የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት በዘንድሮው የ2012 የፋሲካ በዓል የሚከናወነው የእርድ መጠን ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ30 በመቶ ቅናሽ ሊያሳይ እንደሚችል አስታወቀ።
ድርጅቱ በዚህ የፋሲካ በዓል የእርድ መጠኑ ይቀንሳል ያለበት ዋነኛው ምክንያትም ዓለም ዐቀፉ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በኢትዮጵያ መከሰቱን ተከትሎ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመሰባሰብ ክልከላ፣ የክልሎች እንቅስቃሴ መገደቡ እና ኅብረተሰቡ እንደ ከዚህ ቀደም ሁሉ ሥጋ የመጠቀም አቅሙና ፍላጎቱ እንደቀነሰ የሚያሳዩ ጠቋሚ ምልክቶች ናቸው ሲል አስታውቋል።
የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ዮሴፍ ድሪብሳ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ በ2011 የፋሲካ በዓል የተከናወነው ጠቅላላ እርድ ከአሁኑ ጊዜ ጋር ሊመጣጠን እንደማይችል ማሳያዎች አመላክተዋል ብለዋል። በባለፈው ተመሳሳይ ዓመት ላይ ከ2 ሺሕ 200 እስከ 2 ሺሕ 300 የቀንድ ከብት እና ከአንድ ሺሕ 200 እስከ አንድ ሺሕ 300 ያክህል በግና ፍየል እርድ መከናወኑን ምክትል ሥራ አስፈጻሚው አስታውሰው፣ በአሁኑ ጊዜ ያለው ሁኔታ እንደሚቀንስ ጠቁመዋል።
በአሁኑ ዓመት ያለው የግብይት የዋጋ ሁኔታም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ጭማሪ ማሳየቱን የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት የቁም እንስሳት መገበያያ ማእከል ላይ የተደረገው ቅኝት ማሳየቱን ዮሴፍ ተናግረዋል። የዋጋ ጭማሪው የተከሰተበትን ምክንያት ለማጣራት ከነጋዴዎች ጋር በተደረገ ውይይት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላለከል በሚወሰዱ እርምጃዎች የክልሎች የእንቅስቃሴ መገደብ እና የሥጋ ከብቶችን ለገበያ የሚያቀርቡ አርሶ አደርችና አርብቶ አደሮች በወቅታዊ ሁኔታ ችግር ለገብያ በስፋት ባለማቅረባቸው መሆኑን ከነጋዴዎች መረዳታቸውን ዮሴፍ ገልጸዋል።
በአሁኑ ጊዜ የኮቪድ 19 ቫይረስ ከእንስሳት ወደ ሰው ይተላለፋል በሚል ስጋት ኅብረተሰቡ ሥጋ መመገብ እንደሌለበት በሳይንስ ያልተረጋገጠ መረጃ ይዞ እየተደናገረ ነው ያሉት ዮሴፍ፣ እስከ አሁን ኮሮና ቫይረስ ሥጋ በመብላት ከእንስሳት ወደ ሰው ይተላለፋል የሚል ተጨባጭ የሳይንስ ግኝት የለም። ስለዚህም ኅብረተሰቡ ከስጋት ነፃ ሆኖ ከግዥ እስከ ማዕድ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ እንዲያከናውንና እንዲጠቀም መክረዋል።
ነገር ግን በሌላ በኩል ከበዓሉ ጋር ተያያዞ ሥጋ የሚጠቀመው የኅብረተሰብ ክፍል በአገራችን በተከሰተው ወረርሽኝ ምክንያት የኅብረተሰቡ የኢኮኖሚ አቅምና ገቢ እንደተፈተነ የገለጹት ዮሴፍ፣ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሥጋ የመግዛት አቅም ስለማይኖራቸው የሚኖረው የሥጋ ፍላጎትም እንደሚቀንስ አመላክተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ቄራዎች ድርጀት በአዲስ አባበ ከተማ ተገቢ ባልሆነ መንገድ ሊከናወኑ የሚችሉ ሕገ ወጥ እርድን ከመቼውም ጊዜ በላይ ትልቅ ትኩረት የሚሻ በመሆኑ የአዲስ አባባ ቄራዎች ድርጅት ከአዲስ አበባ ፖሊስና ደንብ ማስከበር እንዲሁም ከአዲስ አበባ ከተማ ልማት ኮሚሽን ጋር በትብብር የሕግ ማስከበር ሥራ ለመሥራት ውል ገብተው እየሠሩ መሆኑን ዮሴፍ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። እንደ ዮሴፍ ገለጻ እርድ በሚከናወንበት ጊዜ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እንዳይከሰት ከወትሮው በተለየ መልኩ ትኩረት ስለሚሻ ችግር እንዳይፈጠር በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።
ከዚህ በፊት የእርድ አገልግሎት ላለመክፈል በራሳቸው መንገድ እርድ የሚያከናውኑ አካላት እስከ አሁን የነበረው የገንዘብ ማዳን ጉዳይ ስለነበር ሰው ወደ ቄራ አይሄድም ያሉት ምክትል ሥራ አስፈጻሚው፣ በአሁኑ ጊዜ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን በመከላከል የሕይወትን ቀጣይነት መጠበቅ ስለሆነ ትኩረት ተሰጥቶት የእርድ ሥራዎች በቄራዎች ይከናወናሉ ተብሎ እንደሚታሰብና የሕይወት ጉዳይ ስለሚሆን የግድ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።
ድርጅቱ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ከወትሮው በተሻለ ጥንቃቄና ንፅህናውን በጠበቀ ሁኔታ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑንም እና እርድ ለማከናወን ወደ ቄራ ለሚመጡ ደንበኞች ከስጋት ነጻ በሆነ መልኩ ለማስተናገድ መዘጋጀቱን ምክትል ሥራ አስፈጻሚው ገልፀዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 76 ሚያዝያ 10 2012



