የትግራይ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዓለም ዐቀፍ አገልግሎት የሚሰጥ ኖርዝ ስታር የተሰኘ የአየር መንገድ ለማቋቋም አክሲዮን መሸጥ የጀመረ ሲሆን፣ በዚህም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ 40 ሚሊዮን ብር የአክሲዮን ሽያጭ ማከናወኑን ገለፀ።
የኖርዝ ስታር አየር መንገድ የቦርድ አባል እና አመራር የሆኑት መኮንን አሰፋ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ ቦርድ ተመርጦ የአመራር ድልድል ማካሄድ ተጀምሯል።
ድርጅቱ አክሲዮን ከመሸጥ ባሻገር አውሮፕላንን ጨምሮ የተለያዩ የካፒታል እቃዎችን ወደ መግዛት አለመግባቱን ገልጸው፣ ለጊዜው ግን ለምሥረታው የሚያስፈልገውን ሦስት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር በማሰባሰቡ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። የድርሻ ሽያጩ የታሰበውን ያህል ላለመሆኑም በቂ የማስተዋወቅ ሥራዎች ስላልተሠሩ መሆኑን ተናግረዋል።
አየር መንገዱን ለማቋቋምም በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ያለውን እጥረት ለመፍታት እና ዘርፉን ለማሳደግ በማሰብ እንዲሁም የንግድ እንቅስቃሴዎችን ለማስፋት ታስቦ መሆኑን አስታውቀዋል።
አየር መንገዱ ሲቋቋምም ሦስት ዋና ዋና ተግባራት የሚኖሩት ሲሆን፣ መንገደኞችን ማጓጓዝ፣ የእቃ ማጓጓዣ፣ የሥልጠና እና የጥገና አገልግሎቶችን እንደሚሰጥም ተናግረዋል።
ታዋቂው አትሌት ገብረእግዚአብሔር ገብረ ማርያም፣ የወጋገን ባንክ ፕሬዝዳንት አባይ መሃሪ፣ መኮንን አሰፋ፣ ኬላሊ አዳነ እና ብሩክ አባይነህ የአየር መንገዱ መሥራቾች ናቸው። የአየር መንገዱ በከፍተኛ ዋጋ ለታዋቂ ሰዎች አክስዮን መሸጡም ታውቋል። የቀድሞው የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አዛዥ ጄነራል ጻድቃን ገብረ ትንሳኤ፣ የአየር መንገዱን የማቋቋም ሂደት እንደሚያማክሩ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ከፍተኛ መጠን ያለው የአክሲዮን ድርሻ ገዝተዋል መባሉን ግን አስተባብለዋል።
ከአራት መቶ በላይ የሚሆኑት የባንኩ መሥራቾች በቅርቡ አካሂደውት በነበረው ጠቅላላ ጉባኤም፣ የአንበሳ ባንክ ፕሬዘዳንት ጌታቸው ሰለሞን የቦርድ ዳይሬክተር ሆነው እንዲያገለግሉ ተመርጠዋል። ድርጀቱ ባለ ሠላሳ አምስት ፎቅ ሕንጻ በመቀሌ ከተማ የማስገንባት እቅድ ያለው ሲሆን፣ ከኢትዮጵያውያን ባሻገርም በዳያስፖራ ያለውን ሀብት ለማሰባሰብ ማሰቡን ገልጿል።
ቅጽ 2 ቁጥር 70 የካቲት 28 2012



