ቢ.ጂ.አይ. ኢትዮጵያ አራት ፋብሪካዎቹን ዘጋ

0
1399

ቢ.ጂ.አይ. ኢትዮጵያ በኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ባጋጠመው የፍላጎት እጥረት ካሉት አምስት ፋብሪካዎቹ ውስጥ አራቱን መዝጋቱን አስታወቀ። ፋብሪካው ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው፣ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የተስፋፋው ወረርሽኝ በፋብሪካው ላይ ተጽዕኖ በማድረሱ አሁን በውል የማይታወቅ ኪሳራ የደረሰበት ሲሆን፣ ይህንም ተከትሎ አራቱን ፋብሪካዎቹን ለመዝጋት መገደዱን አስታውቋል።

ፋብሪካው አያይዞ እንዳስታወቀውም የተፈጠረውን የገበያ መቀዛቀዝ ለመፍታት አዳዲስ እቅዶችን እየተከተለ ሲሆን፣ ችግሩ ግን ከዚህም የባሰ ሊመጣ እንዳለ መገመት እንደሚያስችል አስታውቋል።

የቢ ጂ አይ ኢትዮጵያ የንግድ እና ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ገብረሥላሴ ሲፈር ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት፣ ፋብሪካው አራት ሺሕ ቋሚ እና ጊዜያዊ ሠራተኞች አሉት። ፋብሪካው አሁን ባጋጠመው የገበያ መቀዛቀዝ ሠራተኞችን ለመቀነስ ሐሳብ እንደሌለው እና ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም ሠራተኞችን ይዞ ለመቀጠል እንደሚሞክር አስታውቀዋል።

ፋብሪካው እንደ አማራጭ ብሎ ከተጠቀማቸው አዳዲስ የንግድ እቅዶቸ ውስጥ ከቤት ለቤት አከፋፋይ ኩባንያዎች ጋር በመነጋገር ምርቱን ለተጠቃሚዎች ቤት ለቤት በማድረስ እና ተደራሽነቱን ማስፋት እንደሆነ ተናግረዋል። ምንም አይነት ቋሚ ሠራተኞቹን አለመቀሱን ያስታወቀው ፋብሪካው፣ ያሉት ሠራተኞች በስራቸው የሚያስተዳድሯቸው ቤተሰቦች ቁጥራቸው ሰፋ ያለ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ማኅበራዊ ቀውስ ይፈጠራል በሚል እስከ አሁን እንደታገሰ እና በቀጣይም የሚችለውን በማድረግ ለማቆየት እንደሚሞክር አስታውቋል።

ከክልሎችና ከፌዴራል መንግሥት ጋር ወረርሽኙን ለመግታት ፋብሪካው በጋራ እየሠራ እንደሆነ የሚናገሩት ገብረሥላሴ፣ ሦስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ወረርሽኙን ለመግታት እንዲውል እርዳታ ለግሷል። በቀጣይ ደግሞ የቢራ አምራች ዘርፉ እንዲያገግም ከመንግሥት ድጋፍን እንደሚሹ እና ያም እውን ይሆናል ብለው እንደሚጠብቁ አስረድተዋል።

ቢጂአይ ኩባንያ በ53 አገራት ፋብሪካዎችን በመትከል የአልኮል መጠጦችን የሚያመርት ድርጅት ሲሆን በኢትዮጵያም ለ22 ዓመታት በሥራ ላይ ቆይቷል። ቢጂአይ ኢትዮጵያ ቀደምቱን 96 ዓመታትን ያስቆጠረውን የቢራ አምራች ፋብሪካ ቅዱስ ጊዮርጊስን ጨምሮ አምስት የቢራ ፋብሪካዎች በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች አሉት።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ በአዲስ አበባ፣ ኮምቦልቻ ቢራ ፋብሪካ፣ ሐዋሳ ቢራ ፋብሪካ፣ ዘቢዳር ቢራ ፋብሪካ እና ማይጨው ቢራ ፋብሪካ ናቸው። ፋብሪካው ከአምስቱም ቋቶቹ በድምር 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክቶ ሊትር ቢራ በዓመት እንደሚያመርትም ለማወቅ ተችሏል። ቢ.ጂ.አይ. ኢትዮጵያ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ካስትል፣ ፓናሽ፣ ዘቢዳር እና ራያ የተባሉ የቢራ ምርቶቹን ለገበያ በማቅረብም ይታወቃል።

ኩባንያው ከቢራ ፋብሪካዎች ባለፈም ከስምንት ዓመታት በፊት በዝዋይ ከተማ ካስቴል ዋይን ፋብሪካን ገንብቶ እና የወይን እርሻዎችን በመጀመር ወደ ሥራ ገብቷል። ከወይን ምርቱም አካቺያ እና ሬፍት ቫሊ በተሰኙ ምርቶቹ 12 ሺሕ ሔክቶ ሊትር ወይን በዓመት ለገበያ ያቀርባል።

ከሆቴል እና ቱሪዝም ኢንዱስትሪው መቀዛቀዝ ጋር ተያይዞ የቢራው ንግድ መቀዛቀዙን የታዘበው ፋብሪካው፣ ደንገተኛ እና ከባድ መሆኑ እንጂ የከፋው ጊዜ ግን ወደ ፊት እንደሚመጣ ገና ፍራቻ እንዳላቸውም ገብረሥላሴ ይናገራሉ። አሁንም ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር አብሮ የሚሄድ የአሰራር ስርዓትንም በመጠቀም በሥራ ላይ ለመቆየት ሙከራ ላይ እንደሆኑም ተገልጿል።

ቅጽ 2 ቁጥር 75 ሚያዝያ 3 2012

 

ውድ አንባቢዎቻችን በአዲስ ማለዳ 75ኛ ዕትም በወጣው ይህ ዜና ውስጥ ሰራተኞች ያለ ክፍያ ዕረፍት እንዲወጡ ተደርገዋል ብለን በስህተት ገልፀን ነበር። ከድርጅቱ በተሰጠን መረጃ መሰረት ሰራተኞቹ በክፍያ የስራ ወጥተዋል በሚል ማስተካከያ አድርገናል። ለተፈጠረውም ችግር ቢጂአይ እና አንባቢዎቻችንን ይቅርታ እንጠይቃለን።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here