በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የሚንቀሳቀሱ ሦስት ፓርቲዎች ግንባር ፈጠሩ

0
1081

በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የሚንቀሳቀሱት ቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቦዴፓ)፣ የጉምዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ቤሕዴን) እና የቤኒሻንጉል ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ ለሰላምና ዴሞክራሲ ድርጅት (ቤሕነን-ሰዴድ) ግንባር መሰረቱ።

ፓርቲዎቹ ጥር 1 እና 2/2012 የምርጫ ቦርድ ተወካይ ታዛቢዎች በተገኙበት በአሶሳ ከተማ ባደረጉት የጋራ ስብስባ፣ በጋራ ለመንቀሳቀስ ተስማምተው ተፈራርመዋል። ቀሪ መስፈርቶችንም አሟልው ለምርጫ ቦርድ ለማስገባት ዝግጅት ላይ እንደሆኑም አስታውቀዋል።

ግንባሩ ‹‹የቤኒሻንጉል ጉምዝ ዴሞክራሲያዊ ግንባር” የሚል ሥያሜ እንደተሰጠው የቤሕነን-ሰዴድ ሊቀመንበር አብዱልሰላም ሸንገል ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። አብዱልሰላም የግንባሩ ሊቀ መንበር እንዲሆኑ መመረጣቻውንም አስታውቀዋል። የቤሕዴን ምክትል ሊቀመንበር የሆኑትን ግራኝ ጉደታ ደግሞ የግንባሩ ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል።

አብዱልሰላም እንደተናገሩት፣ ምርጫ ቦርድ ባወጣው ማስታወቂያ መሠረትም ከየካቲት 30 በፊት አጠናቅቆ ለማስገባት ወደ አዲስ አበባ መጓዛቸውንም ተናግረዋል።
የቤሕዴን ሊቀ መንበር ደርጉ ፈረንጅ በበኩላቸው፣ ፓርቲዎቹ ግንባር ለመመስረት የተስማሙት በክልሉ ያለውን የፖለቲካ እንቅስቃሴ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ለማካሄድ በጋራ ለመስራት እንዲያመቻቸው እንደሆነ ተናግረዋል። ነገር ግን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መሰረታዊ ነፃነት አለ ለማለት የሚያስችል ሁኔታ የለም ብለዋል።

በክልሉ የሕግ የበላይነት ችግር በስፋት እንደሚስተዋል እና ሕገ መንግሥቱም እየተጣሰ እንደሆነም ተናግረዋል።
‹‹የክልሉ የፍትህ ተቋማት በሥራ አስፈፃሚው የፖለቲካ ጫና ስር የወደቁ ናቸው›› ያሉት ደርጉ ‹‹እንደማሳያም ዜጎች ያለ በቂ ማስረጃ በዐቃቤ ሕግ ይንገላታሉ፤ የካቲት 18/2012 አንድ የፓርቲያችን አባል በፖለቲካዊ እንቅስቃሴው ምክንያት በመተከል ዞን ወንበር ወረዳ ያለ በቂ ማስረጃ ታስሮብናል›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የሦስቱም ፓርቲዎች አመራሮች እንደገለፁት፣ በክልሉ ያለው ፖለቲካዊ አስተዳደር እንደ አማራጭ የሚንቀሳቀስ ፖለቲካ ፓርቲ እንዲኖር ባለመፈለጉ፣ መሠረታዊ የምርጫ ሥራዎችን ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዳንሠራ ተገድበናል ሲሉም ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቤንሻንጉል ሕዝብን ዋሽተዋል›› ያሉት ደግሞ የቦሮ ፓርቲ የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ ዩሐንስ ተሰማ ናቸው። ‹‹በአገሪቱ አለ የተባለው ለውጥ በቤኒሻንጉል የለም። ይልቁንም ተቃራኒ ነው›› ሲሉም ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ አሰምተዋል። ‹‹እኔም በፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ በመሳተፌ ምክንያት ከአሶሳ ዩኒቨርሲቲ መምህርነቴ ተባርሬ አሁን ለደኅንነቴም በመስጋቴ አዲስ አበባ እገኛለሁ። ሌሎች የፓርቲአችን አመራር እና አባለትም በእስር ላይ ይገኛሉ›› ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

በክልሉ በሦስቱም ዞኖች አስከፊ ግጭች እንደተከሰቱ እና የሐሳብ ነፃነትና መልካም አስተዳደር ጉዳይም ፈተና መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ ስላለዉ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ነፃነት ማጣት በተመለከተ ቦዴፓ ለምርጫ ቦርድ አቤቱታ ማቅረቡን የምርጫ ቦርድ የኮምዩኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በዚህም መሰረት ቦርዱ የክልሉ አመራሮች የቦሮ ፓርቲ አመራሮችን ለምን እንዳሰሩ ቦርዱ ድረስ ቀርበው ማብራሪያ እንዲሰጡ ምርጫ ቦርድ መጠየቁንም ገልፀዋል።

የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ፣ በክልሉ ስላለዉ የፖለቲካ ነፃነት ከክልሉ ፕሬዝዳንት ጋር በስልክ እንደተወያዩና በክልሉ ያለው የምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት ጉዳዩን በትኩረት እንዲከታተለው መደረጉን ሶሊያና ገልፀዋል። ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በተደረገ ውይይትም፣ የፓርቲ መሪዎች እንደተፈቱም ጨምረው ገልጸዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 69 የካቲት 21 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here