የፌዴራል መንግሥት ለትግራይ ክልል ለኮቪድ 19 መከላከል የሰጠው ድጋፍ አነስተኛ ነው ተባለ

0
747

የትግራይ ክልል የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል ከፌዴራል መንግሥት የተደረገለት የአስፈላጊ ቁሳቁስ ድጋፍ በቂ እንዳልሆነ እና ወረርሽኙን ለመግታት እንደማያስችለው አስታወቀ። ክልሉ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጸው ከፌዴራል መንግሥት የተደረገው ድጋፍ እዚህ ግባ የማይባል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ክልሉ ክፍተቱን ለመሙላት ባለሃብቶች ገንዘብ እንዲያዋጡ እያደረገ ይገኛል ተብሏል።

የትግራይ ክልል የሕዝብ ግንኙነት የሆኑት ሊያ ካሳ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት፣ የኮሮና ቫይረስ ኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመግታት በዓለም ዐቀፍ ደረጃ እንቅስቃሴ ላይ መኮኑን አስታውሰው፣ የትግራይ ክልልም ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል። ይሁን አንጂ አሁን በመሥራት ላይ ካሉት ሥራዎች መካከል የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ናሙና በመውሰድ የሚመረመርበት ቦታ በመቀሌ አንድ ቦታ ላይ ብቻ መሆኑን ገልፀው፣ ይህም በቂ አይደለም ብለዋል። ይህም ከፌዴራል መንግሥት የተሰጠው ድጋፍ ማነስ ምክንያት እንደሆነም ጠቁመዋል።

በትግራይ ክልል በሁሉም ቦታ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ተደርጓል እየተባለ የሚወራው ከእውነት የራቀ ነው በማለት የትግራይ ክልል ለአዲስ ማለዳ ገልጾ፤ ተገቢውን ልየታ እና የሙቀት ልኬት ለማወቅ እንኳን የፌደራል መንግሥቱ ለክልሎች በተለይም ለትግራይ ክልል የሰጠው ድጋፍ አነስተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እክል እንደገጠማቸው ተናግረዋል።

እንደ ሊያ ገለጻ የተጠረጠሩ ግለሰቦችን እና ከሌሎች ክልሎች የሚመጡ ግለሰቦችን ለይቶ ማቆያ መዘጋጀታቸውን እና ተጨማሪ በመዘጋጀት ላይ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በክልሉ ዋና ዋና ከተሞች ላይ የተጠረጠሩ ግለሰቦች የሚቆዩበት እና ናሙና በመውሰድ ወደ ማእከል የሚላኩባቸው ለይቶ ማቆያዎች የማዘጋጀት ሥራም እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

‹‹የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኙ ከገባ በኋላ ለመቆጣጠር ከአቅም በላይ መሆኑን ማመን ተገቢ ነው›› ያሉት ሊያ የትግራይ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቀድሞ ማውጣቱን አስታውሰው ክልላቸው ቀድሞ መከላከል ላይ ትኩረት ማድረጉንም አስታውቀዋል።

ከዛም በተጨማሪ በትግራይ ክልል የሚገኙት ባለሙያዎች ራሳቸውን ለመጠበቅ እንዲያስችላቸው መሟላት የሚገባውን የጤና ግብዓት በተቻለ መጠን ለማሟላት እየተሞከረ መሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል።

እንደ ሊያ ገለፃ ከሚቀጥለው ሰኞ ሚያዚያ 12/2012 ጀምሮ እስከ ሐሙስ ሚያዚያ 15/2012 የሚቆይ 23 ሺሕ የሚጠጉ የጤና ባለሙያዎች የቤት ለቤት እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል። በዚህም በማኅበረሰቡ ያለው ሁኔታ ላይ ጥናት የሚያደርግ ኮሚቴ ሲሆን ሙቀት የመለካት ሥራ እንደሚሠራም አስረድተዋል።
በዚህም እንቅስቃሴ አንድ የጤና ባለሙያ በከተማ በቀን 23 ቤቶችን እንዲመረምር ግዳጅ መጣሉንም ገልፀዋል። ከዛም በተጨማሪ በገጠሩ አካባቢ ያሉትን ደግሞ 15 የሚሆኑ ቤቶችን በቀን ፈትሾ እንዲውል እንደሚደረግ ሊያ ለአዲስ ማለዳ አብራርተዋል።

እስከ አሁን ምልክቱ ታይቶባቸው ለመመርመር 11 ናሙናዎች ተወስደዋል ያሉት ሊያ፣ ነገር ግን ውጤታቸው እስከ አሁን እንዳልታወቀ ተናግረዋል።
በተያያዘም ሊያ እንደሚገልጹት ለትግራይ የተመደበው በጀት ዝቅተኛ ቢሆንም ነገር ግን በትግራይ ክልል ያሉ ባለሃብቶች ለተለያዩ ተግባራት ማከናወኛ የሚውል የቤት ለቤት ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ በገንዘብ እና የሳኒታይዘር፤ የአልኮል እና የማስክ ወይም ጭንብል ለክልሉ በድጋፍ መልክ እያበረከቱ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በትግራይ ክልል የሚገኙ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እና ባንኮች፣ አነስተኛ የገንዘብ ተቋማት ከፍተኛ የሆነ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል። እነዚህን እርዳታዎች በማሰባሰብ ከተሰጠን በጀት ክፍተቱን ለመሙላት እየሠራን ነው ብለዋልም።

በተያያዘም የጤና ሚኒስቴር ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ተገኔ ረጋሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ መስፈርቱን ጠብቀን ለክልሎች ደልድለን አከፋፍለናል በማለት ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 76 ሚያዝያ 10 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here