በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያለውን የእብነ በረድ ማዕድን ሀብት እሴት በመጨመር ለዓለም ገበያ ለማቅረብ የማምረቻ እና የልህቀት ማእከል ለመገንባት የጣልያን የእብነ በረድ አምራች ድርጅቶች ማኅበር ከክልሉ መንግሥት እና ከፌዴራል ማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስቴር ጋር ስምምነት ፈረሙ።
ስምምነቱን በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የካቲት 20/2012 የኢፌዴሪ ማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ሳሙኤል ኡርቃቶ (ዶ/ር)፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻዲል ሐሰን እና የጣልያን የእብነ በረድ አምራች ድርጅቶች ማኅበር ፕሬዝዳንት ፓዉሎ ማሮኒ ፈርመዋል። በዚህ መሰረትም በአጭር ጊዜ ውስጥ በክልሉ ካሉ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ተቋም አንዱን በመምረጥ እብነበረድ ላይ በተለየ መልኩ የልህቀት ማእከል እንዲሆን ለማድረግ እቅድ ተይዟል።
በእብነ በረድ አወጣጥ ላይ ያተኮሩ የዘርፉ ሥልጠናዎች የሚሰጡበት፣ እብነበረድ ለማምረት የሚያስችሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የሚበለጽጉበት እና ዘርፉን ለሚመሩ ባለሙያዎች የተለያዩ ሥልጠናዎች የሚሰጥበትም እንደሚሆን ክልሉ አስታውቋል።
በእብነ በረድ ምርት ዘርፍ ቴክኒካል ኮሌጅ እንዲሆን የታሰበው ይህ የልህቀት ማእከል፣ በተጨባጭ የሚጀመርበት ጊዜ ባይታወቅም በአጭር ጊዜ ለማስጀመር የዳሰሳ ጥናት እየተሠራ እንደሆነ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ኪሮስ ዓለማየሁ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።
በክልሉ የሚገኘውን የእብነበረድ ሀብት ለአገር ውስጥ እና ለውጪ ባለሀብቶች ለማስተዋወቅም፣ የእብነ በረድ ባዛርና ኤግዚቢሽን ዝግጅቶችን በቋሚነት ለማካሄድ መታሰቡን ኪሮስ ገልፀዋል። ባለሀብቶች በአካባቢዉ ያለውን ሀብት መሬት ላይ ወርደዉ እንዲያዩትና በዘርፉ እንዲሰማሩ ርብርብ ይደረጋልም ብለዋል።
ከጣሊያን አገር የእብነበረድ ባለሙያዎች እና ከፌዴራል ማዕድን፣ ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር እንዲሁም ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የተውጣጣ ቴክኒካል ኮሚቴ ተቋቁሞ በክልሉ ያለውን የእብነ በረድ ሀብት ክምችት ማረጋገጡን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በጥናቱም በአካባቢው ያለውን የእብነ በረድ ክምችት ከማወቅ ባሻገር፣ ጥራቱን ለማረጋገጥ መቻሉን የገለጹት ኪሮስ፣ በጥናቱም እብነ በረዱ ከፍተኛ ጥራት ያለው እና በዓለም ገበያም ተፈላጊ መሆኑን ከጣልያን የመጡት የእብነ በረድ ባለሙያዎች ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።
ኪሮስ እንደሚሉት፣ አሁን እየተከናወነ ያለው እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባውን የእብነ በረድ ምርት በአገር ውስጥ ለመተካትና በአገሪቱ ያለውን የእብነ በረድ ሀብት በቴክኖሎጂ በመታገዝ በአግባቡ ለመጠቀም ያለመ እንደሆነ አስረድተዋል። ይኸው እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ ያላትን ሀብት ተጠቀማ፣ እብነ በረድን ከውጭ ለማስገባት የሚወጣውን የዉጭ ምንዛሬ ለማስቀረት ያለመም እንደሆነ ኪሮስ አክለዉ አብራርተዋል።
በክልሉ ያለዉ የእብነ በረድ ሀብት በጥራትም ከውጭ ከሚገባዉ የተሻለ ደረጃ እንዳለው በጥናቱ መረጋገጡን ኪሮስ ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ በቴክኖሎጂና በሰው ኃይል ልማት ዘርፍ በክልሉ ለማቋቋም ያቀዳቸው የሥልጠናና የልህቀት ማእከላት እውን መሆን ለክልሉ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ትልቅ አስዋጽኦ ይኖረዋል ያሉት የቤኒሻንጉል ክልል የማዕድን ኤጀንሲ ዳይሬክተር አካሻ ኢስማኤል ናቸው። አካሻ አክለውም፣ የእብነ በረድ ኢንዱስትሪዉ በክልሉ እዉን ሆኖ ለአገርና ለዜጎች የሚጠበቀውን ዉጤት እንዲያመጣ፣ ከፕሮጀክቱ ጎን በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ተቋማቸው እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
በስምምነት ፊርማ ስነ ስርአቱ ላይ የተገኙት የጣልያን እብነ በረድ አምራች ድርጅቶች ማኅበር ፕሬዝዳንት ፓዉሎ ማሮኒ፣ በእብነ በረድና በተፈጥሮ ድንጋይ ምርትና ጥበብ ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው የጣልያን ቴክኖሎጂን ይዘው እንደሚመጡ ተናግረዋል። ወደ ሥራ ሲገባም በቴክኖሎጂ ሽግግርና የሥራ እድል ከመፍጠር ባሻገር፣ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሬ በመጨመር በኹለቱም አገራት ጠንካራ የልማት ትስስር እንደሚፈጥር አካሻ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 70 የካቲት 28 2012



