የአገር ሉዓላዊነትና ክብር አንድም በአገር መሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ ይገለጣልና፣ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የአባይ ወንዝ ላይ እየተሠራ ስላለው የሕዳሴ ግድብ ድርድር በሚመለከት የአሜሪካ አኳኋን እንዳልተዋጠላት ኢትዮጵያ በግልጽ አሳይታ ነበር። በዚህም ላይ የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወደ ኢትዮጵያ በመጡ ጊዜ ለተደረገላቸው አቀባበል ያሳዩት ግብረ መልስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ማስቆጣቱ የሚታወስ ነው። ይህም ኢትዮጵያ ጥቅሟን በማክበር በኩል እንደማትደራደርም ሆነ እንደማትንበረከክ ማሳያ ሆኖ ተወስዷል። አዲስ ማለዳም በዚህ ላይ አቋም ይዛ በርዕሰ አንቀጿ አስነብባለች። ግዛቸው አበበ ይህን መነሻ በማድረግ ተከታዩን ብለዋል።
የአሜሪካ ፕሬዝደንት የነበሩት ባራክ ኦባማ በወርሐ ሐምሌ 2007 አፍሪካን በጎበኙበት ወቅት፣ በኬንያ ተወሰዱ የተባሉ አንዳንድ እርምጃዎችን በመጥቀስ፣ ‹ኬንያ ለአሜሪካ/ለኦባማ አስተዳደር ተንበረከከች› የሚል አቋም በአዲስ ማለዳ ጋዜጣ ላይ ተንጸባርቋል። ከዚህ በመነሳትን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ለመንበርከክ በአባይ ጉዳይ አሻፈረኝ ባይ መሆን እንደሌለበት አደራ በማለት፣ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ማይክ ፖምፒዮ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ በተገኙበት ወቅት የታየን አንድ ገጠመኝ በማንሳት ‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ አይንበረከኩም!› ለማለት ይሞክራል። ያድርግልን!!
‹‹መቼም ቢሆን በጫና አንንበረከክም!›› በሚል ርዕስ ስር በአዲሰ ማለዳ ጋዜጣ ቅጽ 2፣ ቁጥር 68 (የካቲት 12/2012 ዕትም) ላይ ለንባብ የቀረበው ይህ ጽሑፍ፣ የኬንያን በጫና መንበርከክ ማሳይ አድርጎ የተለያዩ ኹነቶችን ጠቅሷል። በዚህም ባራክ ኦባማን ይዞ የመጣው ‹ኤር-ፎርስ ዋን› የተባለ የፕሬዝዳንቶች አውሮፕላን ወደ ኬንያ አየር ክልል ለመግባት ከተቃረበበት ጊዜ ጀምሮ ኬንያ የአየር ክልሏን ሌሎች በረራዎች ለአንድ ሰዓት ያህል መዝጋቷን፣ ኦባማ ኬንያን እየጎበኙ በነበሩባቸው ቀናት ከ20 ሺሕ ጫማ በታች በረራዎች እንዳይደረጉ መከልከሏና ኦባማ ከኬንያ ሲወጡ ደግሞ ለ40 ደቂቃዎች የአየር ክልሏን መዝጋቷ ነው።
በእርግጥ ይህ የጥንቃቄ እርምጃ እንጂ የመንበርከክ ጉዳይ ነው ለማለት በጣም አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም ኬንያ ኦባማ ወደ ምድሯ ከመግባታቸው በፊት ለበርካታ ዓመታት ጥቂት የማይባሉ ከፍተኛ የሽብር ጥቃቶችን ያስተናገደች፣ የብዙ ዜጎቿን ጨምሮ የውጭ ዜጎች ሕይወት የተቀጠፉባት አገር ናት። ‘የዓለሚቱን ጠባሳ ያዬ በእሳት አይጫወትም!’ ይባላልና. እኛ ኢትዮጵያውን የሌላ አገር መሪ ለጉብኝት ጎራ ሲል ከፍተኛ ጥንቃቄ የሞላበት ጥበቃ ሲደረግ ለምን እንደሆነ የሚገባን ሕዝቦች ነን። ምክንያቱም በደርግ ዘመን አዲስ አበባ ላይ በተካሄደ የአፍሪካ አንድነት ስብሰባ ላይ፣ የሊቢያው መሪ ኮሎኔል ሙአመር ጋዳፊ አንድን የአፍሪካ አገር መሪ አፍነው ለመውሰድ ሙከራ ማድረጋቸው፣ የሊቢያ ኮማንዶዎችና ከኢትዮጵያ ኮማንዶዎች ጋር ግብግብ ገጥመው የጋዳፊ ተገቢ ያልሆነ ድርጊት መክሸፉን እናውቃለን።
ከዚህ ሌላ በዘመነ ሕወሐት/ኢሕአዴግ የግብጹን መሪ ሆስኒ ሙባረክን ለመግደል በቦሌ መንገድ ላይ ሙከራ ተደርጎ ጭነውት በመጡት ጥይት በማይበሳው መኪናቸው ጋሻነት፣ እንዲሁም በጠባቂዎቻቸው፣ በኢትዮጵያ የደኅንነትና የጸጥታ ኃይሎች ከፍተኛ ርብርብ ሕይወታቸው ተርፎ እዚያው ተኩሱ በተከፈተበት ቦታ ላይ ቀኝ ኋላ ዞረው ወደ አገራቸው መመለሳቸውም የሚዘነጋ አይደለም። በዕለተ ማክሰኞ የካቲት 16/2012 ማረፋቸው የተሰማው ሆስኒ ሙባረክ፣ ተአምር በሚባል ሁኔታ ከሞት የተረፉት መንገድ ዘግተው ተኩስ ከከፈቱባቸውና በሕንጻዎች አናት ላይ ሆነው ቁልቁል ጥይት ከሚያርከፈክፉባቸው በርካታ አጥቂዎቻቸው ሁሉ ነበር። ከዚህ በኋላ የውጭ እንግዳ ሲመጣ ብቻ ሳይሆን፣ የእኛዎቹ ባለሥልጣናትም በቦሌና በሌሎች መንገዶች ሲተላፉም ጭምር በሕንጻዎች ላይ ታጣቂዎች መታየታቸው እንደቀጠለ ነው።
ታኅሳስ 1973 ናይሮቢ የሚገኘውና የታዋቂ አይሁዳዊ ንብረት የሆነው ኖርፎክ ሆቴል የቦምብ ጥቃት ደረሰበት። ጥቃቱ የተለያዩ አገር ዜጎች የሆኑ 20 ሰዎችን ገድሎ 87 አቆሰለ። የሆቴሉ ምዕራባዊ ክፍልም በከፍተኛ ደረጃ ወደመ።
ነሐሴ 1990 በቦምብ የታጨቀ መኪና የተጠቀመ አጥፍቶ ጠፊ ናይሮቢ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ላይ ጥቃት አድርሶ 12 አሜሪካውንን ጨምሮ 213 ሰዎችን ለሕልፈት ዳርጎ ወደ 4 ሺሕ ሰዎችን አቁስሏል። ይህ ጥቃት እስከ 17 ቶን የሚደርስ ፈንጅ ጥቅም ላይ የዋለበትና ከአሜሪካ ኤምባሲ አልፎ በአካባቢው የነበረን ሌላ የኮሌጅ ሕንጻ ያወደመ ነበረ። ከሟቾቹ ብዙዎቹም የኮሌጁ ተማሪዎችና ሠራተኞች ናቸው።
ኅዳር 1995 የእስራኤሉ አሪካ አየር መንገድ ንብረት የሆነ ቦይንግ 757 አውሮፕላን፣ ከሞምባሳው ሞይ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በመነሳት ላይ እያለ ኹለት ስትሬላ ሚሳይሎች ተተኮሱበት። ሚሳይሎቹ ዒላማቸውን ስለሳቱ የተሳፋሪዎችና የአውሮፕላኑ ሠራተኞች ሕይወት ተረፈ። አሪካ አየር መንገድ በቻርተር በረራ፣ በየሳምንቱ ከቴልአቪቭ ሞምባሳ ቱሪስቶችን የሚያመላልስ ኩባንያ ነበር።
ኅዳር 1995 የአፍሪካ አየር መንገድ ቦይንግ ከጥቃት ባመለጠበት ዕለት፣ በተቀነባበረ ጥቃት እስራኤላዊ ቱሪስቶችን በማስተናገድ የሚታወቀው ኪካምባላ ሆቴል የሽብር ጥቃት ደረሰበት። ጥቃቱ የተሰነዘረው ሆቴሉ ከእስራኤል የመጡ 60 ቱሪስቶችን በመቀበል ላይ በነበረበት ወቅት ሲሆን፣ በጥቃቱ 13 ሰዎች ተገድለው 80 ቆስለዋል። በጥቃቱ ከሞቱት ውስጥ ለእንግዶቹ ባህላዊ ውዝዋዜ ለማሳየት በቦታው የተገኙ እና በሆቴሉ ተቀጥረው የሚሠሩ ዐስር ኬንያውያን ይገኙበታል።
መስከረም 1996 ናይሮቢ ውስጥ በሚገኘው ዌስት-ጌት የገበያ ማዕከል ላይ በተፈጸመ የእሩምታ ተኩስ የሽብር ጥቃት 67 ሰዎች ተገደሉ።
ሰኔ 2006 ለኹለት ቀናት ላሙ በሚባለው አካባቢ በሚገኙ መንደሮች፣ ከተሞችና በዙሪያቸው ተኩስ እየተከፈተ ብዙዎች ተገደሉ። በጥቃቱ እስከ 50 የሚደርሱ ጭንብል ያጠለቁ ታጣቂዎች ተካፍለውበታል። አብዛኞቹ የኪኩዩ ጎሳ አባላት የሆኑ ከ60 በላይ ሰዎችም ተገድለዋል። አል-ሸባብ ለጥቃቱ ኃላፊነት ቢወስድም፣ ኡሁሩ ኬንያታ ጥቃቱ የኬንያ ፖለቲከኞች የወመኔዎችን ኔትወርክ ተጠቅመው ያስፈጸሙት፣ በዘር ወይም በሐይማኖት ልዩነት ላይ የተመሰረተ፣ ከመሬት ንጥቂያ ጋር የተያያዘ ጥቃት ሳይሆን እንደማይቀር ተናግረዋል። ጥቃቱ ወደተገኘው ሰው ሁሉ ተኩስ በመክፈት መግደልን ጨምሮ ቤቶችን፣ ሆቴሎችን፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን በማቃጠል ተካሂዷል። አጥቂዎች የተጠለፈ መኪና ተጠቅመው የአካባቢውን ፖሊሰ ጣቢያ አጥቅተዋል።
ኅዳር 1997 ማንዴራ ውስጥ በሚገኘው ኦማር-ጅሎ በሚባል አካባቢ ታጣቂዎች አውቶብስ ጠልፈው፣ ሙስሊም ያልሆኑ 28 ተሳፋሪዎችን ረሽነዋል። ከዐስር ቀናት በኋላ በዚሁ አካባቢ በተመሳሳይ መንገድ 36 ሰዎች ተገድለዋል።
ሚያዝያ 2007 ኦባማ ለጉብኝት ወደ ኬንያ ጎራ ሊሉ ጥቂት ወራት ብቻ ሲቀራቸው፣ የአል-ሸባብ ታጣቂዎች ጋሪሳ ዩንቨርሲቲን በመውረር ወደ 150 ሰዎችን ሕይወት ቀጥፈው በርካቶችን አቁስለዋል። በወቅቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች በታጣቂዎቹ ታግተዋል።
ጥቅምት 2004 የኬንያ መንግሥት ከሶማሌ መንግሥት ጋር ተባብሮ አል-ሸባብን ለመውጋት ጦሩን ወደ ሶማሊያ ካስገባበት ጊዜ ጀምሮ ኬንያ በርካታ የሽብር ጥቃቶችን አስተናግዳለች። የአሜሪካው ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ኬንያን በሚጎበኙበት ወቅትና ከዚም በኋላ የሽብር ትቃቱ አላቋረጠላትም። ስለዚህ ኬንያ በዓለም መድረክ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጣው ብቻ ሳይሆኑ በደም ትስስር ቤተሰብ የሚባሉት ኦባማ ወደ ምድሯ ሲገቡ ከፍተኛ ደረጃ ጥንቃቄ ማድረጓ በጣም ተገቢ ነበር።
ነገር ግን ለኦባማ አስተዳደር የተንበረከኩትንና ያልተንበረከኩትን መለየት የምንችለው ‘ኦባማ ወደ አፍሪካ ለምን መጡ?’ ብለን ከጠየቅን በኋላ እንደገና ‘ያሰቡትንስ አሳኩ ወይስ አላሳኩም?’ ብለን ጠይቀን መልሱን ስናገኝ ነው። የኦባማ ጉብኝት በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ለመምከርና ሽብርን በመዋጋቱ ትብብርን ለማጠናከር መሆኑ በይፋ የተነገረ ቢሆንም፣ ፕሬዘዳንቱ በአፍሪካ ጉብኝት ለማድረግ ማቀዳቸውን ተከትሎ ‘Blunt Message’ ያሉትን አንድ መልዕክት ለአፍሪካ መሪዎች ለማስተላለፍ ቆርጠው መነሳታቸውንም አሳውቀው ነበር።
መልዕክቱም የአፍሪካ መሪዎች የሰዶማውያንን መብት እንዲያከብሩና ሰዶማውያንን የሚያገል አካሄዳቸውን እንዲቀይሩ ማሳሰብ ነው። የኦባማ ጉብኝት ዓላማ ይህን እንደሚያካትት መሰማቱን ተከትሎ ኬንያ ውስጥ ከፍተኛ ጉርምርምታ ተፈጥሮ ቆይቷል፤ የኬንን መሪዎችንም አበሳጭቷል። ኦባማ ወደ ኬንያ ሲንቀሳቀሱም በዚህ ጉዳይ ላይ በአደባባይ ከመናገር አንዲቆጠቡ የወተወቱ የኬንያ ማኅበረሰብ መሪዎች ነበሩ። በኬንያ ሕግ መሰረት ሰዶማዊነት እስከ 14 ዓመት የሚያሳስር ወንጀል ነው።
ኦባማ ግን ከኡሁሩ ኬንያታ ጋር ለጋዜጣዊ መግለጫ በቆሙበት ወቅት የሰዶማውንን መብት ማክበረ እንደሚገባ፣ ሰዶማውያንን ማግለል በአሜሪካ ጥቁሮች ሲገለሉበት ከነበረው ሁኔታ ጋር እንደሚመሳሰልና ይህም በጣም የሚያበሳጫቸው መሆኑን ተናገሩ። ሰዎች ሌሎችን እስካልጎዱ ድረስ የፈለጉትን የሕይወት መንገድ እንዲከተሉ የማንፈቅድ ከሆነ ነጻነት ይሸረሸራል ሲሉም አሳሰቡ። ሌላም ሌላም ነገር አብዝተው ተናገሩ።
ኦባማ መልዕክቱን በማስተላለፍ ላይ እያሉ የኡሁሩ ኬንያታ ገጽታ መለዋወጡንና ኦባማን የሚያዩበት ሁኔታ ከመከፋት አልፈው መቆጣታቸውን የሚያሳብቅ መሆኑን መገናኛ ብዙኀን በምስል አስደግፈው ዘገባ ሰርተውበታል። የኡሁሩ ኬንያታ ተቃውሞ በዚህ የተገደበ አልነበረም። ሰዶማዊነት የኬንያውያን ጉዳይ አለመሆኑን፣ የኬንያ ማኅበረሰባዊ እሴትና ባህሉ ይህን ጉዳይ የማያስተናግድ እንደሆነ፣ ነገር ግን ኬንያ ከአሜሪካ ጋር ልትጋራቸው የምትችል ብዙ የዴሞክራሲና የሥልጣን እሴቶች እንደሚኖር ተናግረዋል። ኡሁሩ ኬንያታ ሰዶማዊነት ግን ከእነዚህ ውስጥ የሚደመር እንዳልሆነ አስረግጠው አስረድተዋል።
የኬንያ ምክትል ፕሬዘደንት ዊልያም ሩቶ፣ የኬንያ ፓርላማ አፈ ጉባኤ፣ የሐይማኖት መሪዎችም በያገኙበት አጋጣሚ የኦባማን ውትወታ የሚቃወም ንግግር አሰምተዋል፣ አስተያየትም ሰንዝረዋል።
ስለዚህ ኬንያ ካላት ተሞክሮ አንጻር ለእንግዳዋና ለልጅዋ የላቀ የደኅንነት ጥንቃቄ ብታደርግም፣ ኦባማ በማይሆን መንገድ ሲመጡ ግን ኬንያውያን ባለሥልጣናት የአገራቸውንና የሕዝባቸውን ክብርን እናስጠብቅበታለን ባሉት መንገድ፣ ከኦባማ ጋር ተቃራኒ የሆነ አቋማቸውን ከማሳወቅ ወደ ኋላ አላሉም።
ኢትዮጵያችን ሶዳማዊነትን ከኃጢያት የሚፈርጁትን ሦስቱንም የአብርሐም የሚባሉት ሐይማኖቶች ማለትም አይሁድነትን፣ ክርስትናን እና እስልምናን ከብዙ አገራት ቀድማ የተቀበለችና ያስተናገደች አገር ናት። የኦባማ መንግሥት የሰዶማውያንን መብት በዓለም ዙሪያ ማስከበር የሚል ዘመቻ ጀምሮ፣ ይህን ዘመቻ ለማሳካት ፓትሪሻ ሐስላች የተባለች አምባሳደር ወደ ኢትዮጵያ ልኮ ነበረ። አምባሳደሯ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቷ በፊት፣ ዋና ተልዕኮዋ በኢትዮጵያ የሰዶማውያን መብት እንዲከበር መሥራት መሆኑን፣ በኢትዮጵያ ሰዶማዊነት ወንጀል መሆኑ እንዲቀር ጥረት ማድረግ መሆኑን ቪኦኤ በአማርኛው ፕሮግራም ላይ ቀርባ ተናግራ ነበር።
ሴትዮዋ ይህን ነገር በይፋ የተናገረችው እዚህ የሚፈጠረውን የልብ ትርታ ለመለካት እንደሆነ ይታመናል። የኢትዮጵያ መንግሥት ከሕጉ፣ ከሕዝቡ እምነትና ባህል ጋር አብሮ የማይሄደውን ይህን ጉዳይ በሚመለከት በማን አለብኝነት ጣልቃ ለመግባት የዛተችውን አምባሳደር ወደ ኢትዮጵያ እንዳትመጣ አልከለከለም። በአገሪቱ ሚሊዮኖችን የሚመለከቱና የሚጣሱ ብዙ መብቶች እያሉ ለጥቂቶች መብት መቆም ነው ተልዕኮዬ የምትል አምባሳደር ስትመጣ፣ የማይቃወሙ ተቃዋሚዎች መኖራቸው አሳዛኝ ነገር ነው። ነጻ ጋዜጠኞች ነን ባዮችና የኢትዮጵያ ጉዳይ ስለሚመለከተን እንጦምራለን ባይ ሰዎች፣ ቻይና የማይሠራ ዲቫይደር እየላከችብን የኤሌክትሪክ ንብረቶቻችን ተቃጥለው አለቁብን እያሉ እያማረሩ የሰዶምና ጎሞራ ከተሞች ሕዝቦች ተቃጥለው ጠፍተውበታል የሚባለው ‹ጸባይ› እንዲስፋፋና እንዲበረታታ ሲሠራ ትንሽም ትንፍሽ አለማለታቸው የምዕራቡ ዓለም የሸልማት ድርጅቶችም የምዕራቡ ዓለም ጋዜጠኞች የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ምን ያህል ኃይለኛ መሆኑን የሚያሳይ ነው።
ሴትዮዋ ወደ ኢትዮጵያ መጥታ የሥራ ዘመኗን ጨርሳ እስክትመለስ፣ እሷን በመቃወም ሐሳቡን የሰነዘረ ወይም ምን እየሠራች ነው ብሎ ተከታትሎ እሷን ለማቆም የሞከረ የኢሕአዴግ ባለሥልጣን፣ የተቃዋሚ ቡድን መሪ፣ የመንግሥት ጋዜጠኛ፣ የግል ጋዜጠኛ፣ የሐይማኖት መሪ፣ ጦማሪ አልነበረም። አምባሳደሯ ላሊበላን ከአደጋ ለመታደግ እያለች ወደ ላሊበላ ስትመላለስና ላይና ታች ስትልም፣ የሚያጨበጭብ እንጂ ‘እርኩሱ በቅዱሱ ቦታ ቆመ’ ብሎ የተከፋ ያለ አይመስልም። እሷ የሠራችው የአደጋ መከላከያ አሁን ራሱ በላሊበላ ላይ አደጋ ደቅኖ ማየታቸው ላይቀር፣ እሷን አጨብጭበው የተቀበሉ ሐይማኖት አለን የሚሉ የፖለቲካ ባለሥልጣናት፣ ጳጳሳት፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት፣ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች ወዘተ… ለምን ዝምታን መረጡ?
ምርጫ 2002 ላይ ለውድድር ቀርበው ከነበሩ ፓርቲዎች በኢቲቪ ላይ የምረጡኝ ዘመቻ ሲያካሂዱ፣ ሰዶማዊነት እንዳይስፋፋ አሠራለሁ ብሎ አቋሙን በግልጽ ያስቀመጠ አንድ ብዙም የማይታወቅ ፓርቲ ብቻ ነበር። እሱም ከኢራፓ ወይም ከአትፓ አንዳቸው ነው። በኢትዮጵያችን የፖለቲካና የመገናኛ ብዙኀን ሰዎች፣ ጦማሪዎችና አክቲቪስቶች ወዘተ… ከአሜሪካ የመጣን ነገር ሁሉ እንዳለ መቀበልን ወይም ለአገርና ለወገን ሲባል፣ ለባህልና ለዕምነት ክብር ሲባል መቃወም ሲገባ፣ ማድፈጥን እንደ ጠቃሚ ነገር አድርገው የሚያዩት ይመስላሉ።
ለምን? ብዙዎች አሜሪካና አውሮፓ ከሚኖሩ ከስደተኞች እርዳታን ጠባቂ ስለሆኑ ከእነሱው መመሪያ ስለሚቀበሉ። ወይም የምዕራባውያኑን የሽልማት ድርጅቶች ትኩረት ለመሳብ አልያም በአሜሪካና በአውሮፓ መንግሥት ዕርዳታ ሥልጣንና ገንዘብ እናገኛለን ብለው ወይስ ሌላ? ራሳቸው ያውቃሉ። እንዲያው ብቻ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ተስማምተው መኖሩን፣ እንደ ምዕራቡ ዓለም ማሰቡን ይመርጣሉ።
አንድ ሰሞን ቻይናዎች የአህያ ቄራ ኢትዮጵያ ውስጥ በከፈቱበት ጊዜ ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞች፣ ጦማሪዎች ወዘተ…. አብዝተው ሲቃወሙ ይሰሙ ነበረ። ከሚቃወሙት ጥቂቶቹ ጉዳዩን ሐይማኖታዊ አድርገውት ‘እምነት የለሾቹ ቻይናዎች በቅዱሱ ምድራችን ርኩስ እንስሳ እያረዱ አገራችንን አረከሱ’ የሚል ዓይነት እሮሮ ያሰሙ ነበሩ። እነዚህ ሰዎች በኦሪት ቅዱሳን መጽሐፍት የተጻፈውን ነገር እያስታወሱ እሮሮ ማሰማታቸው መሆኑ የታወቀ ነው። ነገር ግን በአገራችን አሳማ አርብተው ለገበያ የሚያቀርቡና አሳማ አርደው ለምግብነት የሚያውሉ ሰዎች መኖራቸውን፣ የአሳማ ስጋ ውጤቶች የሚያቀርቡ ሆቴሎችና ሱፐር ማርኬቶች መኖራቸውን ቢያውቁም ቅዱሳን መጽሐፍቱን አስታውሰዋቸው አያውቁም።
ለምን? አሜሪካና አውሮፓ አሳማ ታርዶ ስለሚበላ ነዋ። ሥጋን ግን መሰረት አድርገው ስለ ጽድቅና ስለ ኩነኔ የተፈላሰፉ ወገኖቻችን ሰዶማዊነትን አስመልክተው መፈላሰፍ አልፈለጉም። ለምን? አሜሪካና አውሮፓ የሚሆነውና የሚደረገው ነገር ሁሉ በኢትዮጵያ መደረግ አለበት የሚል አስተሳሰብ ሰፍኖ ይሆናል!
ለመሆኑ ባራክ ኦባማ የአሜሪካ ፕሬዘደንት በሆኑበት ወቅት ወደኋላ እየተመለሰ ያለው የጥቁሮች ነጻነት ጉዳይ ችላ ብለው፣ በብዙ የአሜሪካ ግዛቶች በታጣቂነት እየተደራጁ ጸረ-ጥቁርና ጸረ-ሙስሊም አቋም የሚያራምዱትን ያላዩ መስለው አልፈው፣ ለጥቂት ሰዶማውያን ጠበቃ መሆኑን የፈለጉት ለምንድን ነው? በአሜሪካ የጦር መሣሪያዎች እስከ ከፊል አውቶማቲክ ጠመንጃዎች እንደ ተራ እቃ እየተቸበቸቡ፣ የተለየ ዓላማ ያላቸው ግሰለቦች እያሰለሱ የአሜሪካን ትምህርት ቤቶችና ጎዳናዎች ወዘተ… የጦር ሜዳ ማስመሰላቸውን እንደ ቀላል ያዩትና መቆጣጠሪያ ሕግ ወይም ክልከላ ማስፈኑ ላይ ብዙም ሳይጨነቁ ስለ ሰዶማውያያ አብዝተው ተሟጋች የሆኑት ለምንድን ነው? የአገራችን ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ ጦማሪዎች፣ የሐይማኖት መሪወች፣ አክቲቪስቶች ወዘተ… ለራሳቸው ሊያቀርቧቸው ከሚገቡ ጥያቄወች ጥቂቶቹ እነዚህ ናቸው።
በነገራችን ላይ! የአገራችን ሕግ ልክ እንደ ኬንያው ሕግ ሰዶማዊነት ለረዥም ጊዜ እስር የሚዳርግ ወንጀል ቢሆንም፣ ‘የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ስለሆንኩ ሰዶማዊነትን አልቃወምም’ የምትል የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘደንት ያለን እኛ እንጅ ኬንያውያን አይደሉም።
ግዛቸው አበበ
gizachewabe@gmail.com
ቅጽ 2 ቁጥር 71 መጋቢት 5 2012