በኢትዮጵያ የኖቭል ኮሮና ቫይረስ ያለበት የመጀመሪያው የኮቪድ 19 ተጠቂ መገኘቱን የጤና ሚኒስቴር መጋቢት 4/2012 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታወቀ።
ግለሰቡ ቫይረሱ እንዳለበት ተረጋግጦ በለይቶ ማቆያ ሆኖ የሕክምና ክትትል እየተደረገለት ሲሆን፣ የ48 ዓመቱ ጎልማሳ የጃፓን ዜግነት ያለው ሲሆን የካቲት 25/2012 ከቡርኪና ፋሶ ወደ ኢትዮጵያ አንደመጣ ታውቋል። በቫይረሱ ከተጠቃው ግለሰብ ጋር የቅርብ ንክኪ የነበራቸው 25 ሰዎች በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቱ ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ ተናግረዋል።
በተለይም ስጋት የገባቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፣ ቫይረሱ በኢትዮጵያ መከሰቱ በመግለጫው ከተገለፀ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ የአፍ ማፈኛ፣ የእጅ ማፅጃ (ሳኒታይዘር) እና ጓንት ፍለጋ መድኃኒት ቤቶችን እና ሱፐር ማርኬቶች ውስጥ ተሰልፈው አምሽተዋል። ከዚህ በፊት አራት ብር ይሸጥ የነበረው በአገር ውስጥ የሚመረት የአፍ መሸፈኛ፣ አዲስ ማለዳ ለህትመት እስከገገባችበት ሰዓት ድረስ 50 ብር የተሸጠ ሲሆን፣ ጓንትና የእጅ ማፅጃ በገበያ ላይ አይገኙም።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ኮቪድ19ን ለመለየት ከአየር መንገድ የሙቀት መለካት ሥራ በተጨማሪ በ30 የየብስ መተላለፊያ መንገዶች ላይ ተጨማሪ ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል። የአፍ መሸፈኛ እና ጓንት የኮቪድ19 ምልክት ለታየበት ሰው እና ለጤና ባለሙያዎች እንጂ ለሁሉም ሰው እንደማያስፈልግም ተናግረዋል።
ሚኒስትሯ መንግሥት ለቫይረሱ 300 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት መበጀቱን ገልፀው፣ አሁንም ከተለያዩ የዓለማቀፍ ተቋማት ድጋፍ እየተፈለገ ነው ብለዋል። በመግለጫው ባስተላለፉት መልእክት ትኩሳት፣ ሳል እና የመተንፈሻ አካላት ሕመም ያጋጠማቸው ሰዎች ወደ ሥራ ቦታም ሆነ ትምህርት ቤት ባይሄዱ ጥሩ ነው ብለዋል።
የቫይረሱ መመርመሪያ መሣሪያ እስከ አሁን ገብያ ላይ እንዳልዋለ የተናገሩት ኤባ በበኩላቸው፣ ከተለያዩ አገራት በድጋፍ ያስገባናቸውን ውስን መሣሪያዎች በአግባቡ ለመጠቀም ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ኮሮና ቫይረስ በ134 የዓለም አገራት ተሰራጭቶ የአምስት ሺሕ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ ሲሆን፣ በበሽታው 139 ሺሕ 285 ሰዎች ተጠቅተዋል፣ 70 ሺሕ 729 ያክሉ ደግሞ ከቫይረሱ አገግመዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 71 መጋቢት 5 2012



