ኮቪድ19 እና በድል የተደመደሙ ትንቅንቆች

0
1361

ኮቪድ19 የተሰኘው ቫይረስ ዓለምን ማስጨነቁን አልተወም። መንግሥታት እንደ አገር፣ ሰዎችም እንደ ግለሰብ ያሰቡትና ያቀዱት ቀርቶ፣ ጥቁር እንግዳ ሆኖ በድንገት የተከሰተው ቫይረሱ፣ ሁሉንም ከእቅዳቸው አናጥፏቸዋል። የብዙዎችን ሕይወት ሲቀጥፍ፣ የአገራትን ኢኮኖሚ አስታሞ ማኅበራዊ ግንኙነቶችን አስታጉሏል። አሁንም አስጨናቂ የሞትና በቫይረሱ የመያዝ ዜናዎች እየተሰሙ ነው።

ሆኖም ዜናዎች የሞትና በቫይረሱ የመያዝ ብቻ አይደሉም። የማገገምና የድል ዜናዎችም አሉ። በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸውን ካጡ ሰዎች የሚበልጠው ያገገሙት ሰዎች ቁጥር ነው። ምንም እንኳ ለቫይረሱ መድኃኒት የተገኘለት ባይሆንም፣ በጥንቃቄና በእንክብካቤ ከራስ ላይ ማራቅ እንደሚቻል የሕክምና ባለሞያዎችም ደጋግመው ሲናገሩ የሚሰማው ጉዳይ ነው።

እነዚህ በድል የተጠናቀቁ ከኮሮና ቫይረስ ጋር የተደረጉ የሞት ሽረት ፍልሚያዎች፣ ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎች ያሳለፉት ልምዳቸው፣ መልእክትና ምክራቸው በቫይረሱ ተይዘው በማገገም ላይ ላሉ ተስፋ፣ ላልተያዙት ደግሞ ጠቃሚ የ‹ተጠንቀቁ› ደወል ነው። የአዲስ ማለዳው ኤርምያስ ሙሉጌታም እነዚህን ታሪኮችና ከተለያዩ መገናኛ ብዙኀን ያገኛቸውን መረጃዎች አሰናስሎ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

ከወራት በፊት የፈረንጆች አሮጌው ዓመት መገባደጃ እና አዲሱ ዓመት መባቻ ላይ፣ የሩቅ ምሥራቅ እስያ የፀሐይ መውጫ አገራትን ነበር በማጥቃት የጀመረው፤ ኮቪድ19 ኮሮና ቫይረስ። በወቅቱም የዓለም የጤና ድርጅት የጥር ወር ጅማሬ ላይ ከቻይናዋ ሁቤ ግዛት ዉሃን ከተማ ምንጩ የማይታወቅ ቫይረስ መቀስቀሱን እና በተጠቀሱት የጊዜ ገደብም 44 ሰዎች በጠና መታመማቸውን የሚገልጽ መረጃ እንደደረሰው አስታወቀ።

በዚሁ ቀናት ታዲያ አላስፈላጊ መዘናጋቶችን ወደ ጎን በማድረግ የቻይና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገቢውን ትኩረት ለአዲሱ እና ምንጩ ለማይታወቀው የቫይረስ ወረርሽ በመስጠት ወደ ሥራ ተንቀሳቀሱ። ይሁን እንጂ የቫይረሱ የመዛመት ሂደት እና ፍጥነት ከመጠን በላይ በማሻቀቡ፣ ቻይናን ብቻ ሳይሆን ወደ ሌሎች አጎራባች አገራትም ከመዝመት አልዳነም።

በዚህም ምክንያት ከቀናት ዕድሜ በኋላ ጥር እኩሌታ አካባቢ 44 የነበረው በቻይና የተመዘገበው በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ኹለት መቶዎችን ተሻግሮ ወደ ሦስተኛው መቶ እያሻቀበ ነበር። አልፎም በአጎራባች አገራት በንግድ ማእከልነት፣ በቱሪዝም እና በአምራች ዘርፍ ወደ ተሰማራችው ቅንጡዋ ታይላንድም ብቅ ብሎ በኹለት ሰዎች ላይ ተከሰተ። በተመሳሳይ ወደ ፀሐይ መውጫዋ አገር ጃፓን እና ኮሪያ ጎራ በማለትም በኹለቱ አገራት በአንድ አንድ ሰዎች ላይ እንደተከሰተ የዓለም ጤና ድርጅት ይፋ አድርጎ ነበር።

ገና ከጅማሬው 278 የተረጋገጡ የተጠቂዎች ቁጥርን ያስተናገደችው ቻይና፣ 258 የሚሆነው ከተነሳባት ሁቤ ከተማ ሲሆን 14 የሚሆኑት ደግሞ ከሁዎንግ ዶንግ ከተማ ናቸው። ቀሪዎቹ ከዋና ከተማዋ ቤጂንግ እና ከዓለም ዐቀፍ የንግድ ከተሞች መካከል በግንባር ቀደምትነት በምትጠቀሰው የሻንግሃይ ከተማ የተመዘገቡ ነበሩ። በእነዚሁ ጊዜያት 12 በአስጊ ደረጃ ላይ የሚገኙ ታማሚዎች ቁጥር ሲመዘገብ 6 ሰዎችም ይህን ዓለም ተሰናብተው እንደነበር የዓለም ጤና ድርጅት መግለጫ ያስታውቃል።

ለእንደዚህ ዓይነት ወረርሽኝ እና ብዙዎችን በማጥቃት ለሞት ለሚዳርጉ በሽታዎች አዲስ ያልሆነችው ቻይና፣ ቁርጠኛ ርብርብና አፋጣኝ እርምጃዎችን በመውሰድ ሊመጣ የነበረውን ጥፋት በእጅጉ ለመቀነስ እንቅልፍ የለሽ እንቅስቃሴ አደረገች። አንድ ሺሕ አልጋ የሚይዙ ሆስፒታሎችን በሳምንት ባነሱ ቀናት ገንብታ አጠናቀቀች።
ቀጠለች፤ በኹሉም ግዛቶቿ የቫይረሱ ተጠቂዎችን የማደን ሥራ በስፋት ተጀመረ። ከጥር ወር መባቻ ጀምሮ 35 ንክኪ የማያስፈልጋቸው የሙቀት መመርመሪያ መሣሪያዎች በአውሮፕላን እና በባቡር ጣቢያዎች በመትከል የተግባር ሰዎች መሆናቸውን አሳዩ። በሕመም ተይዘው የሚሰቃዩትን እና አገግመው እንደገና ያገረሸባቸውን ሰዎችንም የመለየት ሥራዎች ተሠሩ። የባህር ውስጥ ምግቦችን በመሸጥ የሚታወቁ ሥመ ጥር ስፍራዎችም እንዲዘጉ ጥብቅ ማሳሰቢያዎች ተላለፈባቸው።

በዚህና በስድስት አፋጣኝ እና አሳዛኝ ሞቶች የተጀመረው ኮቪድ19 ቫይረስ፣ ዓለምን የመውረር ጉዞ በአስደናቂ ፍጥነት ቀጠለ። ቅንጡ የዓለም አገራትን፣ የአውሮፓን ከተሞችም በማጥቃት በሰዎች ሀዘን ላይ ሀዘን ሲደርብ፣ የዓለም ዐቀፍ መገናኛ ብዙኀን የመርሃ ግብር መክፈቻ ሲያደርጉት ሰንብተን አሁን የደረስንበት ደረጃ ላይ ደርሰናል።

የወራት ዕድሜ ባለቤቱ ኮቪድ 19 በዓለም ዙሪያ በ198 አገራት እና ግዛቶች ውስጥ አዳርሶ 475 ሺሕ 175 የተረጋገጡ እና በበሽታው የተጠቁ ሰዎች ተመዝግበዋል። ከእነዚህም ውስጥ 136 ሺሕ 73 ሰዎች ጉዳይ እንደተዘጋ መጋቢት 15/2012 የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል። ጉዳያቸው ከተዘጋው ውስጥም 114 ሺሕ 767 ሰዎች ከበሽታው ያገገሙ ሲሆን፣ 21 ሺሕ 358 የሚሆኑት ደግሞ የቀጣዩን ቀን የማለዳ ጮራ ሳይመለከቱ አሸልበዋል ሲል ይፋ አድርጓል።

በጤና ድርጅቱ ሪፖርት መሰረት፣ ከቀዳሚዎቹ አገራት ውስጥ በዋናነት የወረርሽኙ መነሻ አገር የሆነችው አገር ቻይና በ81 ሺሕ 287 የበሽታው ተጠቂ ቁጥሮች ቀዳሚዋ ብትሆንም፣ ለሞት የበቁት የዜጎቿ ብዛት ግን በተከታይነት ከምትቀመጠው አውሮፓዊቷ አገር ጣልያን በግማሽ ያነሰ ነው። ወረርሽኙ ከተከሰተበት የመጀመሪያዎቹ ቀናት ጀምሮ ቻይና 3 ሺሕ 287 ዜጎቿን ያጣች ሲሆን፣ የአውሮፓ ገበሬ በምትባለው ጣልያን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 74 ሺሕ 386 ነው። የሟቾች ቁጥር ደግሞ 7 ሺሕ 503 ደርሷል።

በየዕለቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎቿን የምትነጠቀው ጣልያን፣ የወረርሽኙን አስከፊነት ማሳያ አገር ተደርጋ ትወሰዳለች። በዚሁ ዓለም ዐቀፋዊ ወረርሽኝ በብዛት ዜጎቿን በቫይረሱ የተጠቁባት አገር አሜሪካ ናት። በዚህም ረገድ 68 ሺሕ 489 ሰዎች በቫይረሱ የተጠቁ ሲሆን፣ የሞት መጠን ግን ከተያዘው ሰው ቁጥር አንጻር እጅግ አናሳ ነው በሚባል ደረጃ 1 ሺሕ 32 ሰዎችን ለህልፈት ዳርጓል።

በኢትዮጵያም ቫይረሱ ከተገኘበት ከወርሃ መጋቢት መጀመሪያ ጀምሮ 12 በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች መኖራቸው የታወቀ ሲሆን፣ እንደ ኢፌዴሪ የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሪፖርት መሰረት፣ ይህ ጽሑፍ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ምንም ዓይነት ሞት አለመመዝገቡ ታውቋል።

ዓለምን በቀን በሌሊት የሚያባትታት ይኸው ወረርሽኝ ቀላል ሊመስሉ በሚችሉ ነገሮች መከላከል የሚቻል እንደሆነ ዓለም ጤና ድርጅት በተደጋጋሚ በዋና ዳይሬክተሩ ኢትዮጵያዊው ዶክተር ቴዎድሮስ አድኃኖም አማካኝነት ሲያስተላልፍና ቆይቷል፤ እያስተላለፈም ይገኛል። ከዚሁ ጋር ተያይዞም ማኅበራዊ ፈቀቅታን መተግበር፣ እጅን በንጽሕና መጠበቅ እንዲሁም የንክኪ ሰላምታን ማስወገድ በዋናነት ወረርሽኙን ለመግታት ከሚደረጉ ጥንቃቄዎች ዋነኞቹ ናቸው።

ይሁን እንጂ ይህን ኹሉ አልፎ ሰዎች በኮቪድ 19 ከተጠቁ በእርግጠኝነት ይሞታሉ ማለት እንዳልሆነም በርካታ ዓለም ዐቀፍ የጤና ባለሙያዎች እና ከጤና ጋር ግንኙነት ያላቸው ጉምቱ ተቋማት ወደ መገናኛ ብዙኀን ብቅ እያሉ የግንዛቤ መፍጠር ሥራ ሲሠሩ ተስተውለዋል።

ኮሮና ኮቪድ 19 ምን ያህል ገዳይ ነው?
ቢቢሲ የአገረ እንግሊዝ መንግሥት የሳይንስ አማካሪዎችን ዋቢ በማድረግ ባስነበበው ጽሑፍ፣ አንድ በኮሮና ኮቪድ19 የተጠቃ ሰው የመሞት ዕድሉ ከ0ነጥብ 5 እስከ 1 በመቶ እንደሚደርስ አስታውቋል። ይህ ደግሞ በዓለም የጤና ድርጅት አማካኝነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተመዘገበው የ16 በመቶ የሞት መጠን እና በእንግሊዝ ብቻ በታየው የ5 በመቶ ሞት እጅግ ያነሰ መሆኑን ያሳያል።

እንደ ዘገባው ከሆነ የቫይረሱ ገዳይነት የሚጠናው በእድሜ ልዩነት እንደሆነም ያትታል። በዚህም ረገድ ከ80 ዓመት በላይ ባሉ ሰዎች ላይ የገዳይቱ መጠን እጅጉን እንደሚጠና ለማወቅ ተችሏል። በሌላ መንገድ ዕድሜያቸው የገፉ ሰዎች በበሽታው ላለመያዝ ከፍ ያለ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸው ያሳስባል ማለት ነው።
የለንደኑ ኢምፔሪያል ኮሌጅ በቻይና ውስጥ በ44 ሺሕ የቫይረሱ ተጠቂዎችን የሕክምና መዛግብት በማገላበጥ ባደረገው ምርመራ፤ የሟቾች ቁጥር ከአምስት እጥፍ በበለጠ የደም ግፊት፣ ስኳር፣ የመተንፈሻ አካላት እክል ያለባቸው እንዲሁም የልብ ችግር ያለባቸው ሰዎች ላይ እንደጠነከረ አስነብቧል።

ከላይ እንደተጠቀሰው በዓለም የጤና ድርጅት ሪፖርት መሰረት ይህ ጽሑፍ እስከ ተጠናቀረበት ድረስ ከወረርሽኙ ያገገሙት ሰዎች በወረርሽኙ ይፋ ከተደረገው የሰዎች ቁጥር የ84 በመቶ ድርሻውን የሚይዝ ሲሆን ይህም በቁጥር ሲቀመጥ 114 ሺሕ 767 እንደሆነ ተገልጿል። ይህ ሲሆን ግን በመጀመሪዎቹ ወራት ከታየው የተጠቂዎች ቁጥር እና 4 በመቶ ከነበረው የሟቾች ቁጥር በአራት እጥፍ በማደግ 16 በመቶ ላይ መቀመጡን ከጤና ድርጅቱ ሪፖርት ለመረዳት ይቻላል።

በአሜሪካ ፍሎሪዳ ግዛት የኦርላንዶ ከተማ የአስቸኳይ መድኃኒቶች ሐኪም ዶክተር ኢዮደን ሐሪ እንደሚሉት፣ ቫይረሱ በሰዎች ውስጥ ከ10 እስከ 14 ቀናት ይቆያል። ከበረታ እና ወደ ሳንባ በመሄድ ጉዳት በማድረስ የሳንባ ምች የሚያስከትል ከሆነ ግን ከዛም ላቅ ላሉ ቀናት ሊቆይና በዚህ ደረጃ ያሉ ሰዎችም በከፍተኛ የሕክምና ድጋፍ እና እርዳታ ሊቆዩ እንደሚችሉ አስታውቀዋል። በእነዚህ ቀናትም የሕክምና ባለሙያዎች የሲቲ ስካን ምርመራዎችን በመጠቀም የታካሚዎች ሳንባ የጤንነት ደረጃን ወደ መልካምም ሆነ ወደ መጥፎ ለውጥ ማሳየቱን መከታተል እንደሚኖርባቸው ኢዩደን ታስታውቃለች።

ከኮቪድ 19 እነማን አገገሙ?
ያንግ ያንግ
የኮቪድ 19 የመጀመሪያ መጠንሰሻ እና መገኛ ከሆነችው የቻይናዋ ውሃን ከተማ የተገኘችው የ28 ዓመቷ ያንግ ያንግ፣ በኮሮና ኮቪድ 19 ቫይረስ ተጠቅተው ካገገሙ ሰዎች አንደኛዋ ናት። ያንግ ከአልጀዚራ ጋር ባደረገችው ቆይታ በበሽታው ተይዛ በነበረችበት የሞት ሽረት ትግል ያጋጠማትን ትናገራለች።

ያንግ ያንግ ከወላጅ አባቷ ጋር ነበር በቫይረሱ የተጠቁት። ይሁን እንጂ በወቅቱ በነበረው ሕክምና ተቋማት የመቀበል አቅም ውስንነት የእርሷን እና የአባቷን ጉዳይ በሕክምና ባለሙያዎች በቂ ትኩረት አልተሰጠውም ነበር። ‹‹በመጀመሪያ ደረጃ የቫይረሱ ተጠቂ መሆናችንን የሚገልጽ የሐኪም ምርመራ አደረግን። ነገር ግን ተደጋጋሚ ምርመራዎችን አድርገን ተመሳሳይ ውጤቶች ካልተገኙ ወደ ሕክምና ተቋሙ ተወስደን ተኝተን የመታከም ዕድል እንደማናገኝ ተነገረን›› ብላለች ያንግ ትውስታዋን ስትገልጽ።

በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ያንግ ያለችበትን ሁኔታ በመግለጽ ረዳት የለኝም የሚል አንድምታ ያለው ጽሑፍ ትለጥፍና ይህም ከፍተኛ መነጋገሪያ በመሆኑ ከሆስፒታል የስልክ ጥሪ ደረሳት። ይህንንም ተከትሎ ቁጥር 7 በተሰኘ ሆስፒታል ገብታ ሕክምናዋን መከታተል እንደምትችል አስታወቋት፤ የሕክምና ጥረቱም ከዚህ ጀመረ።
ያንግ ሆስፒታል በገባችበት ወቅት በሆስፒታል ውስጥ የነበረው የመጨናነቅ ሁኔታ እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ከአምስት ሌሎች ተጨማሪ ታካሚዎች ጋር አንድ ክፍል ልትጋራ ግድ ሆነባት። ‹‹ከሰዎች ጋር የሕክምና ክፍል መጋራቴን አልጠላሁትም። ምክንያቱም አልጋ አግኝቼ ተኝቼ እስከታከምኩኝ ድረስ ጉዳዬ አልነበረም›› ትላለች።

የሞት ሽረት ትግልን ያሳለፈችው ያንግ አሁን አገግማለች። በማኅበራዊ ትስስር ገጾችም ከቀናት በኋላ ራሷ አብስላ የተመገበችውን እንቁላል በተመለከተ ‹‹እንቁላል ይህን አይነት ግሩም ጣዕም እንዳለው ዛሬ ገና አወቅሁኝ›› ስትል ማገገሟን እና ወደተለመደው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዋ መመለሷን የሚነግር መልዕክት አጋርታለች።
ያንግ አሁንም በሕክምና ዕርዳታ ስር ሆነው ለመኖር ጥረት እያደረጉ ላሉ ወዳጆቿ እና ጓደኞቿ በቅርቡ ድነው ለመገናኘት እንደምትመኝ እና ጉጉቷም ትልቅ እንደሆነ አስታውቃለች።

ያንግ በሁቤ ግዛት ውሃን ከተማ ውስጥ ታክመው ከዳኑ የወረርሽኙ ተጠቂዎች አንዷ ናት። በዚሁ ከተማ ከፍ ሲልም በቻይና አገር በወረርሽኙ የተጠቂዎች ቁጥር ጨምሮ ወደ 75 ሺሕ ገደማ ቢደርስም፣ ከሕመሙ የመዳን አዝማሚያ በተቃራኒው እየጨመረ መምጣቱን ቴዎድሮስ አድኀኖም አስታውቀዋል። ቴዎድሮስ አያይዘውም በቻይና በበሽታው ከሚያዙ አምስት ሰዎች መካከል አራቱ መጠነኛ የሆነ የበሽታው ምልክት እንደሚታይባቸው እና የመዳን ዕድላቸውም በዛው ልክ ከፍተኛ እየሆነ መምጣቱን ይፋ አድርገዋል።

ፔንግ
በቤተሰብ ሥሟ መጠራትን የመረጠችው የ34 ዓመት ቻይናዊት ስላሳለፈችው ሁኔታ እንዲህ ታጫውታለች። በጥር 8/2012 ነበር የመጀመሪያ ምልክቶች ማሳየት የጀመረችው። ይሁን እንጂ ከሳምንት በኋላ ነው ለመተንፈስ አስቸጋሪ እየሆነባት በሄደ ጊዜ ወደ ሕክምና ተቋም የገባችው። በሕይወት ቆይታ ቀጣይ ኑሮዋን ለመግፋት የእንደገና እድል እንደሚኖራት ጭራሽ ምንም ተስፋ እንዳልነበራትና በተለይም ደግሞ ከነበረችበት የመተንፈስ ችግር እና ሌሎች ተዛማጅ የቫይረሱ ምልክቶች አንጻር፣ ከፍተኛ የሆነ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንደነበረች ተናግራለች።

ወደ ሕክምና ተቋም ሄዳ በተደረገላት የጽኑ ሕሙማን እንክብካቤ፣ ጤንነቷ ከአስጊ ሁኔታ ተመልሶ ወደ መጠነኛ መሻሻል እንደገባ እና መሽቶ በነጋ ቁጥርም አስጊ የነበረው የጤንነቷ ጉዳይ በጎ ለውጥ ማሳየቱን ቀጠለ። ከኹለት ሳምንታት የሆስፒታል ቆይታ በኋላ በኹለት የምርመራ ውጤቶች ቫይረሱ ከውስጧ መውጣቱን ማረጋገጫ በማግኘቷ ከሆስፒታል እንድትወጣ ሆነ።

ይሁን እንጂ ፔንግ ከሆስፒታል ቫይረሱ በውስጧ እንደሌለ ብትገነዘብም፣ ከሆስፒታል ከወጣች በኋላ ለ14 ቀናት ራሷን ለይታ ለማቆየት እንደተገደደችም ጨምራ ገልጻለች። ከአልጀዚራ ጋር የስልክ ቆይታ ያደረገችው ፔንግ፣ በሆስፒታል ቆይታዋ ያየችው የነበረው ሁኔታ እና ከሕክምና መሣሪያዎች ይወጣው የነበረው ድምጽ በሙሉ ዛሬም በእዝነ ሕሊናዋ ደጋግማ ትሰማዋለች። በተለይም ደግሞ ሕመምተኞችን ለመርዳት በሕክምና ባለሙያዎች ዘንድ ይደረግ የነበረው ርብርብ አሁንም ደረስ እንደማይረሳት ትናገራለች።

‹‹ይሄ ዓለም ዐቀፍ ወረርሽኝ መቋጫ ባገኘበት ሰዓት ወደ ነበርኩበት ሆስፒታል ተመልሼ በሞትና በሕይወት መካከል በነበርኩበት ወቅት ያላሰለሰ ርብርብ አድርገው ነፍሴን ለታደጓት የሕክምና ባለሙያዎች ምስጋናዬን የማቀርብ ነው የሚሆነው” ስትል ምስጋና እና አድናቆቷን ትገልጻለች።

አብዛኞቹ ከወረርሽኙ ያገገሙ ሰዎች እምብዛም የከፋ ምልክት ያልታየባቸው ግለሰቦች ሲሆኑ፣ ወደ ሆስፒታል ገብተው የመታከም ዕድል ያላገኙት ሰዎችም በተመላላሽ እየታዩ ተገቢውን ሕክምና እንደሚያገኙ አልጀዚራ አስታውቋል።

ቤቱ ሆኖ ራሱን በማስታመም የቆየው የቻይናዋ ውሃን ከተማ ነዋሪ ው ጃንካንግ በየቀኑ ወደ ዉሃን ሃንኩ ሆስፒታል በመሔድ መርፌ እንደሚወጋ ይናገራል። ራሱን በራሱ አግልሎ በቆየበት ጊዜም የሰውነት የሙቀት መጠኑ ከፍ እና ዝቅ እንደሚል ይናገራል። ‹‹የመጀመሪው ቀን 38.5 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ሆነ። በቀጣይ ቀን ደግሞ ወርዶ 37.2 ሆነ። ሦስተኛው ቀን በጣም ከፍ ብሎ 39.1 በመሆን አእምሮዬን ተቆጣጥሮ ሌላ ነገር ማሰብ እንዳልችል አደረገኝ›› ሲል ያስታውሳል።

ካርሎ ናቫሮ
‹‹በኮሮና መያዝ ወይም መጠቃት ማለት የሞት ፍርድ ተፈረደብን ወይም እንሞታለን ማለት አይደለም።›› ሲል ይጀምራል፣ የ48 ዓመቱ ባለትዳርና አንዲት ሴት ልጅ አባት የሆነው ፊሊፒናዊው ካርሎ ናቫሮ። ለፊሊፒንስ እንደ አገር የካርሎ ናቫሮ ጉዳይ የመጀመሪያው የኮሮና ግኝት እንደሆነ ታውቋል።

በመጋቢት የመጀመሪያዎቹ ቀናት ቤተሰቦቹ ጋር ለጉብኝት ወደ ጃፓን አቅንቶ በነበረበት ወቅት በቫይረሱ እንደተጠቃ ታውቋል። በቫይረሱ መጠቃቱ በታወቀበት ወቅትም በአፋጣኝ ወደ ሆስፒታል የተላከ ሲሆን፣ ከቤተሰቦቹ ጋር መገናኘት እንዳልቻለ ይናገራል። ‹‹ማንም ሰው እንዲጎበኘኝ አይቻልም ነበር። የቤተሰብ አባላትን ጨምሮ ማንም አጠገቤ እንዲደርስ አይቻልም ነበር። ነገር ግን በየአንድ ሰዓቱ ልዩነት ከባለቤቴ ጋር የቪዲዮ የስልክ ግንኙነቶችን እናደርግ ነበር። በተለይ ደግሞ ፍርሃት ሲሰማኝ ካለሁበት ሆኜ ወደ ልጄ እና ባለቤቴ በመደወል ያለሁበትን ሁኔታ ለመርሳት እሞክር ነበር›› ሲል ይናገራል፤ ካርሎ።

ያም ሆኖ ግን ወደ ሆስፒታል ከገባ ከአራተኛው ቀን በኋላ መፍራት እንደጀመረ እና ለዚህም ደግሞ ምክንያቱ በተመሳሳይ ቀን ወደ ሆስፒታል የገቡ ሰዎች መሞት መጀመራቸው እንደሆነ ይናገራል። ‹‹በሆስፒታል በየማለዳው የሚሰማው የለቅሶ እና የሰቆቃ ድምጽ እጅግ አስፈሪ ነበር። በተለይ ደግሞ ከእኔ ጋር እኩል ቀን ወደ ሆስፒታል የገቡ ሰዎች መሞት ሲጀምሩ በጣም ያስፈራ ነበር›› ይላል ካርሎ ሁኔታውን ሲያስታውስ።

ፊሊፒንስ በአሁኑ ሰዓት 636 የተረጋገጡ በቫይረሱ የተጠቁ ዜጎች የሚገኙ ሲሆን፣ 26 የሚሆኑት ከቫይረሱ አገግመው ወደ ነበሩበት ሕይወት ተመልሰዋል። 38 የሚሆኑት ግን ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ከ15 ቀናት የሆስፒታል ቆይታ በኋላ ወደ ቤተሰቦቹ የተቀላቀለው ኮሮናን ታግሎ ያሸነፈው ፊሊፒናዊው ካርሎ፣ ‹‹ዋናው ነገር እምነት እንዲኖረን ያስፈልጋል። በተለይ ደግሞ ሥነ ልቦናዊ እና ስሜታዊ ዝግጅት በጣም ጠቃሚ ነው።›› ሲል ምክሩን ያስተላልፋል።

ዳዊት (ዲጄ ዳሊዮን)
በስዊድን ስቶክሆልም ከተማ የሚኖረው ዳዊት በኮሮና የተጠቃ እና እያገገመ የሚገኝ በትውልድ ኢትዮጵያዊ ወጣት ነው። ዳዊት በስቶክሆልም ከተማ በምሽት ክበቦች ውስጥ በዲጄነት (በሙዚቃ አጫዋችነት) የሚሠራ ሲሆን፣ ከስቶክሆልም ከተማ ወጣ ብላ ከምትገኝ ከተማ ወደ ስቶክሆልም ለመምጣት ባቡር መጠቀሙን እና በዛን ወቅትም ቫይረሱ ይዞኛል ብሎ እንደሚያምን ከሰይፉ በኢቢኤስ ጋር ባደረገው ቆይታ ይናገራል።

እንደ ዳዊት ገለጻ፤ የሕመም ምልክቱ ሲጀምረው ቀለል ያለ ጉንፋን ዓይነት ስሜት እንደነበረው እና እያደር ግን ከባድ ራስ ምታት እንዲሁም ከፍተኛ የሆነ ሙቀት መከሰት እንደጀመረው ይናገራል። ‹‹ከባድ ራስ ምታት አለው። መተኛት ጭራሽ የማይታሰብ ነው። ምክንያቱም ከፍተኛ የሆነው የራስ ምታት ሊያስተኛኝ አልቻለም። በተለይ የውሃ ጥም ደግሞ ትልቁ ጉዳይ ነው። በቀን ከ10 እስከ 12 ሊትር ውሃ እጠጣ ነበር›› ሲል ይናገራል ዳዊት። የምግብ ፍላጎቱ በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆሉን የሚናገረው ዳዊት፣ ለመተንፈስ ከፍተኛ እክል ይገጥመው እንደነበርም ተናግሯል።

ወደተለያዩ ማኅበራዊ ትስስር ገጾች በተለይም ደግሞ በፌስቡክ ያለበትን ሁኔታ እና ከተለያዩ ግለሰቦች ለሚሰነዘርለት ጥያቄዎችም ምላሽ ሲሰጥ ተስተውሏል። በተለይም ደግሞ ‹‹ጀርባዬ ላይ ወይም ደረቴ ላይ ወፍራም ሰው ወይም ከባድ ነገር የተቀመጠብኝ ይመስለኛል። ለመተንፈስ ከባድ ነው›› የሚለው ዳዊት፣ ነገር ግን ኹሉም መደናገጥ እንደሌለበት እና ላለመያዝ ቢጠነቀቁ መልካም ነው ብሏል።

ነገር ግን ከተያዙም ቀለል አድርገው ተገቢውን እንክብካቤ ለራሳቸው በመስጠትና ወደ ሌሎች ሰዎች በሽታውን እንዳያዛምቱ በመጠንቀቅ ራሳቸውን ለይተው እንዲያቆዩ ይመክራል። ተደራቢ እና ነባር በሽታ ያለባቸው ሰዎች ላይ እስከ ሞት ሊያደርስ የሚችል ጉዳት ሊኖረው እንደሚችል የሚናገረው ዳዊት፣ ‹‹አስም፣ ኤች.አይ.ቪ. እና ሌሎች ከባባድ በሽታ ያለባቸው ሰዎች ሊጠነቀቁ ይገባል። ነገር ግን በሙሉ ጤንነት ላይ የሚገኙ ሰዎች በኮሮና ቢጠቁ ትንሽ ከበድ ካለ የጉንፋን ስሜት የዘለለ ምንም ነገር እንደማያጋጥማቸው እነግራችኋለሁ›› ይላል ዳዊት።

ኢትዮጵያዊት ሴት ከአሜሪካ ኮሎራዶ
በአሜሪካ ዴንቨር ግዛት ኮሎራዶ የምትኖረው እና የሕክምና ባለሙያ የሆነችው ኢትጵያዊት፣ ራሷን ባገለለችበት በግል መኖሪያ ቤቷ ሆና ስለ ወረርሽኙ በስፋት ትናገራለች። የሕክምና ሙያዋን በምታከናውንበት ሆስፒታል ውስጥ በአንድ ታካሚ ምክንያት ቫይረሱ እንደተጋባባት ገልጻለች። እርሷ በምትሠራበት የሕክምና ተቋም ውስጥ ቫይረሱ እንዳለበት የጠረጠረ ሰው እንደመጣ እና ምንም አይነት መከላከያ ሳያደርግ ደረቅ ሳል እያሳለ እንደቀረባትም ጠቅሳለች።

በወቅቱ ምንም አይነት የአፍና አፍንጫ መከላከያ ያላደረጉት የሕክምና ባለሙያዎች፣ ቫይረሱ በቀጥታ ከታካሚው እንደተጋባባቸው ነው የምትናገረው። ሕመሙ ሌሊት 9 ሰዓት ላይ ከእንቅልፏ ቀሰቀሳት፣ በከፍተኛ ላብ ተጠምቃ ግን ደግሞ በአንጻሩ ብርድ ብርድ እየተሰማት ነበር። ደረቅ ሳል እንዲሁም በደረቷ ላይ ከፍተኛ የሆነ ሕመም እንዳለው ስትናገር፣ ራሷን ከሌሎች ሰዎች አግልላ እያስታመመች ትገኛለች።

ያለችበትን ሁኔታ ለማስረዳት ይፋ ባደረገችው ተንቀሳቃሽ ምስል፣ በርካታ ምክር አዘል ሐሳቦችንም አስተላልፋለች። በተለይ ደግሞ ማኅበራዊ ፈቀቅታን ሰዎች በሚገባ እንዲተገብሩትና ንጽሕናም መጠበቅ ለነገ የሚባል ጉዳይ እንዳልሆነ ነው የምታስቀምጠው።

በንግግሯ መሐል በከባድ ደረቅ ሳል የምትደነቃቀፈው ባለታሪክ፤ አራተኛ ቀኗ ላይ እንዳለች እና ሰው ካየችም አራተኛ ቀኗ ላይ እንደሆች ተናግራለች። ከተጠቀሱት የበሽታው ምልክቶች ባለፈ ማቅለሽለሽ እና ወደ ላይ ማለት እንዲሁም ምግብ አልረጋ ማለት እንዳለውም ለመረዳት ተችሏል። ከሚያጋጥመው የደረት ሕመም ጋር ተያይዞ በምትተኛበት ወቅት ኹለትና ሦስተ ትራሶችን መደራረብ ግዴታ እንደሆነባት እና ካልሆነ ግን ለትንፋሽ ማጠር እንደምትዳረግ ታስረዳለች።

በእድሜ ጠና ያሉ ሰዎች ሊቋቋሙት የማይችሉት ከባድ በሽታ እንደሆነ እና ሰዎች ቤታቸው ቁጭ በማለት ይህን ጊዜ በማሳለፍ እና እድሜያቸው የገፋ ሰዎችን ባለመበከል ትልቅ ሥራ መሠራት እንዳለበት ታሳስባለች። በተለይም ደግሞ በኢትዮጵያ ያለውን የአኗኗር ዘይቤ በመመርኮዝ፣ ወረርሽኙን ለመከላከል ትልቅ ሥራና ጥንቃቄ እንደሚጠበቅ የምትገልጸው ባለታሪኳ፣ በአንድ ቤት ውስጥ በርከት ያለ ቁጥር ያለው ሰው ከመኖሩ ጋር ተያይዞ ስርጭቱን እንዳያባብሰው ስጋት አላት።
ተመሳሳይ በርካታ ታሪኮችን ተሰምተዋል። የካናዳ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን ሲቢሲ፣ በቫይረሱ ተይዘው የነበሩና ያገገሙ ጥቂት ሰዎችን አናግሯል። በአሜሪካዋ ሲያትል በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ውስጥ በኮሮና ቫይረስ መያዟን ተከትሎ ሕክምና ስታደርግ የቆየችው ኢያን፣ ከቫይረሱ ጋር የነበራት ቆይታ አሰቃቂ እንደነበር ታስታውሳለች። ‹‹ከዚህ ቀደም ጉንፋን ይዞኝ ያውቃል። ይህኛው ግን የተለየ ነው፣ በጣም ያማል።›› አለች።

ኢያን ትኩሳቱ እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው ስትል፣ ቀለል አድርገው ለሚያዩት ታሳስባለች። የመጀመሪያ ጊዜ ቫይረሱ እንዳለባት ሲረጋገጥ፣ ዶክተሮቹ ጋር የነበረውን መደናገጥ ከፊቷ እንዳልጠፋም ጠቅሳለች። ‹‹ገሃነም እንደመቆየት ነው›› ስትልም በሕክምና ያሳለፈችውን የኹለት ሳምንት ጊዜ ገልጻዋለች።

በተመሳሳይ ጆርጂያ የሚገኘው ጎልማሳው ክሌይ ቤንትሌ፣ መጀመሪያ ሕመሙን ተከትሎ ወደ ሆስፒታል ሲሄድ ቀለል ያለ ኢንፍሉዌንዛ እንደተያዘ ነበር የተነገረው። እርሱም የተባለውን አምኖ ወደ ቤቱ አቀና። በማግስቱ ግን ከአልጋው እንኳ መነሳት አልቻለም፤ መተንፈስም ከባድ ሥራ ሆነበት።

በቫይረሱ መያዙ የተረጋገጠው ከዚህ በኋላ ነው። እርሱም ብቻ ሳይሆን ባለቤቱና የተወሰኑ የቤተሰቡ አባላትም ቫይረሱን ተቀብለውት ነበር። በማገገም ላይ እንዳለ ለሲቢሲ የተናገረው ክሌይ፣ ቀድማ ከማገገሚያው የወጣችው ባለቤቱ ላይ ግን መገለል እየደረሰ እንደሆነ ሳይገልጽ አላለፈም።

ኤልዛቤት ሽናይደር፤ ሳይንቲስቶች ለኮሮና ቫይረስ ምርምር የሚፈልጉትን ደም የለገሰች ወጣት ናት። ይህ በጎ አድራጎት ሥራ የሠራችው ወጣቷ፣ አሁን ከኮሮና ቫይረስ አገግማለች። መጀመሪያ የተለየ ዓይነት ጉንፋን የያዛት የመሰላት ኤልሳቤት፣ ደኅና መሆኗ ከተነገራት በኋላ፣ ‹‹ነገሩ ሊነጋ ሲል ይጨልማል ዓይነት ነው። የከፋ ነገር ሊመጣብን ይችላል። ቢሆንም ግን የተሻለ ቀን ይመጣል። ነገሮች መስተካከላቸው አይቀርም። ሕይወትም ይቀጥላል›› ስትል መልእክቷን አስተላልፋለች።

ዶክተር ያን ታንግ ቼን በስፔን ማድሪድ ከተማ በዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የሕክምና አገልግሎት ይሰጣል። አሁን ግን እጆቹ ታስረው ራሱን በቤቱ አግልሎ እንዲቀመጥና፣ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችንም ለመርዳት እንዳይችል ሆኗል።

ለሲኤንኤን አስተያየቱን የሰጠው የሕክምና ባለሞያው ዶክተር ያኔ፣ ‹‹የሕክምና ባለሞያዎች ጠንቃቃ ናችሁ። ብዙ መከላከያም አላችሁ። በምን በኩል አንተን ሊይዝህ ቻለ?›› የሚል ጥያቄ ከሲኤንኤን ጋዜጠኛ ቀርቦለት ነበር። ይህን ሰው በቫይረሱ የተያዘው ከሥራ ባልደረባው በነበረው ንክኪና መቀራረብ ሲሆን፣ይህም የሆነው ቫይረሱን ለመከላከል መደረግ ያለባቸው ጥንቃቄዎች እንደ አሁኑ ይፋ ባልሆኑ ጊዜ ነበር ብሏል።

ሕመሙ መለስተኛ እንደሆነ የጠቀሰው ዶክተሩ፣ ቀላል አድርጎ ማየት፣ አለመጠንቀቅና መዘናጋት የሚያስከፍለውን ዋጋ ሳይጠቅስ አላለፈም። ‹‹የሕክምና ባለሞያ የሆናችሁ የሥራ አጋሮቹ፣ በየትኛውም አጋጣሚ ጥንቃቄን እንዳትረሱ፤ አደራ›› ሲልም አሳስቧል።

ዘር፣ መደብና ዕድሜ የማይለየው ኮቪድ 19
በ198 አገራት የተሰራጨው ኮሮና ኮቪድ 19 የበርካታ ሰዎችን ሕይወት ከመቅጠፉም ዓለም ዐቀፋዊ ዝናን የተጎናጸፉ ስፖርት ቤተሰቦችን፣ ታዋቂ የፊልም ሰዎችን፣ ለሰማይ ለምድር የከበዱ የዓለም ፖለቲካን እንዘውራለን የሚሉ የኃያላን አገራት መሪዎችንም ሳይነካካቸው እና ሳያስደነግጣቸው አልቀረም። በተለይም ደግሞ ከካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ቱሪዶ፣ ባለቤት ሶፊ ግሪጎሪ እስከ ፈረንሳዩ የባሕል ሚኒስቴር ፈራንክ ሪስተር፣ ከአሜሪካዊው የባህር ኃይል ጄነራል እስከ ኢራን የጤና ሚኒስትር ድረስ፣ ቫይረሱ ያልገባበት የለም።

ከዚሁ ባለፈም በሆሊውድ ፈርጦች ላይም የጭቃ ጅራፉን ያነሳው ኮቪድ 19፣ እንግሊዛዊውን የጥበብ ሰው ኤድሪስ ኢልባን ጨምሮ ቶም ሐንክስን ከእነባለቤቱም በመያዙ፣ ራሳቸውን ለይተው እንዲቀመጡ ምክንያት ሆኗል። በአፍሪካም ምድር የ30 ዓመቱን ወጣት እና ታታሪ ዚምባቡዌያዊ ጋዜጠኛን ዞሮሮ ማካምባን ሮጦ ያልጠገባትን ምድር ገና ብዙ መሥራት እያለበት ነበር በአጭር ያስቀረው። ይህ ሁሉ ወጣትን አይደፍርም፣ ቢይዝም ለክፉ አይሰጥም የሚለውን የልምድ አባባል ፉርሽ ያደረገ ክስተት እንደሆነ አሁን ብዙዎች የተስማሙበት ጉዳይ ሆኗል።

‹ዘ ኬኒ ሪፖርት›› የተሰኘ መሰናዶ በስካይ ኒውስ የሚያቀርበው አውስትራሊያዊው ፖለቲከኛና ዘጋቢ ክሪስ ኬኒ፣ ከኮቪድ19 ኮሮና ቫይረስ መከሰት በኋላ የሚሠራበት የስካይ ኒውስ ቢሮ ምን ያህል ጭር እንዳለ ያብራራል። ሠራተኞች በየቤታቸው ሆነው እየሠሩ መሆናቸውን አስታውሶ፣ ‹‹ዓለም እየተቀየረች ነው›› አለ።
እርግጥም ዓለም እየተቀየረች ይመስላል። ይህ ለውጥ ከስድስት ወራት የዘለለ እንዳይሆን የብዙዎች ምኞት ቢሆንም፣ ሥራቸውን ያጡ ሰዎች፣ መኖርንና ሕይወትን መቀጠል ስጋት የሆነባቸው፣ ቀኑም የዓመት ያህል ረዝሞባቸዋል። በዚህም ውስጥ ግን የሚመዘገቡ ድሎች፣ አገግመው ከሕክምና ተቋማት የሚወጡና፣ በሕክምና ላይ ያሉ እንዲጠነክሩ የሚያበረታቱ ሰዎች፣ ‹‹ይህም ያልፋል!› እያሉ ይገኛሉ።

‹‹መፍትሔው እኛ ጋር ነው፤ ለሁሉም ነገር መንግሥት መልስ አይደለም። ይህንን ቫይረስ ለማኅበረሰብ እንደተሰጠ ፈተና እቆጥረዋለሁ›› የኬኒ አገላለጽ ነው። ይልቁንም ልግስና፣ መግባባት፣ መልካምነት፣ እርስ በእርስ መጠባበቅ ነው ይህን ፈተና ሊያሻግረን የሚችለው ብሏል።

ቅጽ 2 ቁጥር 73 መጋቢት 19 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here