ራይድ ኩባንያ በ4 ሚሊዮን ብር ቴስላ መኪናን በማስገባት ሙከራ ሊያደርግ ነው

0
1423

የኤሌክትሮኒክስ የታክሲ አገልግሎት በመስጠት የሚታወቀው ራይድ ኩባንያ በ4 ሚሊዮን ብር ቴስላ የተሰኘ የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ሙከራ ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ። የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ሳምራዊት ፍቅሩ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰራው የቴስላ ኩባንያ ምርት የሆነን ተሸከርካሪ ወደ አገር ውስጥ በማምጣት በኅብረተሰቡ ዘንድ ስለ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ለመስራት በዝግጅት ላይ እንደሆኑ አስታውቀዋል።

በኮቪድ 19 ምክንያት የሙከራ ስራው ከተያዘለት ከመጋቢት 2012 የመጀመሪያዎቹ ቀናት የተገፋ ሲሆን በጊዜያዊነት የሙከራ ጊዜው ከኹለት ሳምንታት በኋላ በአዲስ አበባ እንዲካሔድ ቀን እንደተቆረጠለት  ሳምራዊት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። እንደ ሳምራዊት ገለጻ ተሸከርካሪውን ኹሉም የኅብረተሰብ ክፍል በተለይም ደግሞ ፖሊሲ አውጪዎች እንዲሞክሩት እና በኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች ዙሪያ ያላቸውን ግንዛቤ በመቀየር በመንግሥት ደረጃ አዳዲስ ፖሊሲ ለውጦች እንዲኖሩ መጠቆሚያ እንደሚሆን ተናግረዋል። አያይዘውም በነዳጅ የሚሰሩ ተሸከርካሪዎችን በቀጣይ በኤሌክትሪክ በሚሰሩ ተሸርካሪዎች የመተካት ዕቅድ እንዳላቸውም ዋና ስራ አስፈጻሚዋ አስታውቀዋል። በአዲስ አበባ በሚደረገው የሙከራ ጊዜ ሰዎች ተመዝግበው በሚወጣላቸው መርሃ ግብር መሰረት ተሸከርካሪውን መሞከር እንደሚችሉ ተጠቅሷል። ለሙከራ የገባው ተሽከርካሪ እስካሁን አንድ ሲሆን 4 ሚሊዮን ብሩም የተሽከርካሪው ዋጋ እንደሆነ ታውቋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here