ፕራይም የተሰኘ አዲስ የቴሌቪዥን ጣቢያ የሙከራ ስርጭት ጀመረ

0
422

‹‹የኛ ሚዲያ በምክንያት የሚወግን ይሆናል››

ፕራይም ሚዲያ የተባለ አዲስ የቴሌቭዥን ጣቢያ ከብሮድካስት ባለሥልጣን ፈቃድ ተሰጥቶት ረቡዕ መጋቢት 2/2012 የሙከራ ስርጭቱን ጀመረ።
ጣቢያው መደበኛ ስርጭቱን ሲጀምር የሚጠቀመው የስርጭት ቋንቋ ስዋሂሊን ሲሆን፣ በተጨማሪ በምሥራቅ አፍሪካ ብዙ ተናጋሪ ያላቸው ቋንቋዎች እንደሚሆን አስታውቋል። ብርሃኑ ሌንጂሶን ጨምሮ አራት ግለሰቦች በመሠረቱት ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ በ100 ሚሊዮን ብር የተቋቋመ ነው። ወደፊት ድርሻ መሸጥ እንደሚኖር የተጠቆመ ከመሆኑ ባሻገር፣ ይህም ጣቢያው የጥቂት ሰዎች እንዳይሆን በማሰብ ነው ተብሏል።

መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገው ይህ የቴሌቭዥን ጣብያ፣ ትኩረቱን የሚያደርገው ኅብረተሰቡን ማስተማር እና የግንዛቤ ለውጥ መፍጠር ላይ ነው ሲሉ የጣቢያው ዋና ሥራ አስኪያጅ ብርሃኑ ሌንጄሶ ተናግረዋል። ነገር ግን ማካተት ያለበት የመዝናኛ ሰዓትም ይኖረዋል ብለዋል።

አዲስ የሚዲያ ተቋም መክፈት ያስፈለገበት ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሚድያ ይዘት በመቃወም መሆኑን ገልፀው፣ ‹‹አብዛኛው የአገራችን ሚዲያዎች ወገንተኛ ናቸው። ይህም በብሔር፣ በፖለቲካ፣ በሃይማኖት እና በሌሎች ማኅበረሰባዊ ጉዳዮች ላይ ወገንተኝነትን የሚያንፀባርቁ ብቻ ናቸው›› ይላሉ። አክለውም ‹‹የኛ ሚዲያ በምክንያት የሚወግን ይሆናል›› ሲሉ ብርሃኑ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

እንደ አገር የሚዲያ ተግባር እና ኃላፊነት ያልገባቸው ሰዎች፣ የኔ ወገን ተነካ እኔ ተሰደብኩ በማለት ለዛ መልስ መስጫ መሣርያ አድርገውታል። ይህም በግልፅ የሚታይ የኢትዮጵያ ሚድያ ችግር ሆኗል ሲሉም ለጣቢያቸው መመሥረት ምክንያት ያስረዳሉ።

የሙከራ ሰርጭቱን ተከትሎ ስድስት ሰዎችን የቀጠረው ፐራይም ሚዲያ፣ ስርጭቱ ለ24 ሰዓት እንደሚሆን የገለፀ ሲሆን፣ የሙከራ ስርጭቱን አገባዶ ሙሉ በሙሉ ስርጭቱ በአንድ ወር ውስጥ እንደሚጀመርም ተናግረዋል።

የብሮድካስት ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት ግብረጊዮርጊስ አብረሃ በበኩላቸው፣ የብሮድካስት ባለሥልጣን አንድ አዲስ ሚዲያ ተቋም ፍቃድ ሊወስድ ሲል ማሟላት ይገባዋል ብለን የምናወጣቸውን መስፈርቶች አሟልቶ መገኘቱን በማረጋገጥ ፈቃድ የሚሰጥ ተቋም ነው ብለዋል።

ነፃነት ኃይሉ የሚዲያው ዋና አዘጋጅ ሲሆኑ፣ መምህር እና የተግባቦት ባለሞያ የሆኑት ታጠቅ ከበደ፣ የቴሌቪዥኑ ባልደረባ መሆናቸው ተገልጿል።
በዚህም መሠረት የሥራ እቅዳቸውን በመመልከት በእቅዳቸው ውስጥ ምን ምን ተካተተ የሚለውን ተመልክቶ ዓላማውን መለየት፤ በመቀጠል ሚዲያ ተቋሙ የሚጠቀምበትን መሣርያ ዘመናዊነት መመዘን፤ ካፒታላቸውን እና የካፒታሉ መነሻ ምንጭ በዋነኛነት መገምገም፤ ከሚዲያ ጋር ያላቸውን ቅርበት እና ስለ ሚዲያ ያላቸው እውቀት፣ ከዛም በዘለለ እቅዳቸውን በመመልከት ያስቀመጡትን አቅጣጫ ምን አይነት ነው የሚለው ታይቶ እንደሚሰጥ አስረድተዋል። ብሮድካት ባለሥልጣኑ ፕራይም ለተባለ አዲስ የቴሌቭዥን ጣቢያም ከኹለት ወር በፊት ፈቃድ እንደሰጠም ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 71 መጋቢት 5 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here