ አዲስ የፊልም ጣቢያ ለኢትዮጵያ ፊልም ፕሮድዩሰሮች እስከ አሁን ሲከፈላቸዉ ከነበረው ክፍያ የተሻለና የሚገባቸዉን ክፍያ እንዲያገኙ እንደሚያደርግም ሐኒ ጠቁመዋል።

ስምምነቱ የኢትዮጵያ ፊልም ኢንድስትሪ እና የፊልም ፕሮድዩሰሮች እንዲሁም የፊልም ሥራ ላይ ለሚሳተፉ አካላትን ተጠቃሚ እንደሚያደርግና የተሻለ መነቃቃት እንደሚፈጥርም ሥራ አስኪያጇ አስረድተዋል።

ካናል ፕላስ በኢትዮጵያ ውስጥ የራሱን የቴሌቪዥን ጣቢያ ሲከፍት ኢትዮጵያዊ ሥም የሚኖረው ሲሆን፣ ስምምነቱ በቴሌቪዥን ማሳየት ብቻ እንደሆነና ኦንላይን (ዲጂታል) ሥርጭትን እንደማያካትት አስረድተዋል። በተጨማሪም አዳዲስ ፊልሞችን ለስድስት ወራት ብቻ የማሳየት ፈቃድ እንደሚሰጠው አስረድተዉ፣ ለዚህም የተሻለ ክፍያ እንደሚከፍል ሐኒ ተናግረዋል።

ከስድስት ወር በኋላ ግን ፕሮድዩሰሩ ለፈለገዉ ጣቢያ የመሸጥ መብት እንዳለዉ የገለፁት ሥራ አስኪያጇ፣ ይህ መሆኑ ለፊልም ፕሮድዩሰሮች ትልቅ ጥቅም አለው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፊልም ፕሮድዩሰሮች ማኅበር ጸሐፊ አርሴማ ወርቁ፣ ካናል የኢትዮጵያ ፊልሞችን ለተወሰነ ጊዜ መከራየቱ፣ በፊልም ኢንዱስትሪዉ ዘርፍ ለዉጥ እንደሚያመጣ ጠቁመዋል። ፕሮድዩሰሮችን ይበልጥ ተጠቃሚ ከማድረጉም ባሸገር፣ እስከ አሁን ከነበረው በተለየ የባለቤትነትን መብት ያስጠበቀ ነው ብለዋል።
አርሴማ አክለውም፣ ካናል በኢትዮጵያ ባህል ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳድርም ስምምነቱ በኢትዮጵያ የተሠሩ ፊልሞችን ብቻ በኪራይ እንዲያሳይ አድርጓል ብለዋል።

ኖላዊ ፊልም ፕሮዳክሽን በኢትዮጵያ ፊልሞችን የሚሠራና ፕሮድዩስ የሚያደርግ የኢትዮጵያ ፊልም አምራች ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ፊልም ፕሮዲዩሰሮች ማኅበር ጋር በቅርበት እና በጋራ የሚሠራ እንደሆነ ሥራ አስኪያጇ ተናግረዋል። በተጨማሪም ዘጋቢ ፊልሞችን እና የተለያዩ ምስሎችን (ቪዶዎችን) የሚሠራ ድርጅት ነው።
ካናል ፕላስ የፈረንሳይ ሚዲያ እና የክፍያ ቴሌቪዥን ድርጅት ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአፍሪካ፣ እስያ እና በአዉሮፓ የሚንቀሳቀስ ድርጅት ነው። ድርጅቱ በዓለማቀፍ ደረጃ 20 ሚሊዮን ተከታዮች አሉት።

በአዉሮፓ በፊልም አምራችነት፣ ፊልሞችን በማሰራጨት እና የቴሌቪዥን ድራማዎችን በማሳየት ከቀዳሚዎቹ የሚሰለፍ ነው። ካናል ፕላስን በባለቤትነት የሚያስተዳድረው ዓለማቀፍ ሚዲያ እና ኮምዩኒኬሽን ቡድን የተባለ ድርጅት ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 69 የካቲት 21 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here