በአማራ ክልል 11 ሺሕ የሚሆኑ ነጋዴዎች ላይ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ማድረጋቸውን ተከትሎ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱ ተገለፀ።
በአማራ ክልል ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉና በሕገ ወጥ መልኩ ሲንቀሳቀሱ በተገኙ ከ11 ሺሕ በላይ ነጋዴዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰዱን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታውቋል።
ከዛም በተጨማሪ 157 ነጋዴዎችም በሕግ ተከስሰው በፖሊስ አስፈላጊው ማጣራት እየተደረገባቸው መሆኑ ተገልጿል። ቢሮው መጪውን የፋሲካ በዓል ግብይት የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል በሚያስችል መልኩ ለማከናወን እንዲቻል እየተሠሩ ያሉ ተግባራትን አስመልክቶም ኅብረተሰቡ በተወሰነው መሰረት መንቀሳቀስ ይኖርበታል ሲሉ ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የንግድ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ተዋቸው ወርቁ በበዓል ወቅት የሚከናወነው የእርድ እንስሳት ግብይት በዋና ሳይሆን በንዑስ የገበያ ቦታዎች እንዲከናወን ለማድረግ በከተሞች ንዑስ የገበያ ቦታዎች እየተዘጋጁ ነው ብለዋል።
በገበያ ሊከሰት የሚችለውን መሰባሰብ ለመቀነስም የዶሮ እንቁላል የመሳሰሉ የግብርና ምርቶች የቤት ለቤት ግብይት በማከናወን ሊፈጠር የሚችለውን ግርግር መቀነስ ይገባልም ብለዋል።
ከዛም በተጨማሪ ነጋዴዎችም በዚህ ወቅት ስለማትረፍ ሳይሆን ይህንን ወቅት አንድ ላይ ለማለፍ በማሰብ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ከማድረግ እንዲቆጠቡ አሳስበዋል። ሸማቹ ከንክኪ በፀዳ መልኩ ግብይት እንዲፈፅምና አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል። ተዋቸው እንደገለጹት ሕገ ወጥ ንግድና ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖርም የንግድ ተቆጣጣሪ አካላት ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ክትትል እየተደረገ ነው ሲሉም አስታውቀዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 76 ሚያዝያ 10 2012


