ወረርሽኙን ለመግታት መንግሥት ጥብቅ እርምጃ ለመውሰድ አያመንታ!

0
634

ከቻይና ቀጥሎ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ማእከል ሆና በቆየችው ጣልያን የመጀመሪያው በቫይረሱ መያዙ የተረጋገጠ ሰው ከታወቀ አሁን ኹለት ወር እንኳን አልሞላም። የ38 ዓመቱ ሰው በሰሜናዊ ጣልያን ሎዲ በምትባል የሚላን ክፍል ከተገኘ በኋላ የመጀመሪያዎቹ የአገሪቱ የቫይረሱ ተያዦች በአካባቢው ነበር የበዙት። ወረርሽኙ እየተዛመተ ሲሄድ እንደ አሜሪካዋ ኒው ዮርክ የችግሩ ገፈት ቀማሽ የነበረችው ሎምባርዲም ከሎዲ ብዙም የማትርቅ ሚላን ውስጥ ያለች ቦታ ነች።

ይህ ሰሜናዊ የአገሪቱ ግዛት የጣልያን ኢኮኖሚ ሞተር በመባል የሚታወቅ ሲሆን ይህንን ቦታ መዝጋት የሚያመጣው ችግር ከአካባቢው አልፎ በአገር እና በአኅጉር ደረጃ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ስለሚታመን አስተዳዳሪዎች ውሳኔውን ለመውሰድ አመንትተዋል። እንዲያውም የቫይረሱን ስጋት ዝቅ ዝቅ ማድረግ ጀምረው ነበር።

ለዚህም በዋናነት እንደማሳያ የሚጠቀሰው የሚላኑ ከንቲባ “ሚላን አትቆምም” የሚል ዘመቻ ቫይረሱ አገሪቷ ውስጥ በተገኘ በስድስተኛው ቀን አውጀው፣ መጠጥ ቤቶች ሌሊቱን ክፍት ሆነው እንዲቆዩ ማድረጋቸው ነው። በ12ኛው ቀን ደግሞ የሚላኑ ትልቁ ካቴድራል ተመልሶ እንዲከፈት ከማድረጋቸውም በላይ ሙዚየሞችም ለቱሪስቶች እንዲከፈቱ ወስነው ነበር። የሚገርመው ግን ይህን ውሳኔ በወሰኑበት በ12ኛው ቀን የተያዙ ሰዎች ቁጥር ኹለት ሺሕ ደረሰ።

የመጀመሪያው ሰው በሎዲ ከተገኘ ከ20 ቀን በኋላ የቫይረሱ ስርጭት እጅጉን ስለጨመረ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ እንቅስቃሴዎች ብቻ ካልሆኑ በስተቀር ሌላ እንቅስቃሴን በሙሉ አገዱ። ነገር ግን በእገዳው ውስጥ የተካተቱት ሕጎች ገልፅ እንዳልነበሩ እና አፈጻጸሙም የላላ እንደነበር ይተቻል። መጠጥ ቤቶች፣ ምግብ ቤቶች እና ሱቆች ሙሉ በሙሉ የተዘጉትም ከ22ኛው እስከ 30ኛው ቀን ነው።

የእንቅስቃሴ ገደቡ ከ20ኛው ቀን ጀምሮ የተጣለ ሲሆን አብዛኞቹ ሰዎች በቤታቸው ከዚሁ ጊዜ ጀምሮ ቆይተዋል። ነገር ግን ሰዉ ወደ ቤቱ ከገባ በኋላ ነበር ከፍተኛው የቫይረሱ ስርጭት የታየው። ለመዝጋት ባመነቱበት ጊዜ ብዙ ሰው ለቫይረሱ ተጋልጦ እንደቆየ እና ቤቱ ከገባም በኋላ ምልክቶቹን ማሳየት እስኪጀምር ቤተሰቡንም እያስያዘ እንደቆየ የሚጠቁም ነው።

በዚህም ጊዜ በቀን ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ ተያዦች ይመዘገቡ ነበር። በመሆኑም ዘግይቶ የሚደረግ የእንቅስቃሴ እገዳ ችግሩን ወደ ቤት በማስገባት ከፍተኛ የሆነ ስርጭትን ሊያስከትል ይችላል።

በሌላ በኩል ደግሞ ደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያ የቫይረሱ ተያዥ ሰውን ከለየች ከ22 ቀናት በኋላ የእንቅስቃሴ ገደቡን የጣለች ሲሆን፣ እስከዛ ጊዜ ድረስ ግን ወረርሽኙ በአሜሪካ እና እንግሊዝ እንደታየው ዓይነት ፈጣን እድገት ሲያሳይ ነበር። የሌሎች አገሮች የበሽታ መዛመት ሁኔታን ግምት ውስጥ በማስገባት በወጣው ትንበያ መሠረት አገሪቱ ከ16 ቀናት በፊት አራት ሺሕ የተያዙ ሰዎች ይኖሩባታል ተብሎ ተገምቶ ነበር። ነገር ግን ከእንቅስቃሴ ገደቡ በኋላ በቀን የሚያዙት ሰዎች ቁጥር እጅጉን አሽቆልቁሎ በቋሚነት 70 አካባቢ ደርሷል። በዚህም መሠረት ከአራት ቀናት በፊት ያለው የተያዙ ሰዎች ቁጥር 2415 ሲሆን ከ16 ቀናት በፊት ትደርስበታለች ተብሎ ተገምቶ ከነበረው በ1585 ያነሰ ነው።

በዚህም በአሁኑ ጊዜ የበሽታውን ስርጭት የሚያሳየውን ግራፍ ቀጥ ብሎ ከመውጣት አግድም እንዲሔድ አድርጋዋለች፤ ደቡብ አፍሪካ። የበሽታው ስርጭት በእጅጉ መቀነስ አነስተኛ ምርመራ ከማድረግ ጋር ይገናኛል የሚሉ ስጋቶች የነበሩ ቢሆንም፣ እንደውም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎች በሰፊው የሚመረመሩበት ጊዜ በመሆኑ እንደማያስኬድ ባለሙያዎቹ እየጠቆሙ ነው።

በመሆኑም ይህ ቅፅበታዊ ማሽቆልቆል በተወሰዱት የድንበር መዝጋት፣ የማኅበራዊ ፈቀቅታ እና የእንቅስቃሴ እገዳ እርምጃዎች ምክንያት የተከሰተ እንደሆነ ይታመናል። ደቡብ አፍሪካውያኖቹም ይህ የወረርሽኙ ጋብ ማለት ቀድመው ለመዘጋጀት የሚያስፈልገውን ጊዜ እንዲያገኙ እንዳደረጋቸው እየተናገሩ ነው።

ከላይ ካየናቸው ኹለት የተለያዩ ሁኔታዎች መረዳት የሚቻለው ጊዜውን የጠበቀ የእንቅስቃሴ ገደብ ሕይወት አድን መሆኑን እና ከዘገየ ደግሞ ሕዝብ ጨራሽ እንደሚሆን ነው። ጊዜውን የጠበቀ መሆኑ ሕይወት ከማዳንም በተጨማሪ አገሮች በወረርሽኙ ከፍተኛ ተፅዕኖ ውስጥ ለረጅም ጊዜ እንዳይቆዩ በማድረግ የኢኮኖሚው ጫና በአንጻራዊ ሁኔታ ጋብ እንዲል ይረዳል።

የኢትዮጵያን ሁኔታ በምናይበት ጊዜ አዳዲስ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች አሁንም ቢሆን በአብዛኛው የውጭ አገር ጉዞ ታሪክ ያላቸው ወይም መያዙ ከታወቀ ሰው ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው። ይህም ቫይረሱ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ከወር በላይ ከሆነው በኋላም የስርጭቱ ሁኔታ እንደሌሎች አገሮች በፍጥነት እየሄደ እንዳልሆነ ማሳያ ነው። ነገር ግን ጥቂት ቫይረሱ ከየት እንደያዛቸው በግልጽ ያልታወቁ ሰዎች መታየት መጀመራቸው በማስጠንቀቂያነት ሊወሰድ ይገባል።

መንግሥት የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር ጥረት እያደረገ እንደሆነ የሚታወቅ ቢሆንም፣ የተወሰዱት እርምጃዎች በቂ መሆን ያለመሆናቸው ላይ በባለሙያዎች ውይይት ሲደረግበት አይታይም። ለምሳሌ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎቹን ሙሉ ለሙሉ ያለማቆም አዳዲስ የተያዙ ሰዎችን ወደ አገሪቱ ውስጥ የማምጣት ሚናው ምን ያህል እንደሆነ በውል የሚታወቅ አይመስልም። ምንም እንኳን አየር መንገዱ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ያለው ከፍተኛ ሚና ተደጋግሞ የሚገለፅ ቢሆንም፣ የኪሳራ መጠኑን ከዜጎች ሕይወት ጋር ማለካካት ግን የሚያስሄድ መንገድ አይደለም። በመሆኑም ውሳኔዎች ከምን ዓይነት ውይይቶች ውስጥ እንደወጡ በሚያሳይ መንገድ ለሕዝብ ግልጽ ሊደረጉ ይገባል።

የፋይናንስ ሚኒስትሩ ኢዮብ ተካልኝም ባለፈው ሳምንት በቪዲዮ ኮንፍረንስ በተዘጋጀ ስብሰባ ላይ የምናጣው ብዙ ስለሆነ ወረርሽኙ በኢኮኖሚው ላይ ረጅም ጊዜ የሚቆይ መናወጥ እንዲያስከትል ማድረግ አንችልም ብለው ነበር። ምንም እንኳን በዚህ ከባድ ጊዜ ኢኮኖሚውን ለመጠበቅ የሚያስችሉ እርምጃዎች መውሰድ ቢያስፈልግም፣ እርምጃው በጣልያን የታየውን ዓይነት መዘናጋት እንዳያስከትል መጠንቀቅ ያስፈልጋል።

የእንቅስቃሴ ገደብ ለመጣል ሌላ ማነቆ ሆኖ የሚታየው ችግር ደግሞ በዋና ከተማችን አዲስ አበባ ውስጥ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ የየዕለት ገቢያቸው ላይ ሕይወታቸውን የመሠረቱ ሰዎች መኖራቸው ነው። ሙሉ በሙሉ የእንቅስቃሴ እገዳ ማድረግ እነዚህ ሰዎች አደጋ ላይ እንዲወድቁ ሊያደርግ ስለሚችል ጉዳዮን ውስብስብ ያደርገዋል። ሊመጣ የሚችለውን ችግር ለመቀነስ የከተማው መስተዳድርም ሆነ ፌዴራል መንግሥት ገንዘብ እና ቁሳቁስ እያሰባሰቡ እንደሆነ የሚታወቅ ነው።

አሁን ያለው እርምጃ እንቅስቃሴ ላይ የተወሰነ ገደብ የሚጥል ቢሆንም ከበዓል መድረስ ጋር ተያይዞ የሰዎች እንቅስቃሴ እንደሚጨምር ከወዲሁ እየታየ ይገኛል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ቢሆን በአጥጋቢ ሁኔታ እየተገበረ ነው ማለት አይቻልም። የተጨናነቁ ገበያዎች ውስጥ ፊታቸውን በማስክ የሚሸፍኑ ሰዎች ቁጥር አሁንም አናሳ ነው፤ አራት እና ከዚያ በላይ ሰዎችም በሻይ ቤቶች ውስጥ ይታያሉ። አዋጁም መሠረታዊ የሆኑትን የማኅበራዊ ፈቀቅታ እርምጃዎች ለማሟላት እንጂ ከዚያ የዘለለ ጫና በሕዝብ ላይ ለመጫን የወደፊት ሂደቶችን የሚጠብቅ በመሆኑ፣ ለውጡ ያን ያህል ሊሰማ የሚችል አይደለም።

በዚህ ላይ ሕዝብ ከመንግሥት የተሰጠውን ትዕዛዝ ተቀብሎ በቀናኢነት ለመፈፀም ያለው ተነሳሽነት አነስተኛ መሆኑ እና የሥነ ምግባር ሁኔታ ጉድለት እየታየ መሆኑ እየተስተዋለ ነው።

በአጠቃላይ መንግሥት ለኢኮኖሚውም ሆነ ለሌላ ምክንያት ጥብቅ እርምጃዎችን ለመውሰድ እያሳየ ያለው ማመንታት የወጡ ሕጎችን ለማስፈፀም ካለው ደካማ አቅም እና የሕዝብ የሥነ ምግባር እጥረት ጋር ሲዳመር፣ የቫይረሱን ስርጭት ለማፋጠን ምቹ ሁኔታ ሊፈጥሩ እንደሚችሉ አዲስ ማለዳ ታምናለች።
በመሆኑም ሙሉ ለሙሉ የእንቅስቃሴ እገዳ ሳይዘገይ ጊዜውን ጠብቆ ሊደረግበት በሚችልበት መንገድ ላይ ግልጽ የሆነ ውይይት እና የስርጭት መጠኑን ግምት ውስጥ የከተተ የጊዜ ሰሌዳ ሊዘጋጅ ይገባል። ይህም ለሕዝብ ይፋ መሆን አለበት።

ቅጽ 2 ቁጥር 76 ሚያዝያ 10 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here