የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ከዘርፉ በስምንት ወራት ብቻ 129 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ።
ገቢው የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች፣ ክር እና ባህላዊ አልባሳትን ወደ ውጪ አገራት በመላክ የተገኘ ሲሆን፣ ለገቢው መጨመር በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ አዳዲስ አምራቾች ምርት መጀመራቸው በምክያትነት ተጠቅሷል። የጀርመን፣ ጣሊያን፣ አሜሪካ፣ አዉሮፓ፣ ቻይና እና የአፍሪካ ገበያ የምርቶቹ ዋና ዋና መዳረሻዎች እንደነበሩም ተጠቅሷል።
በበጀት ዓመቱ ስምንት ወራት በዘርፉ ከተሰማሩ የውጪ እና የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በአጠቃላይ 160 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማስገኘት ታቅዶ የነበረ ሲሆን፣ አሁን የተገኘው የ129 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እስከ አሁን በስምንት ወራት ተገኝቶ እንደማያውቅ የጨርቃ ጨርቅ እና ስፌት ልማት ኢንስቲትዩት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ባንቲሁን ገሰሰ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ለማግኘት ከታሰበው 160 ሚሊዮን ዶላር የውጪ ምንዛሬ ውስጥም 80 በመቶ የሚሆነውን ማሳካት እንደተቻለ ኃላፊው ገልጸዋል። ይህ ገቢም ባለፉት በርካታ ዓመታት በአንድ ዓመት ውስጥ ሲመዘገብ ከነበረው ገቢ እንደሚበልጥ ገልጸዋል።
ከጨርቃ ጨርቅና ስፌት ኢንዱስትሪ ምርቶች ኤክስፖርት በ2009 በጀት ዓመት 271 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማድረግ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ የተገኘው 89 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር ነበር። በወቅቱ ማሳካት የተቻለው፣ የእቅዱን 33 በመቶ ብቻ ነው። በ2012 በጀት ዓመት ከዘርፉ በአጠቃላይ ከ254 ሚሊዮን ዶላር ለማሳካት ታቅዷል።
በአጠቃላይ በስድስት ወራት ውስጥ ከዘርፉ ከተገኘው የውጪ ምንዛሬ ገቢ ውስጥ 93 በመቶው በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ካሉ አምራቾች የተገኘ ሲሆን፣ ቀሪው ሰባት በመቶ ደግሞ በአገር ውስጥ ባለሀብቶች የተገኘ ነው።
የፋብሪካዎች የአስተዳደር ስርዓት አቅም ውስንነት፣ በኢንቨስትመንት ሒደት ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች በወቅቱና በሚጠበቀው አቅም ወደ ማምረት አለመሸጋገር፣ ወደ ማምረት የገቡ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችም ወደ ሙሉ የማምረት አቅም መድረስ አለመቻላቸው ዘርፉ የሚጠበቀውን ያህል ዕድገት እንዳያስመዘግብ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱ ተገልጿል።
ለገቢው ማደግ አዳዲስ አልሚዎች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከመግባታቸው በተጨማሪ በፋብሪካዎች ውስጥ ለሚገኙ ባለሙያዎች ተከታታይ ሥልጠናዎች መሰጠታቸው እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን፣ በዘርፉ ከ60 በላይ ሙያተኞችን በውጭ አገራት በኹለተኛ ዲግሪ እና ከዚያ በላይ ባሉ የትምህርት ደረጃዎች ሠልጥነው ወደ ሥራ መሰማራታቸው ተገልጿል።
በፋብሪካዎች ውስጥ ተቀጥረው በሚሠሩ ሠራተኞች የሚከፈላቸው ደሞዝ አናሳ መሆኑን በመጥቀስ፣ በርካታ ጥያቄዎችን እንደሚያነሱ የገለፁት ባንቲሁን፣ ፋብሪካዎች ሠራተኞች በካበቱት ልምድ ልክ ደሞዝ ይከፈላቸዋል። የሚከፈላቸው ደሞዝ በቂ ነው ለማለት ባያስችልም፣ የኢንስቲትዩቱ ሠራተኞች የተሻለ ደሞዝ እንዲያገኙ ከባለሀብቶች ጋር ውይይት በማድርግ ላይ ይገኛል ብለዋል።
አክለውም ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ኢንስቲትዩቱ ለሠራተኞች እና ለባለሙያዎች ሥልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል ያሉ ሲሆን፣ አዳዲስ አልሚዎችንም ለመሳብ ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር በጋራ እየሠራን እንገኛለን ብለዋል።
በኢትዮጵያ ከ 200 በላይ የሚሆኑ በጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ምርቶች ላይ የተሰማሩ የአገር ውስጥ እና የውጪ አገራት ፋብሪካዎች ሲኖሩ፣ በውስጣቸው ከ100 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ፈጥረዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 72 መጋቢት 12 2012



