ኢትዮጵያ ሕዝቧ ከዳር ዳር ተሰናኝቶ፣ ለክብርና ሉዓላዊነቷ የቆመላት ዘመን ጥቂት አይደለም። ለዚህም ብዙ ጊዜ የአድዋ ድል በቀዳሚነት የሚነሳ ይሁን እንጂ፣ ሃምሳ ዓመት ያልሞላው የካራማራ ድል ከእነዚህ አስደናቂ ሕዝባዊ ድሎች መካከል የሚጠቀስ ነው። ይልቁንም ደግሞ ሠልጥኖ የተዘጋጀ ሠራዊት በመንግሥትና በገዢዎች ቀድሞ ባልተሰናዳበት ሁኔታ፣ የአገሩን ጥሪ ሰምቶ፣ የጦር መሣሪያው ያረጀ ነው ወይም ኋላ ቀር የሚለው ሳያሳስበው፣ ከጦርነት አውድማ ለመግባት ለሕይወቱ ያልሳሳ ሕዝብ፣ ድሉን እውነተኛ ሕዝባዊ ድል አድርጎታል።
የካቲት ወር ከያዛቸው አሳዛኝ እንዲሁም የድል ታሪኮች መካከል፤ በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር 1970 በዚሁ የካቲት ወር ላይ እውን የሆነው የካራማራ ድል ይጠቀሳል። ቀጣዩ የዝማሬ ግጥም ደግሞ አብሮ ይነሳል፤
‹‹ለአንድነቱ
ድሉ እንዲሰምር የነጻነቱ፣
ወጣ ወረደ…ሄደ ነጎደ ሠራዊቱ፣
አለኝ አደራ…የተቀበልኩት ከጀግኖች አውራ፣
እንድትኖር አገሬ ታፍራ ተከብራ፣
ብሎ ተነሳ ሕዝባዊ ሠራዊት…
ጉዞ ጀመረ…እየዘመረ
እንዲያበራ
የነጻነት ድል የአንድነት ጮራ፣
አውለበለበ የድል ባንዲራ…እንዲበራ
አገሬ
መመኪያ ክብሬ፣
አትደፈርም ዳር ድንበሬ
ውርሱ የአባቴ፣
ተደፍሮ ማየት አልሻም መብቴ፤
ብሎ ነጎደ ሠራዊቱ….››
ይህ ኅብረ ዝማሬ ከ42 ዓመታት በኋላ ባሳለፍነው ሐሙስ የካቲት 26 ቀን 2012 የኢትዮ ኩባ ሐውልት ስር ደምቆ ሲሰማ ነበር። ይኸው ዝማሬ ታድያ ቀድሞ የተሰማው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ጦር ሠራዊት ከሩስያ ባገኘው የጦር መሣሪያ ድጋፍ እንደ አዲስ ተደራጅቶ ወደ ውጊያ ሊገባ፣ በመስቀል አደባባይ ሰልፍ ባሳየበት እለት ነበር። ዝማሬው ያንን ዘመን አልፎ፣ የ1970 የካራማራ ድልን ተሻግሮ፣ ‹ተከፍሎልናል› ባሉ ወጣቶች ወደ ዛሬ ደርሷል።
የታሪክ ባለሞያ እና ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት አጭር ቆይታ፣ ትኩረት ሳይሰጣቸው ከቆዩ አገራዊ ድሎች መካከል የካራማራ ድል እንደሚጠቀስና፣ ለረጅም ዓመታት ትኩረት እንዳልተሰጠው ያነሳሉ። በኢሕአዴግ የሥልጣን ዘመን ብቻ ሳይሆን በደርግም ቢሆን እንደ ብሔራዊ በዓል የሚከበር አልነበረም። ነገር ግን በወራሪው ዚያድባሬ ሐሳብና እቅድ ልክ ሲታይ፣ የድሉ ትልቅነት ይጎላል።
ጥበቡ እንዳሉት የዚያድባሬ ጦር ወረራ ታላቋ ሶማሊያን ለመመሥረት የተደረገ ነበር። ይህም ካርታ አዋሽ ድረስ የሚዘልቅ ሲሆን፣ በደቡብና በምሥራቅም የኢትዮጵያን ሰፊ ግዛት የሚጠይቅ ነበር። ኢትዮጵያም ይህን ለማስጠበቅና ለማስከበር ነው ውጊያውን በሕዝባዊ ሠራዊት የተጋፈጠችው።
የሠራዊት አቅም ሚዛኑም ሲታይ የዚያድባሬ ጦር የበለጠ የተደራጀ እንደነበር መዛግብት ያስረዳሉ። በተለይ ጦሩ ኢትዮጵያን ሲወር፣ ደርግ ከንጉሥ ኃይለሥላሴ የተቀበለው 4 ክፍለ ጦር ብቻ ነበረው። እነርሱም በዝርዝር ሲቀመጡ፣ 1ኛ ክፍለ ጦር ክቡር ዘበኛ፣ 2ኛ ክፍለ ጦር ኤርትራ የነበረው፣ 3ኛ ክፍለ ጦር ምሥራቅ (ኦጋዴን) እና 4ኛ ክፍለ ጦር ደቡብ ነገሌ ቦረና የነበረው ነው።
ታድያ የአቅም ሁኔታ ታይቶና ከግጭትም ሰላም ስለሚሻል፣ የማሸማገል ጥረቶች ተደርገው ነበር፤ ግን አልተሳካም። የኩባ ፕሬዝዳንት ፊደል ካስትሮ በዚህ ማስማማት ላይ የተሳተፉ ሲሆን፣ ደቡብ የመን ላይ ለማሸማገል ጥረት በሚያደርጉበት ጊዜ ነው ዚያድባሬ በእብሪት ወረራውን ያደረገው። ያም ነው አንድም ፊደል ካስትሮ ያለምንም ክፍያና ጥቅም፣ ያለምንም የገንዘብ ጉዳይ ጣልቃ ገብነትና ተያያዥ ጥቅማ ጥቅሞች፣ የኢትዮጵያን ሠራዊት ለማገዝ የወሰኑት።
ቀጥሎ የወቅቱ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም፣ ሚያዝያ 4/1969 በብሔራዊ ቴሌቭዥን የእናት አገር ጥሪ መልዕክትንም አስተላለፉ። ይህንንም ተከትሎ 300 ሺሕ የሚጠጋ ሕዝባዊ ሠራዊት ታጠቅ ማሠልጠኛ ጣቢያ ተገኘ። ልምምዶች በፍጥነት እየተካሄዱና የሰንቅና የአልባሳት መሰል ዝግጅቶች በመደረግ ላይ ሳሉ፣ ለተከታታይ 10 ዓመታት ሲሠለጥን ሲታጠቅ የቆየው የዚያድባሬ ኃይል ሐምሌ 3/1969 3ኛ ክፍለ ጦር የነበረውን የኢትዮጵያን ሠራዊት በመግፋት፣ በምሥራቅ 700 በደቡብ 300 ኪሎሜትር ገፍተው ገቡ።
በጊዜው የኢትዮጵያ ትጥቅ ከሶማሊያ ጋር ሲነጻጸር እንደተባለው ኋላቀር መሣሪያ ነበር። ከዛም አልፎ ጦሩ ኢትዮጵያን ለመውረር መነሳሳቱን ያጠነከረለት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው የቀይና የነጭ ሽብር ጦርነቶች ናቸው። ጥበቡ እንዳለው፣ ወቅቱ ብዙ ወጣቶች የሚሰደዱበትና የተተራመሰ ጊዜ ነበር። የሶማሊያ ጦርም ሁኔታው ኢትዮጵያን ለመውረር አመቺ ሰዓት ነው ብሎ በማመን ነበር ወረራውን ያካሄደውና፣ በምሥራቅና በደቡብ የተወሰኑ ኪሎሜትሮችን አቋጦ የዘለቀው።
ኢትዮጵያ ድጋፍ ለማግኘት አገራትን ጠይቃለች። ድጋ የደረሳት ኋላ ላይ ቢሆንም፣ ምሥራቁ የሶሻሊት ጎራ ድጋፍ አድርጓል። በዛም ነው ታጠቅ ሲሠለጥን የቆየው ሠራዊት በአገር ወኔና በተሻለ ሥልጠና ታግዞ በአዲስ ወኔ ወደ ውጊያ የገባው።
ያኔ የጥበብ ባለሞያዎች ከሠራዊቱ ጎን ሆነው በማበረታታት አይረሴ ሥራን ሠርተዋል። ዛሬም ድረስ ከማይዘነጉ የዜማ ሥራዎች መካከልም ድምጻዊ መሐሙድ አሕመድ የተጫወተው የሚጠቀስ ነው፤
‹‹ለበጎ ከሆነ ለቁምነገር ጉዳይ፣
ጎረቤት ወዳድ ነን እንግዳ ተቀባይ፣
ግን አገራችንን ክፉ የሚያስባት፣
ቆራጥ ነን ልጆቿ አንወድም ጥቃት።
…ተከብረሽ የኖርሽው በአባቶቻችን ደም፣
እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይወደም!።››
ሻለቃ ባሻ አሊ በርኬ በ42ኛው የካራማራ ድል መታሰቢያ ላይ በነበረው መርሃ ግብር ባደረጉት ንግግር፣ ሕዝብ በምን ዓይነት የአገር ፍቅር ስሜት እንደዘመተ ያስታውሳሉ። እርሳቸውም ራሳቸው የእናት አገር ጥሪን ተከትሎ ከወለጋ ተነስተው ዋናውን ጦር የተቀላቀሉ ሲሆን፣ አልሞ ተኳሽ አዳኝ ነበሩ። እናም ሲያስታውሱ፣ በጊዜው አንዲት ጥይት ውድ በመሆኗ ዝም ብለው አይተኩሱም ነበር። ‹‹ለምን አትተኩስም ተብዬ ነበር። ግን ጠላት ሳላይ ወዴት እተኩሳለሁ ብዬ መለስኩላቸው።›› ሲሉ ተናግረዋል።
ይህም ሠራዊቱ ምን ያህል የጦር መሣሪያ እጥረት እንደነበረበት አንዱ ማሳያ ነበር። ያ ግን ወደኋላ ያስቀረውና በአገሩ ተስፋ ያስቆረጠው ሠራዊት አልነበረም። ቆይቶ ከሩስያ ድጋፍ በኋላ ግን ሕዝባዊ ሠራዊቱ በተጨማሪ 9 ክፍለ ጦሮች ተዋቅሮ፣ ወደ 13 ክፍለ ጦር አደገ። የኩባው ፊደል ካስትሮም 18 ሺሕ ያህል የእግረኛ ተዋጊና አስፈላጊውን የሜከናይዝድ ኃይል ከሕክምና ባለሞያዎች ጋር ላኩ። ደቡብ የመንም እስከ 2000 የሚደርስ ጠንካራ የመድፈኛ ብርጌድ ድጋፍ አደረጉ።
የካቲት 23/1970 የአድዋ ድል 82ኛ ዓመት ላይ፣ እለት የኢትዮጵያ ጦር በጭናቅሰን እና በቆሬ በኩል ወደ ጅግጅጋ የተጠናከረ ቅንጅታዊ የማጥቃት ዘመቻ ከፈተ። ከጅግጅጋ በምዕራብ በኩል ካለው ካራማራ ተራራ ላይ ማዘዣ ጣቢያውን ለመሥራት የሞከረው የዚያድባሬ ጦር በአንጻሩ ሳይሳካለት ቀርቶ ማፈግፈግ ጀመረ። የካቲት 26/1970 ላይም ጦሩ አገር ለቅቆ ወጣ።
ጥበቡ በለጠ በጦርነቱ ብዙ ሰው እንዳለቀ ያወሳሉ። አሜሪካ ከዚያድባሬ ጦር ጋር የነበረች ሲሆን፣ የመሣሪያ ድጋፍም አድርጋለች። በሌላ በኩል ሩስያ ደግሞ ኢትዮጵያን በመሣሪያና በማማከር በኩል ድጋፍ ሰጥታለች። ‹‹በዚህ ሁሉ አጣብቂኝ ውስጥ የተገኘ ድል ነው።›› ያለው ጥበቡ፣ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የኩባ እና የደቡብ የመናውያን ዜጎችም ድጋፍ የማይዘነጋ እንደነበር ይጠቅሳሉ።
ዛሬስ?
ኮረማሽ የጉዞ ማኅበር እና ማይክ መላክ፣ ከየኢትዮጵያ የኩባ ወዳጅነት ማኅበር እንዲሁም ከኩባ ኤምባሲው ተሳትፎ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት የዚያድባሬ ድል 42ኛ ዓመት መታሰቢያ በተደረገበት ቀን በስፍራው የመንግሥት ባለሥልጣናት አልተገኙም። ይሁንና በርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪ፣ በጊዜው ተዋጊ የነበሩ ወታደሮችና የሠራዊቱ አባላት፣ በጦርነቱ ወላጆቻቸውን ያጡና በሕጻናት አምባ ያደጉ ልጆች እንዲሁም የጉዞ አድዋ ተጓዦች ተገኝተዋል።
ከፕሮግራሙ አዘጋጆች መካከል የሆኑት ማይክ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ በድሉ ተሳታ የነበሩ ጀግና የሠራዊት አባላትና ወታደሮች ተዘንግተዋል። የአገር ባለውለታዎች ተረስተዋል ይላሉ። ‹‹ዓላማችን ዳግማዊ ዓድዋን ማሰብ ነው። አድዋ እንዴት እንደተከበረ አይተናል፤ ያ የአያቶቻችን ድል ነበር። ይህ ደግሞ የአባቶቻችን ድል ነው።›› በማለት ተናግረዋል። አያይዘውም ተነሳሽነቱ ከአዘጋጆቹ እንደመጣና መንግሥት ፈቃዱን እንደሰጠ፣ ወደፊትም ብሔራዊ የድል ቀን ሆኖ እንዲከበር ጥረት መደረግ እንዳለበት ጠቅሰዋል።
‹‹ኢትዮጵያ የመስዋዕትነት አገር ናት። ብዙ ተከፍሎባታል።›› ያሉት ጥበቡ፣ እነዚህ ጦርነቶች አገር እንዴት እንደቆመች ማሳያ ስለሆኑ በትምህርት ውስጥ መካተት አለባቸው፤ ተማሪዎች ቢማሯቸው፣ ኢትዮጵያ ምን ያህል እንደተከፈለባት ያውቁበታል ባይ ናቸው።
እንደ ዛሬ ኢትዮጵያ በብዙ ክልሎች ሳትመደብ በፊት፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እስከ ሶማሌ ድረስ የእኔ ነው ብሎ ከያለበት ወጥቶ ሕይወቱን ሰጥቶ ያስከበረበት ነው ይላሉ።
‹‹እናም ይሄ የእገሌ ነው ያ የእገሌ ነው የሚባል ቦታ ሳይሆን፣ ሁሉም የኢትዮጵያውያን ደም የፈሰሰበት ነው። ካራማራም ከአድዋና ከፋሽስት ወረራ ያላነሰ ትልቅ በዓል ነው። የግድ መሥሪያ ቤቶች ይዘጉ ባይባልም እንደ የካቲት 12 በመላው አገር በተለይ በምሥራቁና በደቡብ የኢትዮጵያ ክፍል፣ ትውልድ እንዲያውቅና አባቶችም እንዲያታወሱ ቢደረግ የበለጠ በትውልድ ውስጥ እንዲታወቅ ማድረግ ይቻላል።›› ሲል ሐሳቡን ሰጥቷል።
ቅጽ 2 ቁጥር 70 የካቲት 28 2012



