‹‹የሚያጣላን የፖለቲካ ታሪክ ሳይሆን የታሪክ ፖለቲካ ነው››

0
1522

ትውልድና እድገታቸው አዲስ አበባ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ዘርፈሽዋል እንዲሁም ገዳመ ሲታውያን ማርያም ጽን ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። ኹለተኛ ደረጃ ደግሞ ምሥራቅ አጠቃላይ። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተው በታክ የመጀመሪያ እና ኹለተኛ ዲግሪያቸውን ይዘዋል።
በዲላ ዩኒቨርስቲ እንዲሁም በአወልያ ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመምህርነት አገልግለዋል። ለሦስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በቱርክ እየተከታተሉ ሲሆን፣ በተያያዘ በቱርክ የቴሌቭዥን ጣቢያ ፖለቲካ በመተንተን እንዲሁም የተለያዩ ፕሮግራሞችን በማዘጋት ሠርተዋል። የታሪክ አጥኚና ፖለቲከኛ ናቸው፤ ኢብራሂም ሙሉሸዋ።

በክርስትና እና እስልምና እምነት ተከታይ ወላጆች መካከል የተወለዱት ኢብራሂም፣ አሁን ባለትዳርና የኹለት ልጆች አባት ናቸው።ብዝኀነትን ከመረዳት አልፈው ለማስረዳት የረዳቸውም በብዝኀ እምነትና ባህል ውስጥ ማደጋቸው እንደሆነ ያምናሉ። በኢትዮጵያ እስልምና ታሪክና በጥቅሉ የታሪክ አረዳድ ላይ፣ እንዲሁም በፖለቲካው ኹነቶች ዙሪያ ከአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።

ነገ እሁድ የካቲት 29 የሴቶች ቀን ተብሎ ይታሰባል። በዚህ እንጀምር፣ በኢትዮጵያ ታሪክና ፖለቲካ የሴቶች ተሳትፎ ምን ይመስላል?
ቃሉን መጠቀም ይኖርብኝ ከሆነ፤ ፌሚኒስት ነኝ ብዬ አምናለሁ። ሴቶችን ዝቅ አድርጎ ማየትን እጠላለሁ። በዛ ላይ የሴቶች ተሳትፎ ትንሽ ነው የሚለውን በፍጹም አልቀበልም። የሴቶች ተሳትፎ በታሪካችንም ሆነ እስከ አሁን ትንሽ ሆኖ አያውቅም። ግን የሴቶችን ተሳትፎ እውቅና መስጠት ነው የሌለው። ኹለቱ ይለያያሉ።

በለመድነው የማኅበረሰባችን ቤተሰብ ውስጥ አባት ሥራ ሄዶ መጣ ይባላል። እናት ጓዳ ስትገባ ሥራ ሄደች አይባልም፣ ቤት ቁጭ ብላ ትውላለች ነው የምትባለው። ልጅ የምታበላ የምታሳደግው፣ ቤተሰቡን የምታበላ የምታጠጣው በሙሉ እሷ ናት። እንደውም ‹ሥራ› ተብሎ የሚተረጎምበት መንገድ በጣም የተሳሳተ ነው ብዬ አስባለሁ።
ስለዚህ አንደኛው የሴቶች እውቅና ያለማግኘት ነው። ከዛ ጋር ተያይዞ አይችሉም፣ አይሠሩም ተብሎ የሚመጣ የሥነ ልቦና ተጽእኖ አለ። ‹አይችልም!› እየተባለ ያደገ ልጅ አይችልም። ትምህርት ቤት ከወንድና ከሴት ቢመረጥ ወንዱ ይላካል። ይህም ማኅበረሰብ የገነባው ነገር ነው እንጂ የሴቶች መቻልና አለመቻል ጉዳይ አይደለም።

ሌላው ሴቶች ይህን ሁሉ አልፈው ስኬታማ የሚሆኑ ናቸው። እርግጠኛ ነኝ አንቺ ቤትሽ ስትገቢ ወደጓዳ ትሄጃለሽ፣ እኔ ግን አልገባም። የሴቶች ችሎታን ከሚያሳየኝ አንዱ ይሄ ነው። ጊዜያችሁ እንዴት እንደሚበቃ ይገርመኛል። ሴት ልጅ ሁሉም ሰው ይገመግማታል። እኔ`ኮ ንጹህ ባልሆን ሰው ላይገመግመኝ ይችላል፤ አንቺን ግን ይገመግምሻል። ይህን ሁሉ ይጠበቃል። ልጆች መያዝ፣ ቤተሰብ መንካባከብ ይጠበቃል።

ያው አሁን ወንድ ቤት ውስጥ መሥራት አለበት ይባላል፤ እኔ ይህ ከመሸንገያ ያለፈ አይመስለኝም። በራሴም ላይ ስለማየው። እና የሴት ልጅ ጥንካሬ የሚገርም ነው፤ በጣም። ማኅበረሰባችንም ውስጥ ከድሮ ጀምሮ በፖለቲካም እነ እቴጌ ጣይቱን፣ እነ ኢሌኒ፣ በሙስሊሙ እነ ድሎምበራን ማንሳት ይቻላል። ትልቅ አስተዋጽኦ ያላቸው ናቸው። በጦርነትም የመጀመሪያ ተጎጂ ሴቶች ናቸው። የኢትዮጵያ ታሪክ የሴት ጀግና አጥቶ አያውቅም። ግን እንዳልኩት እውቅና የማግኘት እና ያለማግኘት ጉዳይ ነው።

ስለታሪክ ስናነሳ፣ ለታሪክ ያለን አረዳድ ከየት የሚመነጭ ነው?
በመጀመሪያ ደረጃ ታሪክ ምንድን ነው ነው። የሰው ልጆች ሁሌ ከታሪክ ጋር ይገናኛሉ። ስለ እናት አባቶቻቸው ይጠይቃሉ። በዚህ መሠረት ታሪክን በኹለት ልንመድበው እንችላለን። አንደኛ ያለፈ የተደረገ ክንውን ነው። የሞተ እንደማለት ነው። በኹለተኛ ደረጃ ግን ስላለፈው የምናወራበት የትምህርት መስክ ነው።
የሰው ልክ በተፈጥሮው ስላለፈው ማወቅ ይወዳል፤ ስለልጅነትሽ ብታውቂ ደስ ይልሻል። ስለዚህ የማንነታችን አንድ አካል ነው። ለምሳሌ አንዳንድ ሰው ‹ምነው ያለፈውን ብንተወውስ!› ይላል። ግን አይተወንም። ደግሞ ጥቅምም አለው። ለምን ጋዜጠኛ ሆንሽ ብልሽ ወደኋላ ሄደሽ ነው የምትነግሪኝ። አንቺን አሁን ላይ ለመረዳት የመጣሽበትን መረዳት ያስፈልጋል። ስለዚህ ታሪክን ማምለጥ አይቻልም።

የተለያዩ ታሪክ እይታዎችና አመለካከቶች አሉ። ከዚህ ጋር የተያያዘ ሌላው ነጥብ፣ ስለታሪክ ያለን አመለካከት ቅርጽ የሚይዘው አሁን ባለን አስተሳሰብ፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊና መሰል ሁኔታ ነው። ለምሳሌ በጣም ሐይማኖተኛ ሰው የሚያስደስተው ታሪክ ሐይማኖት ቀመስ የሆነ ነው። አንድ የብሔር አቀንቃኝም ስለራሱ ብሔር ወደኋላ ታሪክ ማወቅ ይፈልጋል። ስለዚህ አሁን ያለን አቋም የታሪክ አረዳዳችን፣ የታሪክ አመለካከታችን ላይ ተጽእኖ አለው።

ከዚህ ጋር በተገናኘ ብዙ ጊዜ እንደምለው ታሪክ አይደለም የሚያጣላን፣ እኛ አሁን ስለታሪክ ያለን አቋም ነው። ሁሉም ሰው የራሱን አቋም ይዞ ነው የሚያወራው። ይህ ማለት በተለይ እንደ እኛ ብዝኀነት ያለበት አገር ላይ፣ በታሪክ አባቶቻችን የተጣሉትንም እንዲሁ ነው የምንተረጉመው።

ሁሉም ሰው ግን ከታሪክ ጠቃሚ ኃይል ይፈልጋል። እንደ አገር ከታሰበ ስለአገር ታላቅነት፣ በሐይማኖት ካሰብሽ ስለሐይማኖትሽ ትልቅነት፣ ብሔርም ከሆነ ወይም ቤተሰብም ቢሆን፣ እንደዛው ነው። ሰው አያቴ ገዳይ ነው አይልም፣ አያቴ ጀግና ነው ይላል። አያቴ ፈሪ ነው አይልም፤ አያቴ ነገር አይወድም ነው የሚለው። ሌላው ላይ ሲሆን ደግሞ በተቃራኒው ነው። ከገደለ ጀግና አትይውም፤ ጠላት ነው፤ አረመኔ ገዳይ። እነዚህን ነገሮች በመረዳት ነው ታሪክ ላይ መረዳዳት የሚመጣው።

ለማመዛዘን ሊረዳን በሚችል ሁኔታ የኢትዮጵያ ታሪክ ምን ያህል ተጽፏል?
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ1950ዎቹ ነው የታሪክ ትምህርት ክፍል የተመሠረተው። በዛም የኢትዮጵያን ታሪክ ለመጻፍ ተሞክሯል። በተለያየ መንገድም ኢትዮጵያን ለማጥናት ተሞክሯል። ብዙ ጥናቶች ተደርገዋል፣ በውጪም በእኛም። አንደኛው ይሄ ነው። ኹለተኛ እንዴት ነው የተጠኑት ስንል፤ ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ተጽእኖው በዚህም ላይ ይታያል።

ኢትዮጵያ መጀመሪያ ታሪኳን ስትጽፍ ማን ነች ብለን ማየት አስፈላጊ ነው። ዘመናዊት ኢትዮጵያ በአጼ ምኒልክ ስትመሠረት ቀመር ወጥቶላታል። የክርስትያን አገር፣ የሰሜኑ ባህልም ኢትዮጵያ ተብሏል። ታሪካችን በመንግሥት ደረጃ ሲጻፍ ይህን ማረጋገጥ ነበር የያዘው።

በፊት የነበረው ‹አዲስ ነገር› የተሰኘ መጽሔት ላይ፣ ‹የታሪካችን ታሪክ› የሚል አንድ ጽሑፍ አስነብቤ ነበር። በዛም እንዳነሳሁት፣ መጀመሪያ ኢትዮጵያን ተረጎሙ፣ ቀጥለው የኢትዮጵያን ታሪክ ለማወቅ በንጹህነት አይደለም የተጻፈው፣ ይህንን ትርጓሜ ማረጋገጥ ነው የተጻፈው። እንዴት የክርስትያን አገር እንደሆነች፣ እንዴት ሴማዊ እንደሆነችና ወዘተ። ብዙ ጥናቶች እዛ ላይ ነበር ያደረጉት።

ይህን ለማድረግ ሦስት መንገድ ተመረጠ እላለሁ። አንደኛ መረጣ ነው። እየተመረጠ የክርስትያንና የሰሜን ባህል ቀረበ። ዛሬ ታሪክ ሲባል አክሱምና ላሊበላ ወይም ጎንደር በአእምሯችን ይመጣል። አሁን በትግል ሐረርን እንጨምራለን። እንጂ ተመርጦ የማን ታሪክ ለመጻፍ እንደሚሞከር ታያለሽ። ኹለተኛው መተው ነው። የደቡብና የአፋር፣ የሶማሌ የጋምቤላና ታሪክ የለም። ከዛ ሦስተኛው ደግሞ ማጥላላት ነው።

ለምሳሌ ሊዘለሉ የማይችሉ ግን ክርስትያን ተብላ በተቀረጸች ኢትዮጵያ ተቃራኒ የሆኑ ኃይሎች አሉ። አንደኛው ግራኝ አሕመድ ነው። እሱን መዝለል አይቻልም፤ ተጽእኖ ስላለው። ስለዚህ እሱን ታጠለሻለሽ። ቤተክርስትያን ያፈረሰ፣ ሰዎችን አስገድዶ ሐይማኖት ያስለወጠ፣ እንዲሁም ዮዲት ጉዲት ይባላል። ይህ በማጠልሸት ይቀርባል። የእነዚህ ታሪክ የሚቀርበው ኢትዮጵያ የደረሰባትን በደል ለማሳየት እንጂ የእነርሱን ታሪክ ለማሳየት አይደለም።

በእንደዚህ ዓይነት አመለካከት የተቀረጸ ታሪካዊ አረዳድ ይዘን ነው ያለነው። ይሄ ነገር መሻሻል አለው፤ አዎን። በተለይ በ1970 እና 80ዎቹ ላይ የኤርትራ፣ የትግራይ፣ የኦሮሞ ብሔርተኞች አዲስ ነገር ይዘው መጡ፣ ኢትዮጵያን ያለመቀበል፣ የራሳቸውን እየመረጡ በማቅረብ። ለምሳሌ ከኢትዮጵያ በፊት ኦሮሚያ እንዴት እንደነበረች።
ኹለቱም የሚጎድላቸው ነገር አለ። በአንደኛው ኢትዮጵያ ብለን የሳልናት ውስጥ ሌሎችን እንዳናይ ብዝኀነት እንዳይኖር ተደርገናል። በኹለተኛው ደግሞ አብሮነታችን እንዳለ ተተወ፤ ከታሪክ ወጣ። አሁን እንግዲህ ፈተናው ኹለቱን የታሪክ አረዳዶች እንዴት እናስታርቅ ነው። እንደ እኔ አመለካከት ኢትዮጵያውያን ከሌላው ሕዝብ የበለጠ ጻድቅ አይደሉም፣ ከሌላው ሕዝብ የበለጠ አውሬ አይደሉም። ተዋግተናል፣ ተጣልተናል፣ ተዋልደናል ተጋብተናል። ይህንን የሚያሳይ የታሪክ ትርክት ግን አልገነባንም። በማስተዋል አእምሯችን ውስጥ ያለችው ኢትዮጵያ አሁንም ቢሆን እንቅፋት እየፈጠረች ነው። አመለካከታችን ማለት ነው።

ግን የማን ሥራ መሆን ነበረበት፣ ዘመናዊ የታሪክ ጥናትና አጻጻፍ አጭር እድሜ ያለው ከመሆኑ አንጻር?
የገዢው መንግሥት።

ያኔ ንቃቱስ ምን ያህል ነበር ብዬ ነው። ሁሉም ነገሥታት በየጊዜው ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ የየራሳቸውን መንገድ ተጠቅመዋል። በቀደሙት ነገሥታት አውድ ሆነን ስናስበው፣ አሁን ላይ ሆነን እንዲህ ማድረግ ነበረባቸው ማለት አያስቸግርም?
እኔ እንደውም ስለእነርሱም አይደለም የማወራው። እኛ ታሪክ ስናወራ አሁን ስላለው ሁኔታ ነው የምናወራው። እኔ እነሱን እየወቀስኩ አይደለም። ግን አሁንም አመለካከታችን ያው ነው። አንድነት የሚለው ሰውዬ በእርሱ የአስተሳሰብ ጠርዝ ውስጥ ሙስሊም የለም። እሱ አእምሮ ውስጥ ኦሮሞ የለም። ምክንያቱም ይህን ካላወራን መፍትሔ የለም። አሁንም ቢሆን ያው ነው።

ሰውኮ አስቦት ላይሆን ይችላል። ትውልድ የስርዓተ ትምህርት ውጤት ነው። ባለፉት 27 ዓመታት የመጣው የትምህርት ስርዓት ብሔርተኝነት መጣ፤ አሁን በየክልሉ ያለ ልጅ ክልሉን ነው የሚያስበው።

የሚያሳዝነው እነዚህን ተነጋግረን ተወያይተን ከመጻፍ ይልቅ፤ ሁላችንም ጉድጓድ ውስጥ ገብተን የየራሳችን ነው የምንጽፈው። ይህም አደገኛ ነው። እኔ የትም ቦታ ነው አሁን የማወራውን የማወራው። መፍትሔ ይገኛል ብዬ ስለማስብ ነው። ዋናው አረዳዳችን ነው።

ክፉ ሰው የለም፣ ክፉና የሚያራርቅ አስተሳሰብ ግን አለ። እና በዚህ የተነሳ ያለፈው አሁንም እኛ ላይ ተጽእኖ አለው። አሁንም ስለኢትዮጵያ አረዳዳችን ላይ ተጽእኖ አለው። አሁን ደግሞ የሚብሰው ተቃራኒውም ተጽእኖ መፍጠር ጀምሯል። ጽንፍ የወጣ የታሪክ አረዳድ አለ። ይህን ማስታረቅ ይቻላል፤ ቅንነት ካለ። እውነተኛ መንገድ ካስቀመጥን፣ አንድ የምንሆንባቸውን መንገዶች ካመጣን፣ የምንለያይባቸውን ነገሮች እውቅና ከተሰጣጠን፤ አሁንም መንገድ አለ።

ችግሩ ግን ፖለቲካው ራሱ እየረበሸን ነው። የሚያጣላን የፖለቲካ ታሪክ ሳይሆን የታሪክ ፖለቲካ ነው። ስለታሪክ የምንቀርጸው ፖለቲካ ያጣላናል እንጂ፣ የፖለቲካ ታሪክማ አንዱ ገደለ አንዱ ተገደለ ነው፤ አለቀ። አያትሽ አያቴን ገድሎታል፣ ስለዚህ ምን ላድርግ ነው የምለው። እኔ ነበርኩ? በቃ! ግን አያትሽ አያቴን በመግደሉ ዛሬም እኔ እበቀላሁ ከተባለ ጥል ይመጣል። ይህንን እንዴት እናቆመዋለን ነው። አንደኛው በተለይ የታሪክ አረዳዳችን ላይ ግልጽ የሆነ ውይይት ማድረግ ነው።

እንዳሉት ታሪክ እየተመረጠ፣ እየተተወና እየጠለሸ ሲጻፍ የነበረበትን ዘመን ትተን፣ ከዛ በኋላ በነበረው ጊዜ የኢትዮጵያ የእስልምና ታሪክ ምን ያህል ቦታ አግኝቷል?
ኢትዮጵያ ውስጥ ሁላችንም የምንሳሳትበት ኹለት ዓይነት ዝምድና አለ። አንደኛው የጎንዮሽ ነው፤ የማኅበረሰብ ግንኙነት። በዚህ ላይ አንድም ቀን ችግር ኖሮብን አያውቅም። ሙስሊም ከክርስትያን ጋር ተዋልዷል፣ ተጋብቷል፣ እየኖረ ነው፣ ማንም ይህን አይፍቅም፤ ማንም ለማንም ክፉ አይደለም። ኹለተኛ ግን ከላይ ወደታች ግንኙነት አለ። በዚህም መንግሥት ከሙስሊሞች ጋር እና ከክርስትያኖች ጋር ያለው ግንኙነት አንድ አይደለም።

ሙስሊሞች ተጨቆንን ሲሉ ክርስትያኖች ጨቆኑን ማለት ግን አይደለም። መንግሥት እኔን ጨቁኖኛል ነው። ግን አንድ የተፈጠረ አስተሳሰብ አለ፣ ሙስሊሙ ይሄ መንግሥት የክርስትያን ነው በሏል፤ ክርስትያኑም የእኔ ነው ብሏል። ይህን ማስወገድ አለብን። ሙስሊሞች ገዢው ላይ ነው ጥያቄ ያላቸው። ስለዚሀ ክርስትያኖች የአገዛዙ ጠበቃ አይደሉም። መጀመሪያ ይህን አመለካከት ማስወገድ ነው ያለባቸው። ሙስሊሞችም ደግሞ ክርስትያኞችን አይደለም መጠየቅ ያለባቸው፣ መንግሥትን ነው።

አሁን አዲስ አበባ የሁሉም ነች ይባላል። ግን ውሸት ነው። አዲስ አበባ የሙስሊሙ አይደለችም። ይህን ግን ያደረግሽው አንቺ ነሽ? መንግሥት ነው። መንግሥት አመለካከትና ታሪክ ወዘተ ነው። ስለዚህ ሁላችንም አንዳችን አንዳችንን ስላልበደልን፣ ገዢውን መንግሥት እንዴት እንለውጥ በሚለው፣ መመካከር ይቻላል። እንዴት እኩል የሆነ የሀብት ክፍፍል ይኑር፣ ተጠቃሚነታችን እንዴት እኩል ይሁን፣ እንዴት ሀብታችንን በጋራ እንጠቀም?

ስለዚህ ይህን መለየት ያስፈልጋል፤ መጀመሪያ። አለበለዚያ ማኅበረሰብና ማኅበረሰብ ተጣላ የሚል ትርክት ከተነሳ፣ እንደ አገር አንቆምም። በኢትዮጵያ የሙስሊም ክርስትያን ግንኙነት ችግር የለበትም። ሙስሊም ግን ከገዢው ጋር ያለው ግንኙነት ትክክል አልነበረም፤ ጭቆና እና ማግለል ነበር። አሁን ግን ክርስትያኑ ራሱን የገዢው ጠበቃ አድርጎ ‹አይ አልጨቆነም1› ይላል። ይህንን ካላስወገድን፣ ዛሬም ፖለቲከኞች ይህን ነው የሚጠቀሙበት።

ሌላው የኢትዮጵያ መንግሥት በሕግ ደረጃ የተቀየረ ነው፤ ከአብዮቱ በኋላ። ለምሳሌ የመንግሥት ሐይማኖት የለም። አሁንም ግን የሚመኙ ሰዎች እያየን ነው፤ አሉ። ኢትዮጵያ የክርስትያን ደሴት ነች፣ ክርስትያንነቷን እንመልሳለን የሚሉ ሰዎች አሉ። ይህ እንደ አንድ የፖለቲካ አመለካከትና ሙግት ከሆነ ችግር አይኖረውም፣ መጥተው እኔን ክርስትያን አደርግሃለሁ ካላለኝ በቀር። ነገር ግን ጽንፈኛ የሆኑ ኃይሎች ሰዉ ዘንድ የሚያደርሱት ተጽእኖና የሚፈጥሩት መከፋፈል እየጠነከረ ከመጣ አደገኛ ነው። እኔ ሙስሊም ነኝ፣ ኢትዮጵያ የአሕመድ ግራኝ ነች የሚልም ሊመጣ ይችላል።

እንዲህ ያሉ ጽንፎች ሊኖሩ ይችላሉ። ግን መደበኛ የሚባለውን ቡድን (Mainstream) መጠበቅ ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ ታሪክንም ከእስልምና አንጻር ስናየው፣ ኢትዮጵያ ሙስሊሞች የሚኖሩባት አገር ብቻ አይደለችም። ኢትዮጵያ ልክ ክርስትያኖች ግዛት እንደነበራቸው ሙስሊሞች ግዛት የነበራቸው አገር ናት። ሙስሊሞች የራሳቸው የፖለቲካ አመለካከት ነበራቸው። ለምሳሌ ክርስትና ሸዋ ከመድረሱ በፊት እስልምና ነው ሸዋ የደረሰው። ሸዋ ሱልጣኔት ሰሜን ሸዋ ላይ ራሱን የቻለ መንግሥት ነው፤ አገር በቀል።

ከዛ በኋላ እነኢፋት፣ አዳል፣ የሙስሊም ጊቢ ስቴት፣ እነ ሐረር ጅማ ራሳቸውን የቻሉ የሙስሊም ስቴቶች ናቸው። ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ እኔ የምለው ብዝኀ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ብዝኀ መንግሥትና ታሪክ አለ። ታሪካችንም ብዝኀነት ያለው ነው። እንዳልኩሽ ግን እየተመረጠ ስለሚነገረን፣ ኢትዮጵያ የምትባለው አክሱም ጀመረች፣ ከዛ ላሊበላ ከዛ ጎንደርና ከዛ ዘመናዊት ኢትዮጵያ መጣች ነው። ይህ አንድ መስመር ነው።

ይህ የኢትዮጵያ ታሪክ አንድ ትልቅ ክፍል ነው። ኢትዮጵያ ግን ይህ ብቻ አይደለችም። እኔኮ የሙስሊም ሱልጣኔት ብዬ ሸዋ፣ ኢፋት፣ አዳል ሐረርን ነው የማውቀው ልል እችላለሁ። ይህኛው ኢትዮጵያ ይህኛው ኢትዮጵያ ያልሆነ የሚባል ነገር የለም። አልያም በአንድ ነገር መስማማት አለብን። ወይ እነዚህ በሙሉ የኢትዮጵያ ሥልጣኔዎችና የኢትዮጵያ ታሪክ አካል ናቸው ብለን ማመን። ወይም ደግሞ ዘመናዊት ኢትዮጵያ ከምኒልክ በኋላ ነው የመጣችው፣ እኛ ከዛ በኋላ አንድ የሆንበትን አገር ኢትዮጵያ ማለት። ከኹለት አንዱ ነው።

አሁን ያለው የታሪክ አረዳድ ግን ከምኒልክ በኋላ የመጣውን ኢትዮጵያ ይቀበልና፤ ከዛ በፊት የነበረውን ቀጭኑን ይከተላል። ይህ ስህተት ነው። ስለዚህ ሙስሊሞች አገር በቀል ብቻ አይደሉም፣ አገር በቀል መንግሥትና ሥልጣኔ የመሠረቱ ናቸው። ሐረር ውስጥ የሕዝብ ቆጠራ ይካሄድ ነበር፣ የዛሬ 400 ዓመት። እና በኢትዮጵያ እስልምናም ክርስትናም የኢትዮጵያን ሥልጣኔ ያዳበሩ ናቸው። ኢማም አሕመድ የሚመጣውም ከዚህ ነው።

ስለ ኢማም አሕመድ ወይም ግራኝ አሕመድ ከተነሳ፣ ግራኝ አሕመድን በተመለከተ ያለው የታሪክ አረዳድ እንዴት የሚገለጽ ነው?
ሰሜኑ ላይ አክሱም ነበር፤ አክሱም በዛጉዌ ተተካ፣ እነንጉሥ ላሊበላ። ዛጉዌዎች እያሉ ከስር ደግሞ ራሱን የቻሉ የሸዋ ሱልጣኔት አለ፣ ከዛ በኋላ ኢፋት አለ። የሸዋ ሱልጣኔት በኢፋቶች ተተካ፣ እአአ በ1280 አካባቢ። ኢፋት እና ዛጉዌ ራሳቸውን የቻሉ አገር ሆነው ሰላማዊ ግንኙነቶች ነበራቸው። ከዛ በኋላ ዛጉዌ በሰለሞናዊ ስርወ መንግሥት፣ በነይኩኖአምላክ በ1270 ተተካ። ያኔ የመጀመሪያ አማጺ የሆነ ሰለሞናዊ ስርወ መንግሥት ወጣ።

ይህ ሥርወ መንግሥት ያደረገው ሌላውን እውቅና አለመስጠት ነው። በዚህም የመጀመሪያውን ጥይት ኢፋት ላይ ተኮሰ። አስፋፋ ወይም ወረረ በይው። ለማንኛውም ኢፋት በአምደጽዮን ተወረረ። ከዛም የኢፋት መሪዎችን ገደለ፣ ግማሾቹን ሾሞ።

ወረራ ከተባለ መጀመሪያ የተረደረገው ወረራ ይህ ነው። ከዛ ኢፋት ተሸንፎ እየሸሸ ወደምሥራቅ እያፈገፈገ የሙስሊሞች ስቴት ከሸዋ ወደ ምሥራቅ ሄደ። ሐረር ላይ የሚታየው መስፋፋት ከዚህ የመጣ ነው። እስከ 15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማጠቃለያ ድረስ ሙስሊሞች ለነጻነት ሲታገሉ፣ ብዙ ጊዜ ሲሸነፉ 15ኛው ክፍለ ዘመን ደረሰ።

በዛን ዘመን አዳል ወጣ፤ አማጺ መሆን ጀመሩ። ከዚህ ነው ኢማም አሕመድ የወጣው። በወቅቱ ሌሎች ምክንያቶች ተደራርበው የክርስትያን ግዛት፣ በተለይ ከዘርዓ ያዕቆብ በኋላ ሲዳከም አዳል እየተጠናከረ መጣ። ከዛ ኢማም ማህፉዝ በ1517 ሲገደል፣ ኢማም አሕመድ ድልወንበራን አግብቶ ሥልጣን ላይ ይወጣል።

ከዛ ከ1520 ጀምሮ ኢማም ከ14ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የነበረውን የክርስትያን ስርወ መንግሥት መስፋፋትን ገታ፣ የሙስሊሞች የነበረውን ቦታዎች አስለቀቀ። ከዛ በኋላ ግን አልቆመም። ሰሜኑን ክፍል ያዘ፤ ገዛ። እነሱ በክርስትና ሥም ገዙ፣ እሱ በእስልምና ሥም ገዛ።

አሁን ይህን ወረራ ማለት ይቻላል። ግን አምደጽዮን ምንድን ነው ያደረገው? አየሽ! በታሪክ አረዳዳችን የምኒልክ ሲሆን ተስፋፋ ነው የምንለው። ኢማም አሕመድ ሲሆን ወረረ ነው፤ ይህ ልክ አይደለም። ከዚህ ጋር ተያይዞ ኢማም አሕመድ አደረገ የተባለው ነገር አለ። ለምሳሌ ቤተክርስትያን አፈረሰ አቃጠለ። እንደውም እኔ የምለው የመንደር ጎረምሳ አደረከው ወይ ነው። አምደጽዮን 15 ሺሕ መስጂድ አፈረስኩኝ ብሎ ጽፏል። ይህን ማንም አያወራም።

ኢማም አሕመድ ቤተክርስትያን አላፈረሰም ብዬ አልከራከርም፣ ግን ቤተክርስትያን አይደለም ያፈረሰው። አገር ነው ያፈረሰው። ማለቴ መስጅድ ያኔ ለአምደጽዮን ተቋም ሆኖ መፍረስ ከነበረበት ይፈርሳል። በዛ ውስጥ ይህ አገር ሲፈርስ ቤተክርስትያን ተቋም ከሆነችና መፍረሱ ካስፈለገም እንደዛው። ግን ይሄ ቤተክርስትያን ለማቃጠል ክብሪት እንደመለኮስ አይደለም፣ መንግሥት ነው የሚመሠረተው። ሃይማኖትና መንግሥት ደግሞ በወቅቱ የተቆራኙ ናቸው። ኢማም አሕመድ የክርስትያን ስርወ መንግሥትን ነው ያፈረሰው። ይህ ደግሞ በታሪክ ወንጀል ነው ወይ?

አየሽ! አሁን ሰው ስሱ ስሜት ስላለውና ሃይማኖትም ስለሆነ፣ ለ300 ዓመት የቆየና በክርስትያን ስርወ መንግሥት የተጀመረን ጦርነት፣ ልክ የሆነ ሰው ከሆነ አገር መጥቶ እንደደመሰሰ ነው የሚያየው። እንደውም ግራኝ ሰው እንዳልሆነና ሌላ አውሬ እንደሆነ ነው የተሳለው። ግን ኢማም አሕመድ የክርስትያን መንግሥትን ሰበረ። ዘመናዊት ኢትዮጵያ ብቅ ያለችው በዚህም ነው።

እንዴት ይሆን?
ለ300 ዓመት ሲስፋፋ የነበረው የክርስትያን ስርወ መንግሥትን የኢማም አሕመድ ጦርነት ገታ። ከእርሱ በኋላ አዳል ወደ ሐረር ሸሸ። የክርስትያን መንግሥት ደግሞ ወደ ሰሜን ወጣ። በመሃል የኦሮሞ መስፋፋት መጣና ኦሮሞዎች ተጠናከሩ። ከዛ በኋላ የክርስትያን ስርወ መንግሥት ለ200 ዓመት አላንሰራራም። ይህንንም የሚሉት ታደሰ ታምራት፤ ቤተክርስትያን እና መንግሥት በሚለው መጽሐፋቸው ነው።

አሁን ይህን ማውራት እንችላለን፤ ስለመንግሥት ስናወራ። ኢማም እሕመድ ለ15 ዓመት ነው፤ ከዛ በኋላ የለም። ግን አሁን ያለችው ብዝኀነት ያላት ኢትዮጵያ እንድትመሠረት ሆኗል። ምንአልባት ሙሉ ለሙሉ ይህ ኣካባቢ ክርስትያን ይሆን ነበር። ይህን ገትቷል።

እንዲህ ባሉ አጋጣሚዎች ግን ኢትዮጵያ ምን ያህል ጊዜ ከጉዞዋ ቆማለች፣ ወደኋላስ ተመልሳለች?
መንግሥትን ከየት አንጻር ነው የምናየው ነው። እኔ ለምሳሌ የክርስትያኑ መንግሥት መመታት የኢትዮጵያ ውድቀት ብዬ አላስበውም። አሁን ግን ከክርስትና አንጻር ብቻ የሚያየው እንደዛ አይልም። ግን ኢትዮጵያ ብዙ ነች። የኢማም አሕመድ ውድቀት የኢትዮጵያ ውድቀት አይደለም፤ የእስልምና ውድቀት ሊሆን ይችላል። ኢትዮጵያ ከሙስሊምም ከክርስትያንም በላይ ትልቅ ነች።

ዘመነ መሳፍንት ለእኔ አንድ ሂደት ነው፤ መጥፎ ዘመን አይደለም። ዘመነ መሳፍንት በባህሪው ውጊያ የበዛበት ይባላል፤ ግን እስቲ ከአምደጽዮን ጀምሮ ውጊያ የሌለበት ዘመን የትኛው ነው? አጼ ቴዎድሮስ መጡ ውጊያ የለም? አጼ ኃይለሥላሴ መጡ፣ ውጊያ አልነበረም? የደርግ ጊዜ ነው ውጊያ የሌለው? ኢትዮጵያ ውስጥ መች ከውጊያ ወጥተን እናውቃለን? ግን ዘመነ መሳፍንት ውስጥ የበላይ የነበሩት ኦሮሞዎችና ሙስሊሞች ነበሩ።

የትኛው ጊዜ ነው ከዘመነ መሳፍንት የሚሻል? በዛ ውስጥ ግን ኢማም አሕመድ ሌሎች ድርሻ እንዲኖራቸው አደረገ። የየጁ ስርወ መንግሥት፣ የየጁ ኦሮሞዎች፣ ወሎዮዎች አካል ሆኑ።

ኢትዮጵያ በዘመናዊ ታሪኳ ያልተጠቀመቻችው ብዙ እድሎች አሉ። አንደኛ ያልተጠቀመችበት የምለው፤ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በተለይ በተረጋጉበት ዘመን ነው። ኢትዮጵያ ተመሠረተች፤ መቼስ አገር በጉልበት ነው የሚመሠረተው። አንዱ አሸንፎ ሌላው ይሸነፋል። የኃይል ጉዳይ ነው፣ እንጂ ኃይል ቢኖራቸው አባ ጅፋ ሊሆኑ ይችሉ ነበር። እኔ ዘመናዊት ኢትዮጵያ ምስረታ ላይ አላማርርም። እኔ ከኢትዮጵያ አንድ መሆን በኋላ እንዴት የጋራ የሆነ ማንነት መገንባት አቃተን ነው። እንዴት ኢትዮጵያውያንን የሚያስተሳስር ይጠፋል?

ቱርክ ነበርኩ፤ የፈለገ አመለካከት ይኑረው ሁሉም በቱርክ ባንዲራ አይደራደርም። እንዴት በባንዲራ ላንስማማ ቻልን? እንዴት በአድዋ ድል ላንስማማ ቻልን? ችግር አለ ማለት ነው። እኔ የሚታየኝ ከኹለት አንድ ችግር ነው።

አንደኛ የኢትዮጵያ መሪዎች ጉልበት ኖሯቸው በደንብ ጨፍለቀው ሁላችንንም ክርስትያን አማራ ቢያደርጉን ኖሮ ጥሩ ነበር፤ ግን አልሆንም። በአንድ በኩል ጉልበት የላቸውም። ካልሆነ ግን ብዝኀነትን የሚቀበል ስብእና ልናዳብር ይገባል።

ለምሳሌ ክርስትያኖችና ሙስሊሞች ሲዋጉ፣ ኹለቱም እየደከሙ ሄዱና ሌላ ኃይል፣ ኦሮሞ ወጣ። ኦሮሞው ከሌላ ኃይል ጋር ሲዋጋ፣ ነገ ደግሞ ሌላ ይወጣል። በዚህ ብዙ ማኅበረሰብ ጠፍቷል። እስከ መቼ ነው? አሁን አማራና ኦሮሞ እየፎከረ ነው፤ ኹለት ወገኖች ሲዋጉ በአንድ ነገር ይሳካላቸዋል፣ ራሳቸውን በማዳከም። አንዱ አንዱን በማዳከም።

ምኒልክ ጊዜ አላቸው ብዬ አላስብም። ግን በአጼ ኃይለሥላሴ ጊዜ ጥሩ ሥራ ይሠራል ብዬ አስባለሁ። ተቆጣጠሩት፣ ሄደው ግን የሚያደርጉት አንድ ሐይማኖትና አንድ ባህል ለመጫን መሞከር ነው። በኋላ ደግሞ ይህን የሚቋቋሙ/የሚቃወሙ ሰዎች ወጡ። ብዝኀነትን ለማስተናገድ። ኢትዮጵያ እንደ ማንኛውም አገር በጉልበት ነው የተመሠረተችው። ይህ ችግር የለውም። በኋላ የፈጠርነው አንዱ አንዱን የሚያገል አስተሳሰብ ነው ችግሩ።

እንደ እኔ አረዳድ የኢትዮጵያ ችግር እስልምና ነው። የኤርትራ ጉዳይ ላይ ለመገንጠል አልፈለጉም ነበር፤ ጥይት የጫሩት ሙስሊሞች ናቸው። ብሔርተኝነትን ፈጣሪዎች ሙስሊሞች ናቸው። ብዙ ሰው ይህን እንደ መጥፎ ያየዋል። እንደዛ አልቆጥረውም፣ ልክም ነቸው።ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን ከተቀላቀለች በኋላ፣ 1960 እነ ኢድሪስ አዎቴ ጥይት የተኮሱት ለኤርትራ ብሔርተኝነት ሳይሆን ለእስልምና ነው። ለምን ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ከተቀላቀለች ሙስሞች ይጨቆናሉ ነው እንጂ የኤርትራ ብሔርተኝነት አይደለም ትልቁ ጉዳያቸው። በኋላ ላይ ለመጣው ነገር ሁሉ የቀደሙት ነገሮች ናቸው ምክንያት።

ኢትዮጵያ ውስጥኮ ባልተጻፈ ሕግ መስጊድ መንገድ ላይ መሥራት ክልክል ነው። እነዚህን ነገሮች ማውራት አለብን። ትክክለኛ የመንግሥት ችግር ይህ ነው። ካልሆነ መንግሥት ሁሌ የሚያወራልን ‹ኢትዮጵያን ጠላቶች እየወጓት› የሚል ነው። መጀመሪያ ጠላት ማን ነው፤ መተርጎም አለብን።

ትልቁ ፈተና ይህቺን አገር እንዴት አድርገን ሁሉም የሚኖርባት እናድርጋት የሚል ነው። በነገራችን ላይ ከራጉኤል አንዋር መስጊድ ይቀርባል፤ ግን ታክሲ ሲጠራ ራጉኤል እያለ ነው። እነዚህ ትንንሽ የሆኑ ልንፈታቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ። ስለዚህ ውስጣችን ያለው ብዝኀነትን ያለመቀበል ችግር ኃይለኛ ነው። ይህን ደግሞ በግልጽ ተነጋግረን፣ ሳንወሻሽ፣ ሳንፎጋገር፤ ግባችን ደግሞ ለማፍረስና ቂም ለመያያዝ ሳይሆን አገር ለመገንባት ሆኖ ከሠራን፣ መፍትሔ ይመጣል።

ዛሬ ግብጾች ጣልቃ ከገቡ በራሳችን ቀዳዳ፣ አሜሪካኖች ከገቡ በራሳችን ቀዳዳ። ለምን? እውነቱን ስለማናወራ። ግልጽ እንወያይ። መፍትሔ የሌለው ነገር ሞት ብቻ ነው። የሞተ አይመለስም። ሞት መፍትሄ ስለሌለው ችግር አይደለም። ሁሉም ችግር መፍትሔ አለው።

ታድያ ባለፈ ታሪክ ኢትዮጵያ ምን ያህል እድሎችን እንደ አገር አጥታለች ማለት ይቻላል?
በ1966 እድለ አጣን። 1982/83 ኢሕአዴግ ሲገባም አጣን። የደርግ መፈንቅለ መንግሥትን ጨምሮ ከዛ ቀደም የነመንግሥቱ ነዋይ መፈንቅለ መንግሥት እድል ነበር፤ አጣን። አድዋ እድል ነበር። እውነት ነው አድዋ ያኮራል፤ አድዋ ኢትዮጵያውያንን ከሚያኮራው በላይ ጋናዎችን ያኮራል።

ኢትዮጵያን ስስላት፣ ከውጪ ጠንካራ ከውስጥ ደካማ አገር ሆና ትታየኛለች። የአድዋን ድል ደስታና ፉከራችን ለአገር ምንድን ነው የጠቀመው ነው። የኢትዮጵያን መሪዎች የበለጠ ትዕቢተኛ አድርጎ እንዲዘምቱ ነው ያደረጋቸው ወይስ ወደ እድገትና ይህቺ አገር የሁላችንም ናት ወደማለት ነው ያደረሰን?
ኢትዮጵያውያን ለውጪ ጀግና ነን፤ ለውስጥ ግን ደካማ ነን። ስለዚህ ኢትዮጵያ ምንጊዜም ማንም ጠላት የማያሸንፈው አገር ነው። ክፉ አሳቢ ሆኜ አይደለም። ትኩረታችን ትክክለኛ ችግራችን ላይ እንዲሆን ስለምፈልግ ነው። ይህ አገር ትልቅ አገር ነው፤ አየሩ ይበቃል።በዚህ አገር ግን ብዝኀነትን ካልተቀበልን፣ አንድ የሚያደርጉን ምንድን ናቸው ብለን የጋራ እሴቶችን ካላወጣን፣ እኔና አንቺ እየተወሻሸን ሴራ ከሠራን፣ አይሆንም። ሁላችንም በራሳችን ጉድጓድ እየኖርን ነው። ያልሞከርነው ነገር ግልጽነት ነው። መጥፎውን ስናሰብ እዚህ አገር ላይ የማይፈታ አንድም ችግር አይኖርም።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ወደ ሥልጣን መምጣት ተከትሎ የታዩ ተስፋዎችና ተገኘ የተባለ ጥሩ እድል ነበር። ይህንን ለውጥስ እየተጠቀምንበት ነው ወይስ እያመለጠን?
በጣም እያመለጠን ነው እንጂ። አሁን ከባድ ነው። ግን ሂደት ነው ብዬ ነው የማስበው። ፖለቲካ የጀመርነው ራሱ አሁን ነው ባይ ነኝ። እስከ አሁን መንግሥት ብቻ ነው የሚያወራው፣ አሁንም ወደዛ ካልመለሱን (ሳቅ)። አሁን ያለውን የተፈጥሮ ሂደት አድርጌም ነው የማስበው። አሁንም ቢሆን እኔ የምመርጠው እየተለቀቀ በራሱ ጊዜ ቅርጽ እየያዘ ይሄዳል ነው።

ግን ወደ መስተካከል የሚሄድ ይመስላል?
ይሄዳል አትጠራጠሪ። ብዙ አገራት ያለፉበትም ነው። ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት የዛሬ 20 ዓመት ቱርክ የነበረችበት ነው። ቱርክ ኢስታንቡል ላይ ሰዎች አንዱ ሰፈር ወደ አንዱ ማለፍ አይችሉም ነበር፤ እየተጋደሉ። ይህ ያልፋል። በማፈን ግን አያልፍም።

ውሸታችንን ነው እንጂኮ አንዳችን ያለ አንዳችን አንኖርም። ኢትዮጵያ ውስጥም ከእንግዲህ ወዲህ አንዱ አንዱን ጨቁኖ መኖር አይችልም። ይሄ በቃ እውነት ነው! ኹለተኛ ሁላችንም አሁን ስለራሳችን አይደለ የምናወራው? አውርተን አውርተን መፍትሔ የለም። ሁላችንም በቆፈርነው ጉድጓድ ውስጥ ኖረን፤ ከዛ መራብ አለ። ሌላው ያስፈልጋል። ይህን እውቅና የምንሰጥበት ጊዜ ይመጣል ብዬ አስባለሁ።

ሌላው ማንም ማንንም የሚያሸንፍበት ኃይል አይኖርም፤ ሽክርክሪት ነው የሚሆነው። አንዱ ሌላውን፣ ሌላውም ሌላውን እንደዛ እያለ ሁሌ እንሸናነፋለን፣ በዚህም ሁላችንም እንሸነፋለን። ከዚህ ውጩ ቁጭ ብለን እንነጋገርበት። እውነታውን እናስቀምጥ። ይሄ ሃይማኖት ይሄ ብሔር ሳይባል በፍትህ። እና አሁንም እድል አለን ብዬ አስባለሁ።

ልጆችን የነገ አገር ተረካቢ እንላቸዋለን። ነገ በሚባለው ወጣትነታቸው ግን በኃላፊነት ወንበር አይቀመጡም። እርስዎም በሌላ ቃለመጠይቅ ሲናገሩ፣ አሁንም የ1960ዎቹ ፖለቲካውን እንደሚዘውሩት ጠቅሰዋል። ታድያ የወጣቱ ቦታ የት ነው?
የወጣቱ ተሳትፎው ሁልቀን አለ፤ የሚሞተው ወጣት ነው። ትልቁ ነገር ወጣቱ ከሌላው መማር ያለበትን መማር አለበት። ወጣቱን እንደ ማገዶ መጠቀም አለ፤ ትክክለኛ ኃላፊነት እንዳይኖረው ማድረግ ነው። ኢትዮጵያን አሁንም ቢሆን በአመለካከትም እየዘወሩት ያሉት ቀደሙት ናቸው። ይህም በቀላሉ ይጠፋል ብዬ አላስብም። አሁን እድሜያው እየገፋ ስለሆነ ባዮሎጂው ራሱ ጨዋታ እየተጫወተ ነው።

ግን አሁንም ቢሆን አዲስ አስተሳሰብ ለምን አናመጣም ስንል፣ እስቲ ማን ነው ከነዋለልኝ መኮንን በኋላ የወጣ ተጠቃሽ? በሁሉም ዘርፍ የቀደሙት ናቸው የሚነሱት። በአካል ባይሆንም ሐሳባችንን የተቆጣጠሩት እነርሱ ናቸው። ቀይ ሽብር ከበደለን ነገር አንዱ የኢትዮጵያን ክሬሙን ነው ያነሳው። ያኔ የሚቀረው ደረቁ ነው። ያ ትውልድ ሲያልቅ ኮስሞቲክ የሆነ የማያነብ፣ ቴክኒካል ብቻ የሆነ፣ በሐሳብ ላይ የማይመራመር ትውልድ መጣ።

ይህን ስንል አሁን ደግሞ ሊበራላይዜሽንና ማኅበራዊ ድረገጽ ሲመጣ፣ ትንንሽ ነገር እናውቃለን፣ የጥቅስ መዓት እንጽፋለን። ማስተዋል ግን የለም። ባለፉት 27 ዓመታት የትምህርት ስርዓቱም የደከመ፣ ካድሬን የሚያበረታታ ነው። ይህም የእውነት ያስጨንቀኛል። ከዛም ወጣቱ ለተለያዩ ፖለቲከኞችና የሃይማኖት ቀስቃሾች ተጋላጭ ይሆናል። እና ወጣቱ ራሱን በብዙ ነገር ማብቃት አለበት። ከዛ ደግሞ የጎንዩሽ ፉክክር ይበዛል። ከዛ ወጥተን መቼ ነው ትልቁ አገር የሚባል ርእይ ላይ የምናተኩረው? እሱን ለማዳበር ትልቅ ሥራ መሥራት አለብን ብዬ አስባለሁ።

ኢብራሂም ጨለምተኛ አይደሉም፣ ያለፉ ታሪኮችንም በግልጽ ሲያነሱ ወደተሻለ መንገድ ለመመልከት እንዲያስችል አድርገው ነው። ይህ ቀና ነገርን የመጠበቅ አዝማሚያ ከየት ያመጡት ነው?
አላውቅም፤ ባህሪም ሊሆን ይችላል። ጨለማ ማየት አልፈልግም፣ አይታየኝም። ካለፈው ጨለማ ማምጣት ይጠቅማል ብዬ አላስብም። ግን ደግሞ የእኔ ቁስል ሊገባሽ ይገባል። አንድ ሰው ተበደልኩ፣ እዚህ ጋር አሳከከኝ ሲልሽ አላሰከከህም ማለት አትችይም። ብዙ ጊዜ ቅን አለመሆናችን ያሳስበኛል። ከአንዳንድ ሙስሊሞች ጋር የምጣላው ለምን መሰለሽ፣ በጣም ታዋቂ ከሆኑ ራድዮና ቲቪ ላይ እንዲህ ነን እንዲህ ነን ብለው ተለሳልሰው ዋሽተው ይወጣሉ። ከእኔ ጋር ስንገናኝ ግን ተበድለን ይላሉ። ይሄ ልክ አይደለም፤ ለምን ውሸት እናወራለን።

እኔ አስተዳደጌ ሊሆን ይችላል፤ ወደ መፍትሔ የሚመጡ ነገሮችን ነው ማሰብ ደስ የሚለኝ። መፍትሔ የሌለው የለም። ግን ስናወራ፣ እኔ ተበደልኩኝ ማለት አንቺ በደልሽኝ ማለት ነው ካልኩኝ እንጣላለን። እኔን እንድትረጂኝ ካገዝኩሽ ግን አንጣላም።

ቤተሰቤም እንደ ብዙ ኢትዮጵያዊ ቤተሰብ ነው። እናቴ ሙስሊም ናት፤ አባቴ ክርስትያን ነው። ኹለት እህቶቼ ክርስትያን ናቸው፤ ኹለታችን ሙስሊሞች ነን። ያደኩት አዲስ አበባ ነው። በተቻለ መጠን ሌላውን የእውነት ለመረዳት እሞክራለሁ። ሌላውን የእውነት ለመረዳት ከሞከርሽ መፍትሔ ይጠፋል ብዬ አላስብም።

ቅጽ 2 ቁጥር 70 የካቲት 28 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here