ኢትዮ ስኳር መንግሥት እጁን ከስኳር ፋብሪካዎች ላይ ያንሳ ሲል ጠየቀ

0
909

መንግሥት ሦስት በማምረት ላይ ያሉ የስኳር ፋብሪካዎችን ወደ ግል ዘርፍ ለጊዜው አላዞርም ማለቱን አግባብ አይደለም ሲል ከእነዚህ ፋብሪካዎች ውስጥ መተሃራ ስኳር ፋብሪካን ለመግዛት አንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር አክስዮን የሸጠው ኢትዮ ስኳር አክሲዮን ማኅበር ተናገረ።

‹‹እኛ የምንረዳው ጨረታ ላይ የማውጣት ቅደም ተከተሉን ለመጠበቅ እንደሆነ ነው። መንግሥት ከስኳር ፋብሪካዎች ላይ እጁን ማንሳት አለበት። ከዛም ባለፈ ሙያውን ለሙያተኞች ነው መስጠት ያለበት›› ሲል ማኅበሩ ገልጿል። የመተሃራ ስኳር ፋብሪካን መንግሥት በተያዘው የበጀት ዓመት እንደማይሸጥ ማስታወቁን ተከትሎ፣ ምንም ዓይነት ሰጋት እንደሌለባቸው እና ለጊዜው ለሽያጭ የሚቀርበውን ወንጂ ስኳርን እንደሚገዙም አስታውቀዋል።

በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ስር የሚተዳደሩ 13 ፋብሪካዎችን ወደ ግል ለማዘዋር መንግሥት መወሰኑ የሚታወስ ነው።
መንግሥት በስኳር የማምረት ሂደት ውስጥ መቆየት የለበትም የሚሉት እሸቱ ገለቱ፣ የማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ ሲሆኑ ይህ ካልሆነ ኢኮኖሚውን ማቀጨጭ ነው ብለው እንደሚያስቡም ተናግረዋል። የስኳር ዘርፉ የመንግሥትን ያልተገባ እጅ ማስገባት ጎድቶታል ባይ ናቸው።

አክሲዮኑ ወንጂ እና መተሃራ የስኳር ማምረቻዎችን ለመግዛት ድርሻ መሸጥ የጀመረው ታህሳስ/2011 ሲሆን፣ እስከ ግንቦት 30/2012 እንደሚቆይም ተገልጿል። የአንድ አክስዮን ዋጋ አንድ ሺሕ ብር ሲሆን፣ አንድ ሰው በትንሹ 10 ድርሻዎችን እና ቢበዛ ደግሞ 50 ድርሻዎች መግዛት ይችላል።

መተሃራ የስኳር ፋብሪካን ጨረታ በማሸነፍ ለመግዛት የአዋጪነት ጥናት ተካሂዶ ያለቀ ሲሆን፣ አንድ ዓመት የሞላው የአክሲዮን ሽያጩ አንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ሰብስቧል። ስድስት ወር የፈጀ የአዋጪነት ጥናት ተደርጎ የመተሃራ አና የወንጂ የቢዝነስ እቅድ መውጣቱንም መስረቾቹ ተናግረዋል።

እስከ አሁን የወንጂ እና መተሃራ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች፣ አርሶ አደሮች፣ የአካባቢው ነጋዴዎች አክሲዮን መግዛታቸውን ይፋ ያደረገው ኅብር ስኳር፣ የአቅም ማነስ ቢኖር በማሰብ ባንኮች ለባለ አክሲዮኖች የብድር አገልግሎት ማቅረባቸውን ይፋ አድርጓል። ባንኮቹም አዋሽ፣ ኦሮሚያ ኅብረት ሥራ፣ ንብ ኢንተርናሽናል እና ንግድ ባንክ ሲሆኑ፣ ለባለ አክሲዮኖች ያለመያዣ ብድር አቅርበዋል።
በተጨማሪም ከፍተኛ የድርሻ ሽያጩን በቀድሞ የወንጂ እና መተሃራ ፋብሪካዎች ላይ በኃላፊነት ያገለገሉ ሰዎች መግዛታቸውን ተናግረዋል።

‹‹መንግሥት የስኳር ፋብሪካ ውስጥ የመቆየት መብት የለውም። ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት ያለበት የቤት ሥራዎች አሉት›› እሸቱ ብለዋል።
አክለውም መንግሥት በዘርፉ ላይ ባሉ አካላት የማደናገር ሥራ ነበር ሲሠራ የነበረው፣ ከዚህ ቀደም በመንግሥት ስር እና ወደ ግሉ ዘርፍ ይዞራሉ ተብለው የተለዩትን ቀድሞ አለማሳወቁም በኅብረተሰቡ ዘንድ የመጠራጠር እና ተአማኒነቱን የመቀነስ ችግር እንዲፈጠር አድርጎ ነበርም ብለዋል።

የመተሃራ እንዲሁም የወንጂ የስኳር ፋብሪካዎች፣ በሆላንድ ኤች ቪ በተሰኘ ኩባንያ የተቋቋሙ ሲሆኑ፣ ወንጂ አንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ኩንታል እና መተሃራ አንድ ነጥብ ኹለት ሚሊዮን ኩንታል ያመርታሉ።

የገንዘብ ሚኒስትር አማካሪ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር)፣ ሦስት የስኳር ፋብሪካዎች ተለይተው በመንግሥት ስር ይቆያሉ መባሉን መንግሥት አያውቀውም፣ ሐሰት ነው ሲሉ አስተባብለዋል። እርሳቸው እንደሚሉት ከዚህ ቀደም እንደተጠቀሰው ስድስት የስኳር ፋብሪካዎች ቀድመው ለጨረታ እንደሚቀረቡ እና የተቀሩት በደረጃ እንደሚወጡ የሚቀጥል ሲሆን፣ የተቀየረ ነገር አለመኖሩን ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 71 መጋቢት 5 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here