በኃይል አቅርቦት አደጋ ውስጥ የገቡት የክትባት ዘረመሎች መፍትሄ አገኙ

0
1331

ለኢትዮጵያ እንዲሁም ለተለያዩ አገራት የእንስሳት መድኃኒቶችን እና ክትባቶችን የሚያመርተው የብሔራዊ እንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት፣ በኃይል እጥረት የዘረመል ባንኩ ላይ ለረጅም ጊዜ ሲያጋጥመው የነበረው ችግር መፈታቱን አስታወቀ።

በቢሾፍቱ ከተማ የሚገኘው የምርምር ማእከሉ፣ የተዘረጋለት የኃይል መስመር አነስተኛ ኃይል መጠን የሚይዝ በመሆኑ ኃይል እየተቋረጠ በመቸገሩ፣ ይህንንም ለመቋቋም ለአንድ ዓመት ያህል የ24 ስዓት ጀነሬተር ሲጠቀም እንደቆየ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ማርታ ያሚ (ዶ/ር) ገልጸዋል። አሁን ላይ ችግሩን ለመቅረፍ ድርጅቱ በ306 ሚሊዮን ብር ትራንስፎርመር ገዝቶ የመብራት የመስመር ዝርጋታ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

እስከ አሁን ምርት በማምረት ላይ ያለው ፋብሪካው፣ በመብራት መቆራረጥ ምክንያት የማሽኖች ብልሽት አስተናግዷል። ከዚህም ባሻገር ከተመረቱ መድኃኒቶችን መካከል አንዳንዶቹ በማቀዝቀዣ ፍሪጅ ውስጥ መቀመጥ የሚያስፈልጋቸው ስለነበሩ፣ መብራት በመቆራረጡ ምክንያት ከአገልግሎት ውጭ የመሆን ችግር አጋጥሞት እንደነበር ኃላፊዋ ተናግረዋል።
ኢንስቲትዩቱ ለአንድ ዓመት የጀነሬተር ኃይል ሲጠቀም መቆየቱ ለከፍተኛ ወጭ እንደዳረገውም ገልጸዋል። ለዚህም በቀን 200 ሊትር ነዳጅ ይጠቀም የነበረ ሲሆን፣ በገንዘብ ሲሰላ ኢንስቲትዩቱ በቀን አራት ሺሕ ብር ያወጣ እንደነበር ማርታ አስታውሰዋል።

ከዚህ ቀደም በ2011 ሥራ ይጀምራል ተብሎ እቅድ የተያዘለት ማምረቻ ማሽን፣ በመብራት ኃይል አቅርቦት ምክንያት እስከ አሁን ሥራ ሳይጀምር የቆየ ሲሆን፣ ከአንድ ዓመት በፊት የእንስሳት መድኃኒት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ፕሮጀክት ግንባታ አጠናቆ ነበር። ለፋብሪካዉ የሚያስፈልጉ ማሽኖች ቢተከሉም፣ በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እጦት ምክንያት የሙከራ ምርት ሊመረት እንዳልተቻለና ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የፊንፊኔ ዙሪያ ዲስትሪክት ጥያቄ አቅርቦ ሲከታተል ቆይቶ ምላሽ አግኝቷል።

አዲሱ የመድኃኒት ማምራቻ ፋብሪካ የመብራት ዝርጋታዉ እንደተጠናቀቀ ወደ ምርት የሚገባ ሲሆን፣ 11 ዓይነት የእንስሳት መድኃኒቶችን ለገበያ እንደሚያውልም ማርታ ተናግረዋል።
ኢንስቲትዩቱ 23 ለሚሆኑ የእንስሳት በሽታዎች መከላከያነት የሚውሉ ክትባቶችን በማምረት ላይ ይገኛል። እንዲሁም በዓመት እስከ 298.72 ሚሊዮን ዶዝ ክትባቶችን እያመረተ ለገበያ ያቀርባል። በአጠቃላይ 338 ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፣ ከነዚህም ውስጥ ወንድ 214 ሴት 124 ናቸው። በ2011 የበጀት ዓመትም 270.2 ሚሊዮን ዶዝ በአገር ውስጥና 16 ሚሊዮን ዶዝ ወደ ውጭ አገር በመላክ፣ 145 ሚሊዮን ብር ከአገር ውስጥ 19.3 ሚሊዮን ብር ከውጭ ሽያጭ ገቢ ማግኘት ችሏል።

ከእንስሳት መድኃኒትና መኖ ቁጥጥር አስተዳደር ባለሥልጣን ፍቃድ አሰጣጥና ምዝገባ ዳይሬክቶሬት በ2011 በጀት ዓመት ፍቃድ ተሰጥቷቸው የገቡ ጠቅላላ ክትባቶች፣ በበጀት ዓመቱ በገንዘብ 254 ሺሕ የአሜሪካን ዶላር ሲሆን በኢንስቲትዩቱ ተመርተው ለገበያ የቀረቡ 1.4 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ነው። በአገር ውስጥ 22 ዓይነት የክትባት ዓይነቶች ለሽያጭ አቅርቦ፣ የዶሮ ክትባቶች ከፍተኛውን ድርሻ ይዘዋል።ኢንስቲትዩቱ ዋነኛ ሥራዉ የእንስሳት መድኃኒትን ማቀነባበር ሲሆን፣ አዲስ ኢንቨስትመንት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ በ100 ሚሊዮን ብር አስገንበቶ አጠናቋል። ተቋሙ ተገንብቶ ያለቀውን ፋብሪካ የመድኃኒት ማምረት ሥራ ለማስጀመር በሰው ኃይል አደረጃጀት ተገቢውን ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ የኢንስቲትዩቱ የሕዝብ ግንኙነት አወል አብዱልጀበር ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 71 መጋቢት 5 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here