የምርጫው ዝግጅት እንዳይዘነጋ!

0
627

የ2012 አገር አቀፍ ምርጫ ለነሐሴ 23 ቀን ከተቆረጠለት ወዲህ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ የምርጫ ቦርድ ሽርጉድ በትንሹም ቢሆን እንደጨመረ ማየት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ይህ ዝግጅት ምርጫው በታቀደለት ጊዜ ይካሔዳል ወይ የሚለውን ጥያቄ በእርግጠኝነት ለመመለስ በቂ መሆኑ አሁንም አጠራጣሪ ነው፡፡ የፓለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር መብዛት ከምርጫ ቦርድ አቅም ውስንነት ጋር ሲዳመሩ ሁኔታው እጅግ አሳሳቢ እንዲሆን ያደርጉታል፡፡

የምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ እንደሚያሳየው ከጥር 16 እስከ መጋቢት 21 ያለው ጊዜ የምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላ የሚካሔድበት ነው፡፡ በዚህ ሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ቦርዱ 250 ሺህ ገለልተኛ የምርጫ አስፈጻሚዎችን ለመመልመል ዕቅድ የያዘ ቢሆንም ቀኑ መቁጠር ከጀመረ ከአንድ ወር ከአምስት ቀን በኋላም ምልመላው አልተጀመረም፡፡ የሚቀረው አንድ ወር ብቻ መሆኑ ሲታሰብ እና በዚህ ጊዜ ውስጥ የሚኖረው የሥራ ጫና ሲታሰብ ይህንን ለማድረግ ቦርዱ አቅም እንዳለው መጠራጠር የግድ ነው፡፡ አስፈጻሚ የሚሆኑ 250 ሺህ ሰዎችን ለመመልመል አንድ ወር በቂ ጊዜ እንዳልሆነ እሙን ነው፡፡

ሌላ የቦርዱ የጊዜ ሰሌዳ ባለንበት ጊዜ የሚካሔድ ብሎ ያስቀመጠው ነገር የምርጫ ክልል ቢሮዎችን ማደራጀት ነው፡፡ ይህም ከታህሳስ 22 እስከ መጋቢት 2 እንደሚካሔድ የታቀደ ነው፡፡ ይህ ሥራ በመካሔድ ላይ ያለ ሲሆን ጊዜው ሊጠናቀቅ የቀረው 11 ቀናት ብቻ ነው፡፡ ቢሮዎች ማደራጀቱ ያለመጠናቀቁ ቀጣይ ለሆነው የምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላ ሒደት በጊዜው ያለመጀመር በምክንያትነት የሚጠቀስ ነው፡፡ በመሆኑም ቢሮዎች ማደራጀቱ በታሰበለት ጊዜ የማይጠናቀቅ ከሆነ የምርጫ አስፈጻሚዎቹ ምልመላም ሆነ ከዚያ ቀጥሎ የሚመጡ ተግባራት በሙሉ ከዚህ ለበለጠ ጊዜ የሚጓተቱ ይሆናል፡፡

ምንም እንኳን የምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ ያለመጠበቅ ችግር በፓርቲዎች ተገቢውን ተግባር በጊዜ ባለማከናወን እና በሌሎችም ችግሮች ምክንያት የሚከሰት ቢሆንም ምርጫው በታቀደለት ጊዜ እንዲከናወን ቦርዱ ያወጣውን የጊዜ ሰሌዳ ሊከተል ይገባል፡፡ ይህ ደግሞ ከአሁኑ ካልተስተካከለ ተግባራቱ እርስ በእራሳቸው ላይ እየተደራረቡ የምርጫውን ቀን ከታሰበበት እንደሚገፉት ጥርጥር የለውም፡፡ በመሆኑም ምርጫ ቦርድ በፍጥነት ያወጣውን ሰሌዳ በትክክል ወደሚከተልበት ሁኔታ መምጣት አለበት፡፡

በዚህ ሳምንት እንደተሰማው ደግሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች በአዲስ አዋጅ ቁጥር 1162 መሰረት ለመመዝገብ የተሰጣቸው 42 ቀናት መጋቢት 3 ላይ የሚጠናቀቅ ቢሆንም በአገሪቱ ካሉት ፓርቲዎች ውስጥ አስፈላጊውን መረጃ አሟልቶ ለምዝገባ የቀረቡት ሁለት ፓርቲዎች ብቻ ናቸው፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እና የአረና ትግራይ ሉዓላዊነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲዎች ሲሆኑ ብልፅግና ፓርቲ፣ ኢዜማ፣ ኦነግ፣ ኦፌኮ፣ ኢዴፓ እንዲሁም ሌሎች ረጅም ጊዜ የቆዩ እና ትላልቅ ፓርቲዎችም አላቀረቡም፡፡

ፊርማዎችን ማሰባሰብ፣ ጠቅላላ ጉባኤ ማካሔድ፣ የአመራሮች አመራረጥ ዴሞክራሲያዊ መሆን፣ ሕገ ደንባቸውን በሕጉና አሰራሩ መሰረት ማሻሻል በአዲሱ አዋጅ መሰረት እውቅና ለማግኘት የቀረቡ መስፈርቶች ናቸው፡፡ እነዚህን ነገሮች ማሟላት በቀሩት 11 ቀናት ውስጥ ይጠናቀቃል ማለት ዘበት ነው፡፡

አገሪቷ ውስጥ ካሉት 106 ምርጫ ቦርድ የሚያውቃቸው ፓርቲዎች ውስጥ በተሰጡት 42 ቀናት ውስጥ ሁለት ፓርቲዎች ብቻ መረጃዎቹን ማቅረባቸው ፓርቲዎች ምን ያህል በሌላ ጉዳዮች ተጠምደው እንዳሉ እና ሕግን የማክበር ልምዳቸውም አናሳ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ በመሆኑም ሌላ ጊዜ መጨመር ሳያስፈልግ በቀረው ጊዜ ውስጥ ፓርቲዎች የሚጠበቅባቸውን አስፈላጊ መረጃ ለቦርዱ ማቅረብ እንዳለባቸው ግልጽ ነው፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ የምርጫው ጊዜ እንዲራዘም ቢወሰን ፓርቲዎቹ ከራሳቸው ውጪ ማንም ላይ ጣታቸውን ሊጠቁሙ አይገባም፡፡ ምርጫው አሁን በተያዘው የጊዜ ሰሌዳ እንዳይካሔድ የሚፈልጉ ፓርቲዎች ሆን ብለው ነገሮችን ለማስተጓጎል እንዳይሞክሩ ምርጫ ቦርድ ሁሉም ፓርቲዎች መረጃዎቹን በጊዜው ገደብ እንዲያስረክቡ ግፊት ሊያሳድር ይገባል፡፡ ይህንን በማያደርጉ ላይም ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል መሰረት ካለ ጉዳዩን ቦርዱ ሊቃኘው ይገባል፡፡

የፓለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት ሒደቶችም በየካቲት 30 እንዲጠናቀቁ ቀን የተያዘላቸው ቢሆንም ዘጠኝ ቀናት ብቻ እየቀሩ ፓርቲዎች ድርድራቸውን በጊዜው አጠናቀው ለምርጫ ቦርድ መረጃዎችን ማስገባት ላይ ሲዘገዩ ይታያል፡፡ በዚህ ረገድም ብዙ በመስመር ላይ ያሉ ጥምረቶች እንዳሉ ቢታወቅም የመጨረሻውን ቀን በመጠበቅ ይሁን ወይም በሌሎች ምክንያቶች በጊዜ እንደሚጠናቀቁ ምንም ማረጋገጫ እንደሌለ በጥምረት ላይ እየሠሩ ካሉ ፖለቲካ ፓርቲዎች መንደር የሚሰማው ወሬ ያመላክታል፡፡

ከእነዚህ የምርጫ ቦርድ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ችግሮች በተጨማሪ ሌሎች ችግሮችም የምርጫውን ጊዜ መጠበቅ ላይ አሉታዊ ጫና ሊያሳድሩ ይችላሉ፡፡ ከእንደዚህ ዓይነት ችግሮች መካከል በዋነኛነት የሚጠቀሰው የክልልነት ጥያቄዎች መፍትሔ ያለማግኘት ነው፡፡ በተለይ በደቡብ ክልል ውስጥ ያሉ የተለያዩ ዞኖች የክልልነት ጥያቄ ካነሱ አንድ ዓመት ያለፋቸው ቢሆንም ጉዳዩ ምንም ዓይነት ግልጽ የሆነ እልባት ወይም ትኩረት ያገኘ አይመስልም፡፡ ባለፈው ሳምንት እንዳየነውም በሕዝበ ውሳኔ ክልል መሆንን ከመረጠ ወራት የተቆጠሩት ሲዳማ ከደቡብ ክልል ጋር የሥልጣን ሽግግር እንዲደረግ ጥያቄ የሚያነሱ ወገኖች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ምላሽ ሳያገኙ ወይም መንግሥት በግልጽ ከእነዚህ የክልል ባለጥያቄዎች ጋር ተነጋግሮ መግባባት ላይ ሳይደርስ መቀጠሉ በምርጫው ላይ የሚያጠላው ጥላ አለ፡፡ ነገሮችን ከወዲሁ መልክ በማስያዝ ከምርጫው ጊዜ ቀደም ብሎ ሰላምና ደህንነትን ማስፈን የሚያስፈልግ መሆኑ ሲታሰብ በተለያዩ ቦታዎች የተነሱ የክልል ጥያቄዎችን አስመልክቶ ግልጽ የሆነ ስምምነት ላይ ከሕዝብ ጋር መድረስ ወሳኝ ነው፡፡

በአጠቃላይ ከላይ ለመመልከት እንደሞከርነው ከፊታችን ያለው አገራዊ ምርጫ ጊዜውን ጠብቆ በስኬት እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ ሚና መጫወት የሚገባቸው እንደ ምርጫ ቦርድ፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም መንግሥት ያሉ አካላት የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እያደረጉ ነው ለማለት የሚያስደፍር ሁኔታ የለም፡፡ በመሆኑም አሁን ባለው ሁኔታ ከቀጠለ የምርጫው ጊዜ በድጋሚ ሊተላለፍ እንደሚችል አዲስ ማለዳ ታምናለች፡፡ ይህንን ሁኔታ ቀይሮ ምርጫው በታቀደለት ጊዜ እንዲካሔድ ካስፈለገ የእነዚህ አካላት ተግባራት እጅግ ሊነቃቁ እንደሚገባም ጥሪ ታደርጋለች፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 69 የካቲት 21 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here