አቢሲኒያ ባንክ በኢትዮጵያ የባንክ እንዱስትሪ ታይቶ የማይታወቅ የሠራተኞች የደሞዝ ጭማሪ አደረገ። የተደረገው የሠራተኛ ደሞዝ ጭማሪ በቅርቡ ንግድ ባንክ ካደረገው ጭማሪ በላይ ነው።
የቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ መነሻ ደሞዝ የደረጃ አንድ ከ20 ሺሕ 800 ብር ወደ 36 ሺሕ ብር፣ የደረጃ ኹለት 41 ሺሕ 500 ብር እና የደረጃ ሦስት ሥራ አስኪያጆች መነሻ ደሞዝ ወደ 47 ሺሕ 500 ብር ማሳደጉን አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች።
ከዚህ በፊት የባንኩ የጀማሪ ተቀጣሪ ሠራተኞች የወር ደሞዝ መነሻ ለመጀመሪያ ሦስት ወራት አራት ሺሕ 800 ሆኖ፣ ከሦስት ወር በኋላ 6 ሺሕ 300 የነበረው፣ አሁን ላይ የባንኩ ጀማሪ ሠራተኞች የወር ደምወዝ ለመጀመሪያ ሦስት ወራት ስምንት ሺሕ 300 ሆኖ፣ ከሦስት ወር በኋላ 11 ሺሕ 500 በማድረግ ከፍተኛውን የባንክ ሠራተኞች ደሞዝ ጭማሪ አድርጓል።
ሌሎች ከጀረጃ ውጭ የተቀጠሩ የባንኩ ሠራተኞች የወር ደሞዝ መነሻ፣ ባንኩ ባደረገው አዲስ የደሞዝ ጭማሪ፣ ከነበረበት ሦስት ሺሕ 800 ብር ወደ ስድስት ሺሕ 900 ብር ማደጉን የአዲስ ማለዳ ምንጮች ተናግረዋል።
የተደረገው የደሞዝ ማሻሻያ በባንኩ ሠራተኞች አቅም ላይ መነቃቃት መፍጠሩንም ሠራተኞቹ ተናግረዋል። ባንኩ ከአራት ዓመት በፊት ባደረገው የደሞዝ ጭማሪ፣ ከኢንዱስትሪው ከፍተኛ ሆኖ የነበረ ሲሆን፣ ቀስ በቀስ የተነጠቀውን ከፍተኛ ከፋይነት መልሶ ይዟል።
ባንኩ ባለፉት ጥቂት ወራት አሳሳቢ የሆነው የገንዘብ እጥረት እስከ አሁን እንዳልገጠመው የባንኩ ሠራተኞች ለአዲስ ማለዳ ጠቅሰዋል።
‹‹ደንበኞች እስከ አሁን የሚፈልጉትን ያህል ገንዘብ ወጪ ያደርጋሉ። እኔ ባለሁበት ቅርንጫፍ በቀን እስከ 42 ሚሊዮን ብር ይንቀሳቀሳል። ሌሎች ባንኮች በቀን 20 ሺሕ ብር በለይ አናወጣም ቢሉም፣ እኛ ጋር ግን አንድ ሰው አምስት ሚሊዮን ድረስ ከኛእ ቅርንጫፍ ሲያወጣ ተመልክቻለሁ›› ሲሉም ያስረዳሉ።
የባንክ እና ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮችን በመተንተን የሚታወቁት አብዱልመናን መሐመድ፣ በከተሞች እየጨመረ የመጣው የኑሮ ውድነትን ሠራተኞቹ መቋቋም እንዲችሉ አቢሲኒያ ባንክ የደሞዝ ጭማሪ ማድረጉ ተገቢ ነው ብለዋል። አያይዘውም ሌሎች ባንኮችም ሠራተኞቻቸውን ለማቆየት ተመሳሳይ የደሞዝ ጭማሪ እንዲያደርጉ ሊያስገድድ እንደሚችል ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ የሚገኙ የግል ባንኮች እስከተጠናቀቀው የፈረንጆቹ ዓመት መጨረሻ ድረስ ብቻ ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ ለሠራተኞች ደሞዝ እና ጥቅማ ጥቅም አውጥተዋል የሚሉት አብዱልመናን፣ ድርጊቱ የሠራተኞችን የሥራ ተነሳሽነት የሚጨምር ቢሆንም የባንኮቹን የትርፍ መጠን እና የባለ አክሲዮኖችን የክፍፍል ድርሻ ሊጎዳው ይችላል ብለዋል።
አክለውም ባንኮች ጉልህ የደሞዝ ጭማሪ ማድረጋቸው የዋጋ ግሽበት ሊፈጥር ይችላል ያሉ ሲሆን፣ የዋጋ ግሽበቱ በአዲስ አባባ ከተማ ላይ ጎልቶ ሊታይ እንደሚችል አሳስበዋል። ለዚህም በባንክ ኢንዱስትው ተቀጥረው ከሚሠሩ ከ100 ሺሕ በላይ ሰዎች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው በመዲናዋ መገኘቱን በምክንያትነት አንስተዋል።
በኢትዮጵያ በግል እና በመንግሥት ባንኮች እጅ የነበረው የጥሬ ገንዘብ መጠን በባለፈው በጀት ዓመት በ21 ነጥብ 3 በመቶ የቀነሰ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት (2011) ሰኔ ወር መጨረሻ 143 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ደርሶ እንደነበር የብሔራዊ ባንክ መረጃ ያመለክታል።
መጠኑ በ2012 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመትም መቀነሱን የቀጠለ ሲሆን፣ መጠኑ ከባለፈው በጀት ዓመት የመጨረሻ ሦስት ወራት ውስጥ ከተመዘገበው ጋር ሲነፃፀር በ72 ነጥብ 7 በመቶ መውረዱን ብሔራዊ ባንክ ከወር በፊት ይፋ ያደረገው ሪፖርት ያመላክታል።
በሌላ በኩል፤ ባንኮች ከፍተኛ የቁጠባ መቀነስ እያጋጠማቸው በ2012 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ወደ ባንኮች የገባው የቁጠባ መጠን፣ ካለፈው በጀት ዓመት የመጨረሻው ሩብ ዓመት ጋር ሲነፀፀር በ45 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር (በ72 በመቶ) ወርዷል።
ባለፉት ኹለት ወራት ውስጥ በባንኮች የገንዘብ እጥረት አጋጥሟል። ለአብነትም ከወር በፊት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባጋጠመው የገንዘብ እጥረት ምክንያት ለጊዜው ለሠራተኞቹ ብድር ማቆሙን ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ይህም በብዙዎቹ የግል ባንኮች በተመሳሳይ ምክንያት ተግባራዊ ተደርጓል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቅርቡ የሠራተኞች ደሞዝ ጭማሪ ማድረጉ የሚታወስ ነው።
አብሲኒያ ባንክ በአዲስ አበባ 158 ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ ውጭ በክልሎች 195 ቅርንጫፎች፤ በጥቅሉ 353 ቅርንጫፎች አሉት። ባንኩ አሁን ላይ የሚያስተዳድራቸው ከስድስት ሺሕ በላይ ሠራተኞች አሉት። የባንኩ ተጠቃሚ ደንበኞችም ከአንድ ሚሊዮን በላይ ደርሷል።
ብሔራዊ ባንክ ባወጣው ሪፖርት መሰረትም፣ አቢሲኒያ ባንክ በኢትዮጵያ ካሉት የግል ባንኮች ከአዋሽ እና ከዳሽን ቀጥሎ በሀብት መጠኑ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ቅጽ 2 ቁጥር 71 መጋቢት 5 2012



