የብሔራዊ ሎተሪ የ2012 በጀት ዓመት የግማሽ ዓመት የተጣራ ትርፍ 108 ሚሊዮን ብር በመሆን ተመዝገበ። ይህም ገቢ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በስድሰት ሚሊዮን ብር ቅናሽ ቢያሳይም፣ ከውርርድ የተገኘው ገቢ ትርፉ ከዚህ በላይ እንዳያሽቆለቁል እንዳደረገው ተቋሙ አስታውቋል።
በስድስት ወር ውስጥም 492 ሚሊዮን ብር የሎተር እድል ቲኬቶች የተሸጡ ሲሆን፣ በፈቃድ ከሚካሄዱ ሎተሪዎች ኮሚሽን እና የፈቃድ ክፍያዎች 40 ሚሊዮን ብር ገቢ ሰብስቧል። በአጠቃላይ ያልተጣራ ገቢው 460 ሚሊዮን ብር ሆኖ መመዝገቡን ብሔራዊ ሎተሪ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።
ብሔራዊ ሎተሪው የካፒታል ወጪዎቹ 19 ሚሊዮን የደረሱ ሲሆን፣ ለሠራተኞቹም ባለፈው ስድስር ወር 27 ሚሊዮን ብር ደመወዝ ከፍሏል።
ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት 114 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ሲያዝመዘግብ በታሪኩ የመጀመሪያው ነበር። በወቅቱም ከ2010 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ጋር ሲነፃፀር፣ የ28 ሚሊዮን ጭማሪ በማሳየት ነበር ገቢውን በታሪክ ከፍተኛው አድርጎ ያስመዘገበው።
በወቅቱ ለገቢው መጨመር ምክንያት ሆኖ የተጠቀሰው ከባንኮች እና ከቢራ ፋብሪካዎች የሚሰጡ የእድል ጨዋታዎች የሚከፍሉት የ15 በመቶ የኮሚሽን ክፍያ ነበር። ነገር ግን መንግሥት በድንገት ማንኛውም አልኮል ነክ መጠጥ ላይ የሚደረጉ የእድል ጨዋታዎች እንዳይካሄዱ መከልከሉን ተከትሎ፣ የብሔራዊ ሎተሪ ገቢ እንዲያሽቆለቁል ምክንያት መሆኑን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ገብሬ ሀጎስ ተናግረዋል።
ነገር ግን ከውርርድ ጨዋታዎች የተሰበሰበው የፈቃድ ገቢ 42 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፣ ይህ በበጀት ዓመቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰበሰበ እና ከፍተኛ መሆኑም ታውቋል።
የብሔራዊ ሎተሪ ዋና ዓላማው ገቢ መሰብሰብ አይደለም ያሉት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው፣ ትርፍ ከማግኘት በላይ የውርርድ ጨዋታ ፍቃድ ጠያቂዎች ፈቃድ ከመስጠት ባሻገር ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የተጣለባቸውን ኃላፊነት መፈጸማቸውን በመቆጣጣር፣ ያንን ተላልፈው ሲገኙ ፈቃዳቸውን እስከመሰረዝ እንደሚደርስም አስታውቀዋል።
እስከ አሁንም 46 ባለቤቶች ፈቃድ ወስደው እየሠሩ መሆኑን ተናግረው፣ በግማሽ ዓመቱ 42.5 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን አስታውቋል።
ለገቢው መቀነስ በተለይም የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ደርጅት የመደበኛ፤ የዕድል እና የልዩ ሎተሪ ትኬቶችን በጊዜ አትሞ ማቅረብ ያለመቻሉ አንዱ ምክንያት ነው ሲሉም ኃላፊው ገልፀዋል። በተጨማሪም የቢራ ፋብሪካዎች ሲያካሂዱት የነበረው የእድል ጨዋታ በድንገት መከልከሉ ገቢውን በሰፊው እንደጎዳው ገልፀዋል።
በተያዘው ዓመት የገበያውን ሁኔታ ለመረዳት ኹለት ጊዜ የብሔራዊ ሎተሪ በውርርድ ጨዋታው ላይ ለእያንዳንዱ አንድ ወር የፈጀ ጥናት ተሠርቶ እንደነበርም ተናግረዋል።
‹‹በውጤቱም ጨዋታውን ፈቃድ ከሰጠን በኋላ ምን አይነት ክትትል ማድረግ እንዳለብን እና ከእኛ ፈቃድ ወስደው ነገር ግን ራሳቸውን ችለው ከመሥራት ይልቅ በምግብ ቤቶች አካባቢ፣ በእምነት ቦታና በትምህርት ቤቶች አካባቢ መኖራቸው ትውልድን ከመጉዳት አንፀር ክፍተት እንዲኖረው ያደረገ መሆኑን በመለየት እግድ አስቀምጠናል። አሁን በመቀጠል ሚያዚያ የሚካሄድ አንድ የመጨረሻ ጥናት ይኖራል›› በማለት ተናግረዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 71 መጋቢት 5 2012



