ኢትዮጵያ ከሱዳን የምታስገባውን ነዳጅ አቆመች

0
1023

ኢትዮጵያ ከሱዳን የምታስገባቸውን የነዳጅ ምርቶች በጊዜያዊነት ማቆሟን የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ኤጀንሲ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ። ኤጀንሲው እንደገለጸው፣ ሱዳን በአገሯ የኮቪድ 19 ስርጭት እንዳይስፋፋ በምታደርገው ክልከላ ምክንያት ከሱዳን ይገባ የነበረው የነዳጅ ምርት ሙሉ በሙሉ ቆሟል። ኤጀንሲው አያይዞም በጊዜያዊነት የቆመው የነዳጅ ምርቶችን ከሱዳን የማስገባት ሂደት ሊቀጥል እንደሚችል አብራርቷል።

በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ከሱዳን የምታስገባው የነዳጅ ምርት ሊቆም የቻለበት በዋናነት ሱዳን ከኢትዮጵያ ወደ ግዛቷ የሚገቡ አሽከርካሪዎችን ከወረርሽኙ ስርጭት ፍራቻ ጋር በተያያዘ ጤንነታቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ካላቀረቡ እንዳይነቀሳቀሱ እግድ በማውጣቷ ነው። አሽከርካሪዎች ጤነኝነታቸውን የሚያስረዳ የሕክምና ማስረጃ ካላቀረቡ ለ14 ቀን በለይቶ ማቆያ እንዲቆዩ በመጠየቋ እና ይህ ደግሞ ነዳጅ ማመላለስ ሂደቱን ስለሚያጓትተው የነዳጅ ምርቱን ማስገባት አልተቻለም ተብሏል።

የተፈጠረውን ጉዳይ በሚመለከት የኢትዮጵያ ነጋጅ አቅራቢ ደርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ታደሰ ኃይለማሪያም፣ ኢትዮጵያ ከሱዳን የምታስገባው ቤንዚን ከመጋቢት 15/2012 ጀምሮ እንዳቆመ እና ለአገሪቱ የሚያስፈልገውን ፍጆታ ለማቅረብ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ከዚህ በፊት ከጅቡቲ ያስገባ የነበረው ነዳጅ መጠን በመጨመር እያስገባ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከሱዳን የምታስገባውን የነዳጅ ምርት አቅርቦት ለመተካት በጅቡቲ በኩል ከዚህ በፊት ይገባ የነበረውን 1.8 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ወደ ኹለት ሚሊዮን ከፍ በማድረግ ለማካካስ እየተሠራ መሆኑን አያይዘው አንስተዋል። መንግሥትም ችግሩን ለመፍታት በሱዳን በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል እየተነጋገረ እንደሚገኝ ዋና ሥራ አስፈፃሚዉ ጠቁመዋል።

እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚዉ ገለጻ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ሙሉ በሙሉ የነዳጅ ምርቶችን የምታስገባው በጅቡቲ በኩል ነው። ነገር ግን በጅቡቲ በኩል ያለው የማጓጓዝና የማስተናገድ አቅም ከሚችለው በላይ መሆኑን አክለው ተናግረዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ከሱዳን የምታስገባው 20 በመቶ ነዳጅ ምርት በመቅረቱ በተወሰነ ሁኔታ በአማራ ክልል እጥረት ተፈጥሮ ነበር። በአማራ ክልል እጥረት ያጋጠመበት ምክንያት ኢትዮጵያ ከሱዳን የምታስገባው ነዳጅ በአማራ ክልል በኩል ገብቶ ለክልሉ ይሰራጭ ስለነበር እንደሆነ አስረድተዋል። ይሁን እንጂ በአሁኑ ሰዓት በክልሉ ተፈጥሮ የነበረው መጠነኛ የቤንዚን እጥረት ከጅቡቲ ከሚገባዉ ወደ ክልሉ በማጓጓዝ እና በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በክልሉ እንቅስቃሴዎች በመገታታቸው እንዲሁም የነዳጅ ፍላጎቱም በመቀነሱ እጥረቱ እየተፈታ እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ ጨምረው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በዓመት የምታስገባዉ ጠቅላላ ነዳጅ ሦስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ሲሆን፣ ከምታስገባው ነዳጅ 10 በመቶ የሚሆነው ቤንዚን ወይም ከጠቅላላው ነዳጅ ምርት 400 ሺሕ ሜትሪክ ቶን የሚሆነው ቤንዚን ነው። ከዚህም 20 በመቶ የሚሆነውን የቤንዚን ምርት የምታስገባው ከሱዳን ነበር።

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከጅቡቲ ነዳጅ ለማጓጓዝ የሚወስደው ጊዜ በኮሮና ቫይረስ ስርጭት ምክንያት የመዘግየት ችግር እንዳለ እና በተፈለገው ጊዜ እየደረሰ እንዳልሆነ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዓለማየሁ ፀጋዬ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድረጅት በ2012 በጀት ዓመት በመጀመሪያው 6 ወራት በጥቅሉ ኹለት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የተጣራ ነዳጅ ምርት ለማቅረብ አቅዶ፣ 1.945 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በ45.73 ቢሊዮን ብር አስገብቷል።

የአለም የነዳጅ ዋጋ በኮረና ቫይረስ መከሰት ምክንየት አንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ በሚያዚያ ወር 24.42 ዶላር ዋጋ የተቆረጠለት ሲሆን ፤ ወረርሽኙ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተስፋፋ ጀምሮ ዋጋው እያሽ ቆለቆለ እንደሚገኝም ታውቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 75 ሚያዝያ 3 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here