የሟቹ አራጣ አበዳሪ አየለ ደበላ ንብረት ለተበዳዮች እንዲተላለፍ ፍርድ ቤት ወሰነ

0
690

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ጥር 27/2012 በዋለው ችሎት፣ በአራጣ ማበደር የተፈረደባቸው ሟች አየለ ደበላ ሴት ልጅ እና በጠቅላይ አቃቤ ሕግ መካከል በነበረው የንብረት ይገባኛል ክርክር ለግል ተበዳዮች እንዲሆን ፍርድ ቤቱ ወሰነ።

የአየለ ደበላ ልጅ ሥም ለቀድሞ የአራጣ ተበዳሪ ዋስ ለነበሩት ግለሰብ ልጆች ይገባል ሲል ውሳኔ ያስተላለፈው ፍርድ ቤቱ፣ መኖሪያ ቤቱን ለአየለ ደበላ ልጅ ሊተላለፍ የቻለው በአራጣ ድርጊት መሆኑንም አክሏል። ይህም ሳሙኤል ደበበ የተባሉ ግለሰብ ከአራጣ አበዳሪዉ አየለ ደበላ ከ582 ሺሕ ብር ተበድረው፣ ለተበደሩት ገንዘብ ማስያዣነት የዋለው ይህንን ቤት በፍርድ ቤት አስፈርደው ያሸጣሉ።

ይህንን ቤትም ገዢ ሆነው የቀረቡት የከሳሽ አየለ ልጅ ሲሆኑ፣ ቤቱን በአንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ብር ይገዛሉ። ሟች የአራጣ ማበድር ወንጀል ፈጽመዋል ተበሎ ከተፈረደባቸው በኋላም ከሳሽ አቃቤ ሕግ ይህንን ንብረት በወንጀል ያፈሩት ስለሆነ ተሸጦ ለሕዝብ ይከፍለ ሲል ክስ መስርቷል።

ከአየለ አራጣ ተበድረዉ ባለመክፈላቸዉ በዋስ ቤታቸዉን ያስያዙት ሳሙኤል ደበበ ልጆችም፣ በክርክሩ ላይ ጣልቃ ገብተው ‹‹ቤቱ ይገባናል፤ ያለ አግባብ ነው የተወሰደብን›› ሲሉ ባቀረቡት ቅሬታ መሰረት፣ ፍርድ ቤቱ ላቀረቡት የይገባኛል ጥያቄ ፈርዶላቸዋል።

የፍርድ ቤቱን ውሳኔ የተቃወመው አቃቤ ሕግ ‹‹የአራጣ ተበዳሪ ቤተሰቦች ከአራጣ አበዳሪዉ ወስደውት የነበረዉን ብር ስለተጠቀሙ ቤቱ አይገባቸውም። ቤቱ ከተገባቸውም እንኳን ከአራጣ አበዳሪዉ የወሰዱትን ብር መመለስ አለባቸዉ ይህ ካልሆነ ንብረቱ ወደ መንግሥት መግባት›› አለበት ብሎ ሲከራከር ቢቆይም፣ ፍርድ ቤቱ ጣልቃ ለገቡት ሦስተኛ ወገን ተበዳይ ላላቸዉ ወስኗል።

ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈውን ውሳኔ በመቃወምም አቃቤ ሕግ ይግባኝ ለማለት እየተዘጋጀ መሆኑ ታውቋል። ከፍርድ ቤት የዚህን ውሳኔ ግልባጭ ለማግኘት ከኹለት ሳምንት በላይ የፈጀበት አቃቤ ሕግ፣ ውሳኔው ከእጁ እንደገባ አቤቱታውን እንደሚያሰማ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በጉዳዩ ላይ ተሳትፎ ያላቸው አቃቤአን ሕግ ይናገራሉ።

አየለ ደበላ በ2002 ግንቦት ወር በ10 የተለያዩ ክሶች በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 11ኛ ወንጀል ችሎት ጥፋተኛ ተብለዉ የነበሩ ሲሆን፣ ከ22 ዓመት ፅኑ እስራት ባሻገር በንብ ባንክ የነበራቸዉ ድርሻ ኢንሹራንስ እና ተጨማሪ 300 ሚሊዮን ብር እንዲከፍሉ ወስኖባቸው ነበር። ውሳኔዉ የገንዘብ መቀጮን ጨምሮ ወደ 450 ሚሊዮን ብር ክፍ እንደሚል፣ በገቢዎች እና ጉምሩክ ዐቃቢ ሕግ ይግባኝ ተብሎ ሳለ በ2005 ሕይወታቸው አልፏል።

መደበኛ ክርክሩ ባለቀበት ወቅትም በተከፈተዉ የአፈጻጸም መዝገብ በወር ኹለት ሺሕ ዶላር በሚከራየው መኖሪያ ቤት ዙሪያ ክርክር የተነሳ ሲሆን፣ በዚህም ልጃቸዉ የወራሽነት ጥያቄ አንስተዋል። በወቅቱም የተሰጠዉ ውሳኔ የሦስተኛ ወገን መብት ተከብሮ ይፈፀም የሚል በመሆኑ፣ ለጥያቄዎች መሰረት ሆኖ ክርክር ሲደረግበት ቆይቷል።

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ከአራጣ ማበደር ተግባር ጋር ተያይዞ በአየለ ደበላ ላይ ክስ ያቀረበው፣ ግለሰቡ ለባንክ ብቻ የተፈቀደውን አገልግሎት ሲሰጡ በመገኘታቸዉ፣ የግብር አዋጅን በመጣስ የተጨማሪ እሴት ታክስ ሳይከፍሉ መቅረታቸዉ እንዲሁም በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ በማቅረብ ገቢ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቶችን አሳስተዋል በሚል ነበር።

ቅጽ 2 ቁጥር 70 የካቲት 28 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here