በጌዴኦ ዞን በሦስት ወረዳዎች የበረሀ አንበጣ ጉዳት እያደረሰ ነው

0
537

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት በጌዴኦ ዞን በይርጋ ጨፌ፣ ራፔ እና ቡሌ ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ 19 ቀበሌዎች ላይ የበርሀ አንበጣ ሰፍሮ በአርሶ አደሩ ሰብል ላይ ከፍተኛ ውድመት እያደረሰ መሆኑ ተገለጸ።

በዞኑ ውስጥ በሚገኙ በሦስቱ ወረዳዎች ለስድስተኛ ጊዜ የተከሰተው የበርሀ አንበጣ፣ እስከ አሁን በዞኑ ተከስቶ ከነበረው የበርሃ አንበጣ ይልቅ ከፍተኛ ቁጥር ያለውና የከፋ ጉዳት እያስከተለ እንደሚገኝ የዞኑ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት መምሪያ ኃላፊ ተገኝ ታደሰ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። የበርሀ አንበጣው በስፋት ከሰፈረባቸው 19 ቀበሌዎች ውስጥ ከይርጋ ጨፌ ወረዳ ቡልሽና ኢርቻ፣ ከቡሌ ወረዳ አዋዶና ኤዴ ሄሬአ እንዲሁም ከራፔ ወረዳ ቶራ መጥሪ ወካ በዋነኝነት እንደሚገኙበትም ተገኝ አብራርተዋል።

በዞኑ የተከሰተው የበረሀ አንበጣ በዞኑ የሚገኙ የሰብል ልማቶች ላይ ውድመት እያስከተለ ሲሆን፣ በዋናነት ግን እስከ አሁን በቡና፣ በባህር ዛፍ፣ በጎመን፣ በእንሰት እና በባህላዊ የንብ ቀፎዎች ላይ ያደረሰው ውድመት ከፍተኛ መሆኑን ኃላፊው ጨምረው ገልጸዋል። በተለይም በይርጋ ጨፌ ወረዳ የበረሀ አንበጣው ከሰፈረ አምስት ቀናትን እንዳስቆጠረ እና በአካባቢው ገና በአበባ ላይ የነበረ የቡና ስብል ልማትን እንዳወደመ ኃላፊው ጠቅሰዋል።

በአካባቢው ያለው ዝናባማ የአየር ሁኔታ ለአንበጣው ምቹ ሁኔታን እንደፈጠረለትና በሰፈረበት ቦታ ላይም ተመቻችቶ እንዲቆይ እንዳደረገውም ለማወቅ ተችሏል። ከዚህም በተጨማሪ በአካባቢው ባሉ ረጃጅም ዛፎች ላይ መስፈሩ ለማባረርም ትልቅ ተግዳሮት እንደሆነ ከዞኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

በዋነኛነት በዞኑ ያለው የሕዝብ አሰፋፈር ሁኔታ እና ከፍተኛ የሆነ የእንስሳት ክምችት የኬሚካል ርጭት እንዳይደረግ ከፍተኛ ተግዳሮት የፈጠረ ሌላኛው ማነቆ መሆኑም ተያይዞ ተገልጿል። በግብርና ሚኒስቴር የእጽዋት ጥበቃ ዳይሬክተር ዘብዲዮስ ፈላታ በጌዴኦ ዞን ባሉ ሰባት ወረዳዎች በእያንዳንዱ ወረዳ በነፍስ ወከፍ ሦስት ባለሙያዎች ለአካባቢው የሚመጥን የመከላከል ሥልጠና ወስደው እየሠሩ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ዳይሬክተሩ አካባቢው ቀዝቃዛ በመሆኑ ቀዝቃዛ ቦታዎች ላይ ምን መደረግ እንዳለበት ሠልጥነው ከፌዴራልም የተላኩ ባለሙያዎችም በቦታው ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
ዘብዲዮስ አንደገለጹት፣ በአሁኑ ጊዜ በጌዴኦ ዞን ሰፍሮ የሚገኘው የበረሀ አንበጣ መንጋ ከዚህ በፊት ቦረና አርፎ የነበረ ነው። ፀረ ተባይ በሚረጭበት ጊዜ ኹለት መንጋ አምልጦ ወደ ዞኑ እንደገባም አስታውሰዋል።

ዘብዲዮስ እንደሚሉት ካለው የኅብረተሰቡ የአሰፋፈር ሁኔታ አንጻር በአውሮፕላን ፀረ ተባይ መድኃኒት መርጨት ባይቻልም፣ ኅብረተሰቡ ከፌዴራል እና ከክልል ከተላኩ ባለሙያዎች ጋር በመተባበር ዝናብ በሚያቆምበት ጊዜ አስፈላጊውን የመከላከል ሥራ እንዲሠራ አቅጣጫ መሰጠቱን ጠቁመዋል።

በግብርና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ሞገስ ኃይሉ፣ የበርሀ አንበጣው ከጌዴኦ ዞን ባለፈም በክልሉ ውስጥ በስድስት ቦታዎች እንቁላል መጣሉን ተናግረዋል። የበርሀ አንበጣው አንቁላል ከጣለባቸዉ ቦታዎች ውስጥ የደቡብ ኦሞ ዞን ኮንሶ ወረዳ አንዱ መሆኑንም ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል። የአየር ሁኔታውንና አንበጣዎቹ በብዛት እንቁላል መጣላቸውን ተከትሎ፣ በአገሪቱ የሚከሰተው የበርሀ አንበጣ ከዚህ በኋላ ሊጨምር እንደሚችል ሞገስ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 73 መጋቢት 19 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here