ሰባት ወራት የፈጀው የሎጂስቲክ ሕንፃን የማፍረስ ሙከራ አስቸጋሪ ሆኖ ቀጥሏል

0
963

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት በመሆን ለ21 ዓመታት ያገለገለው ሕንጻ፣ ለለገሃር የተቀናጀ ልማት የቤቶች ግንባታ ታስቦ እንዲፈርስ ተወስኖ ለሰባት ወራት ሙከራ ቢደረግም እስከ አሁን ሙሉ ለሙሉ ማፍረስ ሳይቻል ቀጥሏል።

ስምንት ወለል ወደ ላይ የሚረዝመው እና ከምድር በታች አንድ ወለል ያለውን ይህንን ሕንፃ ለማፍረስ ለሰባት ወራት ያህል ቢሞከርም፣ የሕንፃው ጥንካሬ ግን አሁንም የማፍረስ ሥራውን ከባድ አድርጎታል። ሕንፃው ለ50 ዓመታት አገልገሎት ታስቦ ከ21 ዓመት በፊት የተገነባ ሲሆን፣ ለግንባታው ባለ 32 ቁጥር እና ባለ 16 ቁጥር ፌሮዎች ሥራ ላይ በመዋላቸው፣ የማፍረስ ሥራውን የማይቻል አድርጎብናል ሲሉ በጥቃቅን እና አነስተኛ የተደራጁት ወጣቶች ተናግረዋል።

እነዚህ በኮንስትራክሽን ሥራ የተሰማሩት ወጣቶች፣ ሕንፃውን የማፍረስ ሥራውን ማገባደድ ባለመቻላቻው የቀን ሠራተኞቻቸውን አሰናብተው አዳዲስ አማራጮችን እየተመለከቱ እንደሆነም ተናግረዋል።

ከቀድሞው የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ዋና መሥሪያ ጎን እና ጎን የሚገኙ ሌሎች ሕንፃዎች በቀላሉ ፈርሰው የተጠናቀቁ ሲሆን፣ ሕንጻዎቹም ባለ አራት እና አምስት ወለል ያላቸው እንዲሁም 35 እና 40 ዓመት እድሜ ያስቆጠሩ ነበሩ።
እነዚህ በጥቃቅን እና አነስተኛ የተደራጁ ወጣቶች፣ አፈር በማስገልበጥ እና ስካቫተር በአፈሩ ላይ እንዲሄድ በማደረግ መሰረቱን ለማላላት እየሞከሩ እንደሆኑ ተናግረዋል።

ላለፉት ስድስት ወራት ኢንተርፕራይዙ ሰባ የቀን ሠራተኞች ቀጥሮ የማፍረስ ሥራው ሲሠራ እንደነበር ገልፀው፤ ነገር ግን ከዚህ ቀደም እንደተለመደው በሰው ኃይል ሊፈርስ አለመቻሉን ተናግረዋል።

‹‹ይህ በመሆኑ…›› ይላሉ የማኅበሩ አባል ‹‹ይህ በመሆኑ እንደማንኛውም ሕንጻ ጠንካራ ነው ብለን በኤክስካቫተር ለማፍረስ ብንሞክር፣ አካባቢው ላይ ያለው ግንባታ ላይ የማናጋት ችግር ሊፈጠር ስለሚችል አፍር ከሌላ ቦታ አምጥተን በመገልበጥ በዛ ላይ ኤክስካቫተሩ እንዲንቀሳቀስ በማድረግ የሕንፃውን ጥንካሬ የማላላት ሥራ እየሠራን ነው›› በማለት አስረድተዋል። በዚህም ምክንያት ሕንፃውን አፍርሶ የማጠናቀቁ ሂደት እስከ ቀጣይ ኹለት ወራት ሊዘልቅ እንደሚችልም ገልጸዋል።

የህንፃውን ግንባታ ያከናወነው ቫርኔሮ ሪል ስቴት ሲሆን ይህን ሕንፃ ልማት ባንክ ግማሹን ማለትም ከ37 አስከ 40 ሚሊዮን ብር አካባቢ ባቀረበው ብድር ለኢትዮጵያ ንግድ መርከብ የተገነባ ሕንፃ ነበር ሲሉ፣ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አሸብር ኖታ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ከአንድ ዓመት በፊት መንግሥት ቦታውን ለለገሃር ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት መፈለጉን እና ሕንጻው ሊፈርስ እንደሆነ በደብዳቤ እንደተገለፀላቸው አስታውሰው፣ መሥርያ ቤቱ በመፍረስ ላይ ባለው ሕንፃ በነበረ ጊዜ 4 ሺሕ 700 ሠራተኞች እንደነበሩት ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኪነ ሕንፃ ግንባታ እና የከተማ ፕላን መምህር ዮሐንስ መኮንን ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ ሕንፃ እንዴት መፍረስ እንደሌለበት ማስተማርያ ነው ይላሉ። ‹‹በተጨማሪም የእኛ ተማሪዎች ለልምምድ ሲሄዱ በተማሩት መሰረት፣ እንዴት መፍረስ እንዳለበት እንዲነግሯቸው አድርገናል›› በማለት አክለዋል።
አንድ ሕንፃ ሲፈርስ የሕንፃው ዓይነት እና የሕንጻውን ክብደት የተሸከመው የትኛው ምሶሶ ነው የሚለው ከተለየ በኋላ ነው፣ ከዛ በመጀመር የሚፈርሰው ሲሉም ያስረዳሉ።

ከዛም በተጨማሪ ሁለት አይነት ህንፃ የማፍረስ ዘዴዎችን መጠቀም ይቻላል፤ እንደ ባለሞው ገለፃ። ዳይናሚክ እና ኤክስካቫተር ዲሞሊውሽን ማሽን በመጠቀም በቀላሉ ህንፃዎችን ማፍረስ እንደሚቻል ተናግረዋል።

ዳናሚክስ ማለት ህንፃውን በሙሉ አቅም የተሸከመውን ምሶሶ በቴክኒክ ለይቶ በማፈረስ ወደ ሌላው በመሄድ ማፍረስ ይቻላል ሲሉ ያስረዳሉ። ይይ ካልተሳካ ግን የኤስካቫተር ዲሞሊውሽን ማሽን ደግሞ ድምጽ የሌው በህፃው መካከል በማስቀመጥ በንዝረት ህንፃውን በቀላሉ የማፍረስ ዘዴ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 70 የካቲት 28 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here