ኢትዮጵያ ከስጋ የውጭ ንግድ የምታገኘው ገቢ አሽቆለቆለ

0
1037

በዓመት ቄራዎች 10.8 ሚሊዮን ፍየሎች የሚፈልጉ ሲሆን የሚቀርብላቸው ግን 3.2 ሚሊዮን ብቻ ነው፡፡

የስጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የስጋ እንስሳት አቅርቦት እጥረት እና ጥራት በማጋጠሙ ኢትዮጵያ ከዘርፉ የምታገኘዉ ገቢ ማሽቆልቆሉን አስታወቀ።
በስጋ ምርት ላይ በአምራችነትና በላኪነት የተሰማሩ 14 ኢንዱስትሪዎች ወደ ውጪ ከሚልኩት ምርታቸዉ ውስጥ 90 በመቶ የሚሆነው የፍየል ስጋ ነዉ።የአገሪቱ የስጋ አምራችና ላኪ ድርጅቶች በጥቅሉ በአንድ ዓመት 10.8 ሚሊዮን ፍየሎች የሚያስፈልጉ ሲሆን አምራቾቹ አሁን ላይ ጥራት ያለውና በዓለም አቅፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ምርት ሊሰጡ የሚችሉ ፍየሎችን ማግኘት አልቻሉም።

በዓመት ለ14ቱም ቄራዎች የሚቀርቡ የጥራት ደረጃውን የሚያሟሉ ፍየሎች ብዛት 3.2 ሚሊዮን ሲሆን ከአምራቾች ፍላጎት ጋር ሲነፃፀር የ7.6 ሚሊዮን ያክል እጥረት እንዳለ የኢትዮጵያ ስጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ደበሌ ለማ ተናግረዋል።በኢትዮጵያ ስጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ሪፖርት መሠረት የ14ቱ ኢንዱስትሪዎች የ7 ወር የውጪ ንግድ አፈፃፀም 67.88 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን በበጀት ዓመቱ ግማሽ ዓመት ማሳካት የቻሉት 43.7 ሚሊዮን ዶላር ነው። አፈጻጸሙ በመቶኛ ሲሰላ ኢንስቲትዩቱ የዕቅዱን 64.37 በመቶ ብቻ ነው ማሳካት የቻለዉ። ከባለፈዉ ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ2011 በጀት ዓመት 56.10 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን ልዩነቱም የ12.4 ሚሊዮን ዶላር ሆኗል።በዚህም የ2012 በጀት ዓመት ግማሽ ዓመት አፈጻጸም ከባለፈዉ ግማሽ ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ22.13 በመቶ ማሽቆልቆል አሳይቷል።ደበሌ ለዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶት ካልተሰራ ችግሩ ለዓመታት እንደሚቀጥልና አገሪቱ ከዘርፉ ልታገኝ የምትችለውን የውጪ ንግድ ገቢ እየጎዳ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው እንደገለጹት ኢንስቲትዩቱ በ2012 በጀት ዓመት አጋማሽ ከባለፈዉ ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ20 በመቶ ማሽቆልቆል ዋና ምክንያቱ ዓለም አቀፍ ጥራቱን የጠበቀ የስጋ ከብት አቅርቦት እጥረት መኖሩ ነዉ።

እንደ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዉ ገለጻ ጥራቱን የጠበቀ የስጋ ከብት ዕጥረት የችግሩ ዋነኛ መንስዔ ቢሆንም ለእንሰሳት ስጋ ምርት የተሻለ ውጤት እንዲመጣ የፍየል፣ የበግ እና የቀንድ ከብት ዝርያ አለመሻሻል ተጨማሪ ችግር መሆኑን አስረድተዋል።ችግሩን ለመፍታት ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የእርድ እንስሳት ዋነኛ ምነጭ በሆኑት አካባቢዎች ወጣቶችን በማደራጅት ወደ ተግባር አንዲገቡ ጥረት እየተደረገ ነዉ ያሉት ደበሌ፣ በዋናነት ችግሩን ለመፍታት ግብርና ሚኒስቴር የስጋ እንሰሳትን ዝርያ ማሻሻል ላይ በትኩረት መስራት እንዳለበትም እና ለዘርፉ ትኩረት መስጠት እንዳለበት አመላክተዋል።

የእንሰሳት ሀብት ባለሙያ የሆኑት ታሪኩ ተካ አገሪቱ በእንሰሳት ሀብት ቀዳሚ ሀብት ቢኖራትም በአጠቃቀም ችግር ማግኘት ያለባትን ያክል ጥቅም እያገኘች እንዳልሆነ ያስረዳሉ።

ግብርና ሚኒስቴር አርሶ አደሩ በእንስሳት ልማቱ ላይ ገበያ ተኮር እንዲሆን መስራት፣ በግብዓት አቅርቦት መደገፍ እንዲሁም ሙያዊ አስራርን ማስተማር አለበት ይላሉ። ታሪኩ እንደሚሉት ዘርፉን ለማሳደግ የእንስሳት ዝርያን የስጋ እና የወተት ብሎ በየዘርፉ ማሻሻል እንደሚስፈልግ ሙያዊ ጥቆማቸውን ሰጥተዋል።ኢትዮጵያ ስጋ ከምትልክባቸዉ የውጭ አገራት ውስጥ ዱባይና ሳዑዲ አረቢያ ቀዳሚዎቹ ናቸዉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 72 መጋቢት 12 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here