የአምራች ዘርፍ ተበዳሪዎች የብድር አመላለስ መሻሻል ማሳየቱን ልማት ባንክ አስታወቀ

0
828

ልማት ባንክ ከነበረበት ኪሳራ ወጥቶ በ2012 ግማሽ ዓመት 951 ሚሊዮን ብር ትርፍ ያስመዘገበ ሲሆን፣ ከዚህም ውሰጥ 73 ነጥብ ሰባት በመቶውን የሚሸፍነው ከኢንዱስትሪ ዘርፍ የተገኘ መሆኑን ባንኩ ይፋ አደረገ።

ባንኩ በኢንዱስተሪ ዘርፍ ለተሰማሩ ፕሮጀክቶች ካበደረው ብድር ባሳለፍነዉ ግማሽ ዓመት ሦስት ነጥብ ኹለት ቢሊዮን ብር ማስመለስ ችሏል። ባንኩ በተያዘው በጀት ዓመት በስድስት ወር ውስጥ ካስመለሳቸዉ ከግብርና ዘርፍ ከተሰማሩ ፕሮጀክቶች የተመለሰ ብድር 10 በመቶ ሲሆን፣ ይህም ዝቅተኛ መሆኑን የባንኩ ፕሬዝዳንት ኃይለኢየሱስ በቀለ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ብድሩ ከኢንዱስትሪው ዘርፍ በተሻለ ለመሰብሰቡ ባንኩ ለተበላሹ ብድሮች ተጨማሪ ገንዘብ ማፍሰስ ማቆሙ እና የከሰሩ ኢንዱስትሪዎችን በቅርበት በመደገፉ ምክንያት መሆኑንም ፕሬዝዳንቱ ይናገራሉ። ከዚህ በተጨማሪም የአሰራር ሂደቶችን በማሻሻል በተለይም በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ብድሮች እንዲከፈሉ ጥረት በማድረጉ፣ የኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሻለ እዳ እንዲመልስ እና የተቋሙም ትርፍ እንዲጨምር ማድረጉን ይናገራሉ። ያለአግባብ ተይዞ የቆየ የመጠባበቂያ ገንዘብ መጠን በመቀነስም፣ የባንኩ አፈፃፀም እንዲሻሻል ማድረጉን ተናግረዋል።

ልማት ባንክ ያለው አጠቃላይ የአጠራጣሪ ብድር መጠን 16.08 ቢሊዮን ብር ደርሷል። የባንኩ የተበላሸ ብድር መጠን ባለፈው ዓመት 40 በመቶ ድርሶ የነበር ሲሆን፣ በ2012 ግማሽ በጀት ዓመት ጠቅላላ የተበላሸ ብድር መጠን በመቶኛ 34.10 ዝቅ በማለት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀርም መሻሻል አሳይቷል።

እስከ ዛሬ በነበረዉ የብድር ፖሊሲ ክፍተት ኪሳራ ውስጥ ገብቶ እንደነበርና በአሁኑ ጊዜ ባንኩ ካለበት መሰረታዊ ችግር ለመውጣት የብድር ፖሊሲዉን ማሻሻሉን ፕሬዝዳንቱ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

‹‹የተበላሹ ብድሮችን ማስቆም የባንኩን አቋም ለመቀየር አማራጭ የሌለው ውሳኔ ነዉ›› ያሉት የባንኩ ፕሬዝዳንት ‹‹በ2012 የጀት ዓመት እስከ ሰኔ መጨረሻ ድረስ አዲስ ብድር መስጠት አቁመናል›› ሲሉ ጠቁመዋል።

በጊዜው ብድራቸውን ሳይከፍሉ የቀሩና ጥለው የጠፉ 71 ፕሮጀክቶች ላይ ምርመራ እያደረገ እንደሆነ ፕሬዝዳንቱ ጨምረው ገልጸዋል። ምርመራዉ እንዳለቀም ባንኩ አስተዳደራዊና ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድና ውጤቱንም ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ አያይዘው አስታውቀዋል። በተጨማሪም አንዳንድ ተበዳሪዎችና የባንክ ሠራተኞች ተመሳጥረዉ የመሥሪያ ቦታና እቃዎች ሳይዘጋጁ እንደተዘጋጁ አድርጎ በማቅረብ ብድር እንዲወጣ ያደረጉ እንዳሉ ጠቅሰው፣ በፍትሐ ብሔር ሕግ እንዲጠየቁ እንደሚደረግ አስረድተዋል።

በቤኒሻንጉል ጉምዝና በኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ በተፈጠረ ግጭት 38 የባንኩን ብድር የያዙ ፕሮጀክቶች መውደማቸውን ኃይለኢየሱስ አስታውሰዋል። ከባንኩ ገንዘብ ተበድረዉ በጊዜዉ ብድራቸዉን ያልከፈሉና ጥለዉ የጠፉ ፕሮጀክቶችንም ተረክቦ የማስተዳደርና ለሦስተኛ ወገን የመሸጥ ሥራ እየተሠራ ነው ያሊ ሲሆን፣ አይካ አዲስ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካም 4 ሺሕ 700 ሠራተኞችን የሚያስተዳድር ፋብሪካ ብድሩን ባለመክፈሉ ተቀብሎ ለሠራተኞች ደሞዝ እየከፈለ እያስተዳደረ እንደሆነና ለመሸጥ ጨረታ እንዳወጣ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

ባንኩ በጥቅሉ ለ2020 ፕሮጀክቶች ብድር የሰጠ ሲሆን፣ ከዚህ ዉስጥ 529 ያክሉ በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ ፕሮጀክቶች እንደሆኑ የባንኩ የኮምዩኒኬሽን ባለሙያ ናትናኤል ኃይለ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በጥቅሉ ለፕሮጀክቶቹ ያበደረዉ ብድር ክምችት 47.1 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ አጠቃላይ ያለው ሀብት 89.3 ቢሊዮን ብር ደርሷል።

ከብሔራዊ ባንክ 52 ሚሊዮን ብር ብድር እንደተበደረ እና 32 ቢሊዮን ብር መክፈሉን ፕሬዝዳንቱ ጠቅሰዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 69 የካቲት 21 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here