በሰዎች በመነገድ ወንጀል ሲፈለጉ የነበሩ ተጠርጣሪዎች አዲስ አበባ ተያዙ

0
811

በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እና በሌሎች ተያያዥ ወንጀሎች በዓለም ዐቀፉ የወንጀለኞች አዳኝ የፖሊስ ግብረ ኃይል (ኢንተርፖል) እና በአውሮፓ አገራት በጥብቅ ሲፈለጉ የነበሩ ኹለት ኤርትራውያን እንዲሁም አራት ኢትዮጵያውያን አጋሮቻቸው አዲስ አበባ በቁጥጥር ስር ዋሉ።

የኤርትራ ዜግነት ያላቸው ተጠርጣሪዎቹ ኪዳኔ ዘካሪያስ እና ዋሊድ ጎይቶም ኪሮስ አዲስ አበባ ውስጥ የተያዙ ሲሆን፣ በኔዘርላንድ እና ጣሊያን መንግሥታት በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ምርመራ ተጣርቶባቸው የሚፈለጉ መሆናቸው ተገልጿል።

ዋሊድ ጎይቶም የተባለው ተጠርጣሪ ከ15 ቀናት በፊት ኮልፌ አካባቢ የተያዘ ሲሆን፣ ኪዳኔ ዘካሪያስ የካቲት 03/2012 ላምበረት አካባቢ ከምሽቱ አራት ሰዓት ላይ ከአምስት ግብረ አበሮቹ ጋር በቁጥጥር ስር ሊውል ችሏል።

ተጠርጣሪዎቹ ሰዎችን በሊቢያ ወደ አውሮፓ አገራት በሕገወጥ መንገድ ሲያሻግሩ እና በጨረታ ለባርነት ሲሸጡ ከመቆየታቸውም በተጨማሪ፣ ተጓዦችን በማገት እና ቤተሰቦቻቸውን በማስፈራራት ከ 500 እስከ 600 ሺሕ ብር ሲቀበሉ መቆየታቸው ተጠቅሷል።

ሊቢያና ሱዳን ከሚገኙ ሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያላቸው ተጠርጣሪዎቹ፣ እስከ አሁን ከአምስት በላይ ሰዎች ሕይወት መጥፋት ተጠያቂ ናቸውም ተብሏል። ሌሎች 16 ተጎጂዎች ከተጠርጣሪዎቹ መያዝ በኋላ በሰውነታቸው ላይ የደረሰውን ጉዳት በማሳየት ምስክርነት የሰጡ ሲሆን፣ ከተጠርጣሪዎቹ መያዝ በኋላ ሌሎች ተጎጂዎች እንደሚመጡም ይጠበቃል።
ተጠርጣሪዎቹ ሥማቸውን በመቀያየር የሚንቀሳቀሱ ሲሆኑ፣ ኢትዮጵያ ውስጥም ገንዝብ የሚዘዋወርበት እና ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የሚፈፀምባቸው ሰፊ ሰንሰለቶች እንዳሏቸውም ታውቋል።

ከሕገወጥ የሰዎች ዝውውር በተጨማሪ ተጠርጣሪዎቹ በአስገድዶ መድፈር እና ተያያዥ ወንጀሎች እንደሚፈለጉም ለማወቅ ተችሏል። በአሁኑ ወቅት ሌሎች አንድ ሺሕ የሚሆኑ ሰዎች በኮንቴኔሮች ውስጥ በሊቢያ እንደሚገኙም በምርመራ ላይ የተሳተፉ ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ተጠርጣሪዎቹን ለመያዝ በተደረገው ክትትል ላይ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ ፌዴራል ፖሊስ እና የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ኤጀንሲ ተሳትፈውበታል። በአጠቃላይ ክትትሉ አንድ ወር የወሰደ ሲሆን፣ ዋሊድ ጎይቶም ኪሮስ በተጠርጣሪው ጉዳት የደረሰበት ግለሰብ ባደረገው ጥቆማ ሊያዝ ችሏል።

የኔዘርላንድ እና የጣሊያን መንግሥታት ተጠርጣሪዎቹ እንዲሰጧቸው ጥያቄ አቅርበዋል የተባለ ሲሆን፣ ተጠርጣሪዎቹ ፍርድ ቤት ቀርበው ጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል። ዋሊድ ሦስት ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረበ ሲሆን፣ ለሦስተኛ ጊዜ የምርመራ ጊዜ ተፈቅዷል።

ክትትሉ በከፍተኛ ምስጢር የተከወነ ከመሆኑ ተጨማሪ ተጎጂዎችን እና ምስክሮችን ለማግኘት ሲባል ይፋ እንዲወጣ ተደርጓል። የተጠርጣሪዎቹ መያዝ ኢትዮጵያ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ለምታደርገው ጥረት ትልቅ ስኬት መሆኑም ተገልጿል።

ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል የወጣው አዋጅ 900/2007 መሰረት ማንኛውም ሰው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የገንዘብ፣ ቁሳዊ ወይም ሌላ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ስደተኞችን በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ለማስገባትም ሆነ ከኢትዮጵያ ግዛት ለማስወጣት ሲል ድንበር ካሻገረ፣ ድንበር ለማሻገር ከሞከረ ወይም ድንበር ለማሻገር በዝግጅት ላይ ከሆነ፣ ከ15 እስከ 20 ዓመት የሚደርስ ፅኑ እስራትና ከብር 150 ሺሕ እስከ ብር 300 ሺሕ በሚደርስ መቀጮ እንደሚጣልበት ይደነግጋል።

በዚህ አዋጅ በአንቀጽ ሦስት ወይም አምስት የተመለከተው የወንጀል ድርጊት፣ በተጎጂው ላይ ከፍተኛ የአካል ጉዳት ወይም ሞት ያስከተለ እንደሆነ ወይም ወንጀል አድራጊው ድርጊቱን የፈፀመው የተደራጀ የወንጀል ቡድን አባል በመሆን ወይም ቡድኑን በመምራት ወይም በማስተባበር እንደሆነ፣ ወይም ወንጀሉ የተፈጸመው በስፋትና በብዛት እንደሆነ፣ እንደነገሩ ሁኔታ ቅጣቱ የእድሜ ልክ ፅኑ እስራት ወይም ሞት ይሆናል።

ቅጽ 2 ቁጥር 71 መጋቢት 5 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here