ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ለመጀመሪያ ጊዜ የኮሮና ቫይረስ ሕሙማንን በኤካ ኮተቤ ሆስፒታል በመገኘት የጎበኙ ሲሆን፣ በተቋመጁ እያገለገሉ ላሉ የሕክምና ባለሞያዎችም ስጦታዎችን አበርክተዋል።
ከትላንት በስቲያ ሚያዚያ 8 ቀን 2012 ወደ ሆስፒታሉ ካቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸውና ኢንጂነር ታከለ ኡማ የተገኙ ሲሆን፣ ታማሚዎችን አበረታተዋል፣ የጤና ባለሞያዎችንም አመስግነዋል።
በእለቱ በተመሳሳይ ተጨማሪ የፉሲካ በዓል ስጦታዎችን የተለያዩ ቦታዎች በመጓዝ ያበረከቱ ሲሆን፣ አፍንጮ በር አካባቢ በሚገኝ ሕጻናት ማሳደጊያም በተመሳሳይ ስጦታዎችን ሰጥተዋል።
ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ኅብረተሰቡ እንዲረዳዳና እንዲተጋገዝ ጥሪ አቅርበው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አሁንም ጉብኝቱን አስመልክተው በፌስቡክ ገጻቸው እንዳሰፈሩት፣ ርቀትን እየጠበቁ ማኅባራዊ ትስስርን ማጠናከር የሚጠይቅ ጊዜ ነው። በርኅራኄና በልግስና ለሌሎችም መትረፍ ይጠበቅብናልም ብለዋል።
‹‹የከፋ ችግር ለገጠማቸው የድጋፍ እጃችንን የምንዘረጋበት እና የጋራ መከራችንን በአንድነት የምንጋፈጥበት ጊዜ ነው›› ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 76 ሚያዝያ 10 2012